በቩርዝቡርግ ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ዐውደ ርእይ ተካሔደ።

በጀርመን ንዑስ ማእከል

መጋቢት 26 ቀን 2009 ዓ.ም

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሰ/ት/ቤ/ማ/መምርያ ማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማእከል የጀርመን ንዑስ ማእከል እና የቩርዝቡርግ ቅዱስ ማርቆስ ሰበካ ጉባዔ በመተባበር ከየካቲት ፳፭ እስከ የካቲት ፳፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ዐውደ ርእይ እና የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር አካሄዱ። ዐውደ ርእዩ የቩርዝቡርግ ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ በሆኑት በቀሲስ ገብረማርያም እና የአውሮፓ ማእከል ሰብሳቢ በሆኑት በቀሲስ ዶ/ር ያብባል ሙሉዓለም የተከፈተ ሲሆን ፍኖተ ቤተ ክርስቲያን፣ ዝክረ ገዳማት ወቤተ ጉባኤ እና ማኅበረ ቅዱሳን የሚሉ ሦስት ክፍሎችን ያካተተ ነበረ።

በዐውደ ርእዩ የመጀመሪያ ክፍል የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሕገ ልቡና፣ በሕገ ኦሪት እና በሕገ ወንጌል የነበረው ጉዞዋ፣ ያሳለፈቻቸው የፈተና ወቅቶች እና ወርቃማ ዘመናት እንዲሁም አሁን ያለችበት ነባራዊ ሁኔታዎች ተዳሰዋል። በሁለተኛው ክፍል የቤተክርስቲያኗ መሠረት የሆኑት ገዳማት እና የአብነት ትምህርትቤቶች ታሪክ፣ ያበረከቱት አስተዋጽኦ፣ያሳለፏቸው ፈተናዎች እና አሁን የገጠማቸው ችግር እንዲሁም ማኅበረ ቅዱሳን የገዳማት እና አብነት ት/ቤቶችን ችግር ለመቅረፍ ያከናወናቸው እና በማከናወን ላይ ያለው ተግባራት በዝርዝር ቀርበዋል። ሦስተኛው የዐውደ ርእዩ ክፍል የማኅበረ ቅዱሳን የአመሰራረት ታሪክ፣ መዋቅራዊ አሰራሩ እና ተግዳሮቶቹ የቀረቡ ሲሆን  በዐውደ ርእዩ ማብቂያ ላይ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

20170304_164911 20170304_173917

ከአውደ ርእዩ በተጨማሪም በቀሲስ ዶ/ር ያብባል ሙሉዓለም እና በቀሲስ አብርሃም አሰፋ ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል። የአጥቢያው ምእመናን በሁለቱ ቀናት ውስጥ ገዳማት እና አብነት ት/ቤቶችን ለመርዳት የተለያዩ ድጋፎችን ያደረጉ ሲሆን ለወደፊቱም በአጥቢያው ስም በማኅበረ ቅዱሳን ከተጠኑ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱን በመምረጥ ድጋፍ ለማድረግ ተስማምተዋል።

በመጨረሻም ለመርሐ ግብሩ መሳካት ከፍተኛ ድጋፍ ያደረጉትን የሰበካ ጉባኤ አባላት እና ምእመናኑን ቀሲስ ዶ/ር ያብባል አመስግነው በአባቶች ጸሎት የዝግጅቱ ፍጻሜ ሆኗል።