ምኵራብ

ዲያቆን አለባቸው በላይ

የካቲት 25 ቀን 2009 ዓ.ም

 

ቅዱስ ወንጌል እንደሚነግረን በምኵራብ ያገለግሉ ዘንድ የተሾሙ ካሕናተ አይሁድ እና የጥቅም ተጋሪዎቻቸው ኃላፊነታችውን ረስተው፣ዓላማችውን ዘንግተው ቅዱስ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቤት መንፈሳዊ ገበያነቱ ቀርቶ የሥጋ ገበያ፤ ቅጽረ ምኵራብን የወንበዴዎች መናኻሪያ (ማቴ 21:13፤ ሉቃ19:46) አድርገውት ነበር። በዚህ ምክንያት በቤቱ ተገኝቶ ጸሎት ማድረስ፤ መባእ ማቅረብ፤ ከፈጣሪ ጋር መገናኘት የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ስለዚህ ነው አምላክ ወልደ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በምኵራብ ተገኝቶ ካህናቱን እና ሻጭ ለዋጮችን በመገሰጽ፤ በመግረፍ፤ ገበያውን በመበተን ቤቱን ያነጻውና ክብርና ልዕልናዋን በተግባር ያስተማረው።

ይህ አምላካዊ ሥራ ነቢያት አስቀድመው በትንቢት መነጽር ያዩትና የተናገሩት እንጅ እንደ እንግዳ ደራሽ የመጣ አልነበረም። ነቢዩ ዳዊት እና ነቢዩ ሶፎንያስ “የቤትህ ቅናት በልታኛለችና” (መዝ 68:9) “በእግዚአብሔር የቁጣ ቀን ብራቸው ሆነ ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም መላይቱ ምድር በቅናቱ ትበላለችና”(ሶፎ 1:18) በማለት የተናገሩት ትንቢት መድረሱን፤ እርሱም ኦሪትና ነቢያትን ሊፈጽም የመጣ አምላክ እንደሆነም (ማቴ 5:17) አስተምሯቸዋል።

የእግዚአብሔር ቤት ሥጋዊና መንፈሳዊ ድኅነት የሚታደልባት የምሕረት ቤት መሆኗን ይረዱ ዘንድ፤ ወደ እርሱ የመጡ ዕውሮችና አንካሶች በምኩራብ ፈውሷቸዋል (ማቴ 21:14)። ስለዚህ ቤተ እግዚአብሔር ካሕናት እና  ምእመናን ከፈጣሪያቸውና ከቅዱሳን ጋር በጸሎት፣በምስጋና፣ የሚገናኙበትና በረከተ ሥጋ ወነፍስ የሚታደልበት እንጅ የወንበዴዎች ዋሻ አለመሆኗን ልብ ይሏል።

አምላካዊ ሥራ ከተገለጠበት ከዚህ ታሪክ የሚከተሉትን ዓበይት ነጥቦች ለክርስቲያናዊ ሕይወታችን መመሪያ አድርገን መውሰድ ይኖርብናል ።

. ክብረ ቤተ መቅደስን መጠበቅ

ስለ ቤተ መቅደስ ስናስብ ሕንጻ ቤተክርስቲያኑን ብቻ ሳይሆን ማኅደረ መንፈስ ቅዱስ ይሆን ዘንድ የተፈጠረ የእያንዳንችንንም ሰውነት ነው (1ቆሮ 3:16)። ቤተ ክርስቲያንን ከክርስቲያን ፤ ክርስቲያንንም ከቤተ ክርስቲያን መለየት አይቻልምና። ካሕናተ አይሁድ እና ሕዝቡ በሥጋዊ ሐሳብና ሥራ መጠመዳቸው የተቀደሰውን የእግዚአብሔር ቤት ወደ ገበያነት እንዲቀይሩ አድርጓቸዋል። ሥለዚህ በደመ ክርስቶስ መሰረትነት፤በቅዱሳን ግድግዳና ጣሪያነት የታነጸ  የእግዚአበሔር ቤት፤ የቤተ ክርስቲያንን ክብር የተረዱ በቅድስናና በንጽሕና በቤቱ የሚያገለግሉ ካሕናትና ምእመናንን ይፈልጋል። ለዚህም ነው ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ይህች የእግዚአብሔር ደጅ ናት ጻድቃን ወደሷ ይገባሉ” ሲል የተናገረው (መዝ118:20)።

 

. ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ማወቅና መፈጸም

የሰማያዊት ኢየሩሳሌም፤ የመንግስተ እግዚአብሔር ምሳሌ የሆነችው ቤተ ክርስቲያን የምትመራበት ሥርዓት አላት። ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ልዩ የሚያደርጋት ዕንቍ ከሆነ መሠረተ እምነቷ ጋር ሥርዓቷ ነው።ይህ ሥርዓት ከዓለመ መላእክት ጀምሮ ያለ እስከ ኅልፈተ ዓለም የሚኖር ነው።ቅዱሳን አባቶቻችን በዘመናት ስለዚህ አማናዊ ሥርዓት ክብር በስፋት አስተምረዋል፤ ራሳቸውን አሳልፎ እስክ መስጠት መከራ በመቀበል ጠበቀው አስረክበውናል። ካሕናተ አይሁድ እና ሕዝቡ ይህንን በመዘንጋት ነው ከሥርዓት ውጭ የሆነ ተግባር በቤተ እግዚአብሔር ሲፈጽሙ የነበሩት።

ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በግልም ይሁን በማኅበር፤ በአንድም ይሁን ሌላ የአገልግሎት ዘርፍ በቤተ ክርስቲያንና በክርስትና ሕይወት ስንኖር ሁሉን በአግባብና በሥርዓት ልናደርግ እንደሚገባ ይመክረናል (1ቆሮ 14:40)። ሥለዚህ እኛም ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በመረዳት፤ በቤቱ ሊደረግ የሚገባውን ብቻ በማድረግ የቅዱሳን አባቶቻችንን ፈለግ ልንከተል በረከታቸውም ሊደርሰን ይገባል።

እግዚአብሔር አምላክ “እሽ ብትሉ ለእኔም ብትታዝዙ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤እምቢ ብትሉ ግን ብታምጹም ሰይፍ ይበላችኋል” ብሎ ነቢዩ ኢሳይያስ አድሮ እንደተናገረ (ኢሳ 1:19-20)፤  የቤተ ክርስቲያንን ክብርና ሥርዓት ጠብቀን በተቀደሰ ዓላማ አንድ ሁነን በመንፍሳዊ ቅናት የምንመላለስ ከሆነ እግዚአብሔር በረከቱን  ሊያድለን የታመነ አምላክ እንደሆነ፤ እንደ ካሕናተ አይሁድ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቤት ሥጋዊ ገበያ የምናደርግ ከሆነ ግን ከቤቱ፣ከፍቅሩ እንደምንለይ እንደምንቀጣ፤ እግዚአብሔር ግን ቤቱን እንደሚጠብቅ ልናስተውል ያስፈልጋል።

. ካሕናትና መናን የዓላማ አንድነት ሊኖራችው እንደሚገባ

የካሕናትና ምዕመናን ጉዳይ የመንፈሳውያን አባቶችና ልጆች ጉዳይ ነው። ልጅ የራሱ ድርሻ እንዳለ ሆኖ በዋናነት ግን የሚመስለው አባቱን ነውና ካሕናትና ምእምናን የእግዚአብሔርን መንግስት መውረስ ተቀዳሚ ዓላማችው ሊሆን እንደሚገባ አያጠያይቅም።በምኵራብ የነበሩ ካሕናትና ወደ ምኵራብ ለጸሎትና መብዓ ለማቅረብ ይመጡ የነበሩ ሕዝብ የዓላማ አንድነት አልነበራችውም። በዚህ ምክንያት ምዕምናን ተጨንቀው ተጠበው መርጠው ይዘው ያመጡትን በሬ የከሳ፤ ወርቁን ነጭ ነው እግዚአብሔር አይቀበለውም በማለት ካሕናተ አይሁድ እና የዚህ ጥቅም ተጋሪዎች ምእመናኑን ያንገላቷቸው ነበር።ይህ የዓላማ ልዩነት ካሕናቱን መሪ ወይም ምሳሌ ሳይሆን መሰናክል ነው ያደረጋቸው።

ስለዚህ ካሕናትና ምእመናን በተቀደሰ ዓላማ አንድነት ሊኖራቸው እንደሚገባ፤ ይህ ካልሆነ ግን አንዱ ለሌላው መሰናክል እንደሚሆን ማስተዋል ያስፈልጋል። ቅዱስ ወንጌልም መሰናክል ከመሆን እንጠበቅ ዘንድ ይመክረናልና (ሉቃ17:1)።

.  ስለ ቤተ እግዚአብሔር መቅናት እንደሚገባ

ቅዱሳት መጻሕፍት የቅዱሳን አባቶቻችን ሕይወትና አገልግሎት አንዱ ምንጭ መንፈሳዊ ቅናት እንደሆነ ይነግሩናል። ለስም አጠራሩ ምስጋና ይግባውና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም በምኵራብ ለቤተ ክርስቲያን ክብርና ሥርዓት ዘብ መቆም የመንፈሳዊ ቅናት መገለጫ መሆኑን በተግባር አስተምሮናል። በተለይም ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ትውልዱ እንዲዘነጋና እንዲረሳ ጠላት በሚራወጥበት በዚህ ዘመን እንደ ነቢዩ ዳዊት፣ ነቢዩ  ኤልያስ እና ቅዱስ ጳውሎስ  ያሉ በመንፍሳዊ ቅናት የተመሉ መምህራን፤ እንደ ጠቢቡ ሰሎሞን፣ ነቢዩ  ኤልሳዕ እና ቅዱስ  ጢሞቴዎስ ያሉ ደቀመዛሙርት ቤተክርስቲያን ያስፈልጓታል (2ሳሙ 7:2፤ 1ነገ 18:36-37፤ ሐዋ 17:16)። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን የሁላችን ሁላችን የቤተ ክርስቲያን ነንና፤ በመንፈሳዊ ቅናት ተመልተን የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ያገባኛል ልንል ያስፈልጋል ።

በአጠቃላይ ይህን የምኵራብ ሳምንት በቤተክርስቲያን ካሕናት ምእመናንን እንዲያውቁ በማስተማር ምእመናንም ለተረዱት እና ላወቁት ሥርዓተ ቤተክርስቲያን በመቅናት እንዲሁም የቤተክርስቲያንን ክብር በመጠበቅ እና በማስጠበቅ እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን የጾሙን በረከት ሊቀበሉ ይገባል።

መንግስቱን እንድንወርስ አምላከ ቅዱሳን ሁላችንንም ይርዳን!

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር