ሀገረ ስብከቱ የመጀመሪያውን “ዝክረ ቅዱስ ያሬድ“ መርሐግብር አካሄደ

በጀርመን ን/ማእከል ኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ክፍል

ግንቦት 20 ቀን 2008 ..

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በደቡብ፣ ምሥራቅ እና ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት የቤተ ክርስቲያናችን የዜማ አባት የሆነውን ቅዱስ ያሬድን ሕይወቱን እና ሥራዎቹን የሚዘክር “ዝክረ ቅዱስ ያሬድ“ የተሰኘ መርሐግብር በጀርመን ካርልስሩኸ ምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ከግንቦት 12-14 2008 ዓ.ም. በደማቅ ስነ ሥርዓት አከበረ። በሀገረ ስብከቱ አስተባባሪነት እና በካርልስሩኸ ም/ቅ አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አዘጋጅነት በቀረበው መርሐግብር ላይ ከተለያዩ ሃገራት የተጋበዙ መምህራን፣ ጥናት አቅራቢዎች፣ በጀርመን እንዲሁም በፈረንሳይ ፓሪስ ያሉ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች፣ ምእመናን እና መዘምራን እንዲሁም ጀርመናዉያን እንግዶች በአጠቃላይ 400 የሚደርሱ ታዳሚዎች ተገኝተዋል።

Kyared1

አርብ ግንቦት 12 ማምሻውን በጸሎት በተከፈተው መርሐግብር ላይ በዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርት ከተሰጠ በኋላ መዝሙራት የቀረቡ ሲሆን መርሐግብሩ ቅዳሜ ከረፋዱ ጀምሮ እስከ እኩለ ሌሊት ቀጥሎአል ። በቅዳሜው መርሐ ግብር ላይ ከትምህርት በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዜማ ከቅዱስ ያሬድ በፊት እና በኋላ ምን እንደሚመስል እንዲሁም የቅዱስ ያሬድ ዜማ ለእኛ እንዴት ደረሰ በሚሉት ጉዳዮች ዙሪያ የመጀመሪያውን ጥናት ያቀረቡት መልአከ ስብሐት ተክሌ ሲራክ የካርልስሩሀ ም/ቅ/አቡነ ተክለሃይማኖት እና የክሮንበርግ ቅዱስ ዑራኤል አብያተክርስቲያናት አስተዳዳሪ ናቸው ። በመቀጠልም የአብነት ትምህርት ቤቶች አሁን ያሉበትን ሁኔታ በተለይም ችግሮቻቸውን እና ችግሮቹን ለመፍታት በማኅበረ ቅዱሳን አስተባባሪነት በምእመናን እየተሰሩ ያሉ አበረታች ተግባራትን ቀሲስ ዶ/ር ያብባል ሙሉዓለም በማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል ሰብሳቢ አቅርበዋል። ሶስተኛው ጥናት በቅኔ አጀማመር ላይ የቅዱስ ያሬድ አስተዋጽኦ በሚል ርእስ በመጋቤ ምሥጢር ኅሩይ ኤርምያስ የካስል ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም እና የዳርምሽታት ሐመረ ኖህ ኪዳነ ምሕረት አብያተክርስቲያናት አስተዳዳሪ እና የደ/ም/ም አውሮፓ ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ የቀረበ ሲሆን ቅዱስ ያሬድ የቤተ ክርስቲያናችን የዜማ ብቻ ሳይሆን የቅኔም አባት ተብሎ ሊጠራ እንደሚችል ማስረጃዎችን በመጥቀስ አብራርተዋል። የመጨረሻውን ጥናት ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥነ-ልሳንና ፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ ሲሆኑ የቅዱስ ያሬድ አስተዋጽኦ ለኢትዮጵያ የስነጽሑፍ ሀብትም ከፍተኛ እንደሆነ አብራርተዋል ። ከጥናቶቹ እና ስብከተ ወንጌል በተጨማሪም የበርሊን፣ የሀምቡርግ፣ የሙኒክ፣ የቩርዝቡርግ፣ የዳርምሽታት፣ የክሮንበርግ፣ የካርልስሩኸ እና የዱሰልዶርፍ ሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን ያሬዳዊ ዝማሬ በማቅረብ ለዝግጅቱ ልዩ ውበት ሰጥተውታል።

መርሐግብሩ በማኅሌት በቅዳሴ በመዝሙር እና በትምህርት እሁድ እለትም የቀጠለ ሲሆን ከቅዳሴ በኋላ መልአከ ሕይወት ፍስሐ ድንበሩ የፓሪስ ደ/ም/ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ትምህርት የሰጡ ሲሆን ተጋባዥ እንግዶችም ንግግር አድርገዋል ።

Kyared2

የቅዱስ ያሬድ መታሰቢያ ክብረ በዓል በአውሮፓ ምድር እንዲጀመር ሀሳቡን ያቀረቡትንና እውን ሆኖ እንዲተገበር ብርቱ ጥረት ያደረጉትን መልአከ ስብሐት ተክሌ ሲራክን በማመስገን የሀገረ ስብከቱን መልእክት ያስተላለፉት የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ መጋቤ ምሥጢር ኅሩይ ኤርሚያስ ይህ መርሐግብር ይዘቱ ወደ ፊት ሊሠፋ እንደሚችል እና ምእመናኑ ስለቤተ ክርስቲያናቸው ትውፊት ሥርዓትና ቀኖና በቂ እውቀት እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራ ሊሠራበት እንደሚገባ ገልጸዋል። መርሐግብሩ በሀገረ ስብከቱ ሥር በሚተዳደሩ የተለያዩ አድባራት እየተዘዋወረ እንደሚከበር ያስታወቁት ዋና ጸሐፊው የቀጣዩን ዓመት የሚያዘጋጀውን አጥቢያ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ተወያይቶ በቅርቡ እንደሚያሳውቅ ገልጸዋል። መልአክ ስብሐት ተክሌ ሲራክ በበኩላቸው ለመርሐግብሩ ድምቀት ከየአጥቢያው ለመጡት አስተዳዳሪዎች፣ መምህራን፣ ጥናት አቅራቢዎች፣ መዘምራን እና ምእመናን ከፍተኛ ምሥጋና አቅርበዋል።