በእንግሊዝ ሀገር የመጀመሪያው ሐዊረ-ሕይወት ተካሄደ

በዩናይትድ ኪንግደም ንዑስ ማእከል

ነሐሴ 8 ቀን 2009 ዓ.ም.

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤ/ማ/ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን አዉሮፓ ማእከል የዩናይትድ ኪንግደም ንዑስ ማእከል ያዘጋጀዉ የመጀመሪያ ዙር የሐዊረ-ሕይወት መርሐ ግብር ሐምሌ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በዩናይትድ ኪንግደም የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ማእከል (ስቲቪኔጅ) ተካሄደ። በተለያዩ የእንግሊዝ ከተሞች የሚኖሩ ከ200 በላይ የሚሆኑ ምእመናን መነሻቸዉን ለንደን እና በርሚንግሃም ከተሞች ባደረጉ አራት አዉቶቡሶች ወደ ቦታዉ ተጉዘዋል።

መርሐ ግብሩ በካህናት አባቶች በጸሎት ከተከፈተ በኋላ በማኅበረ ቅዱሳን የአዉሮፓ ማእከል ሰብሳቢ የሆኑት ቀሲስ ዶ/ር ያብባል ሙሉዓለም የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።  በዩናይትድ ኪንግደም የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ አቡነ አንጌሎስ (Bishop Angaelos) በመርሐ ግብሩ ላይ በመገኘት ጉባዔዉን ባርከዉ አባታዊ ምክር ሰጥተዋል። ለዕለቱ ከተዘጋጁት ትምህርቶች መካከል የመጀመሪያ የሆነዉ እና መሰረታዊ የቤተ ክርስቲያናችን የነገረ ክርስቶስ አስተምህሮዎች ላይ ያጠነጠነዉ ትምህርት የርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ በሆኑት መጋቤ ሐዲስ ቀሲስ አባተ ጐበና ተሰጥቷል ።

በማስከተልም በጽሑፍ፣ በድምጽ እና በምስል የታገዘ ስለማኅበረ ቅዱሳን አመሠራረትና ዓላማ፣ ማኅበሩ የተለያዩ አካላትን በማስተባበር ስለሠራቸው ሥራዎች በተለይም  ስብከተ ወንጌል ባልተስፋፋባቸው ቦታዎች ላይ ስለሚካሄደው የስብከተ ወንጌል ማስፋፍያ መርሐ ግብር እንዲሁም አብነት ት/ቤቶች እና ገዳማት ያሉባቸዉ ችግሮችና ራሳቸዉን እንዲችሉ ለማድረግ የተሠሩትን እና እየተሠሩ ያሉትን ሥራዎች የሚያሳይ ገለፃ ተደርጓል። የዕለቱ ሁለተኛ ትምህርት የሆነዉ “የንስሐ ህይወት” በሊቀ ሊቃዉንት ገብረሥላሴ አባይ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ ክርስቲያን የሰሜን ምዕራብ አዉሮፓ ሀገረ ስብከት ትምህርት ክፍል ኃላፊ እና የለንደን ደብረ ገነት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ተሰጥቷል።

MKUK Hawire Hiwot2 Pict Two

ከወላጆች መርሐ ግብር በተጓዳኝ መዝሙር ጥናት፣ ትምህርት እንዲሁም የጥያቄና መልስ ዉድድር ያካተተ የልጆች መርሐ ግብር የተካሄደ ሲሆን በጥያቄና መልስ ዉድድር ላይ ለተሳተፉ ልጆች የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።

በመቀጠል የዩናይትድ ኪንግደም ንዑስ ማእከል ሰብሳቢ ዶ/ር ዶዮ ግራኝ ለጉባዔዉ ዝግጅት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሰሜን ምዕራብ አዉሮፓ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት፣ በለንደን እና ከለንደን ዉጭ ለሚገኙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔያት እና የጽዋ ማኅበራት፣ በዩናይትድ ኪንግደም የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ማእከል፣ በገንዘብ እና በተለያየ መልክ ለረዱ ድርጅቶች፣ በተለያየ ደረጃ  በጉልበታቸዉ፣ በገንዘባቸዉና በጊዜአቸዉ ለተሳተፉ ምእመናን በሙሉ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን  በተለያዩ ምክንያቶች መርሐ ግብሩ በታሰበዉ ሰዓት ባለመጀመሩ ባስከተለዉ የሰዓት ሽግሽግ ምክንያት ለመጀመሪያዉ ክፍል የትምህርት  የተሰጠዉ ሰዓት መቀነስ እና ለምእመናን ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥበት መርሐ ግብር መታጠፍ ተሳታፊዉን ይቅርታ ጠይቀዋል።

በመጨረሻም የሰሜን ምዕራብ አዉሮፓ ሀገረ ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ ክፍል ኃላፊ  ሊቀ  አዕላፍ ቆሞስ አባ አሮን የሀገረ ስብከቱን መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ መርሐ ግብሩ በጸሎት ተፈጽሟል።

MKUK Hawire Hiwot

የዕለቱን መርሐ ግብር በተመለከተ ከተሳታፊ ምእመናን የተሰበሰበ አስተያየት እንደሚያመለክተዉ ምእመናን በመርሐግብሩ ጠቃሚ ትምህርት እንዳገኙ እና የዚህ ዓይነቱ መርሐግ ብር ቀጣይነት እንዲኖረዉ የጠየቁ ሲሆን አሁን የታየዉ የሰዓት አጠቃቀም ችግር ወደፊት መስተካከል እንደሚገባ አሳስበዋል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!