የመስቀል (ደመራ) በዓል በፊንላንድ ርዕሰ መዲና በሄልሲንኪ ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ በድምቀት ተከበረ።

በአውሮፓ ማእከል ኅ/ኤ/ሚ ክፍል

መስከረም 26 ቀን 2009 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አዘጋጅነት በተካሄደው የደመራ በዓል ላይ የደብሩ አገልጋይ ካህናት ዲያቆናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን እና ምዕመናን ተገኝተዋል።  በተጨማሪም የሄልሲንኪ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ካህናት እና ምእመናን፣ ከከተማው የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች  እና ጋዜጠኞችም  በበዓሉ ላይ ተካፍለዋል።

በዓሉ ከምሽቱ 11፡30 (16:30 CET) ላይ በጸሎት ተጀምሮ ዕለቱን የሚያዘክር  ስብሐተ እግዚአብሔር ደርሷል። ከዚያ በማስቀጠል የደብሩ ሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን ወረብና መዝሙራትን አቅርበዋል። እንዲሁም የደብሩ አዳጊ ሕጻናትም መዝሙራትን እና በዓሉን የሚዘክሩ ጽሑፎችን በፊኒሽኛ ቋንቋ ለህዝቡ አቅርበዋል።

dsc_0783 dsc_0123-1

 

በዓሉን  በተመለከተ አጠር ያለ ትምህርተ ወንጌል በደብሩ አስተዳዳሪ መጋቤ ብሉይ ቀሲስ ለማ በሱፍቃድ ተሰጥቷል። የደመራው ችቦ ከመለኮሱ ቀደም ብሎ የደብሩ እና ከኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  የመጡ ካህናት በጋራ ያሬዳዊ ዜማ አቅርበዋል።

ደመራው በደብሩ አስተዳዳሪ ተባርኮ  በካህናቱና በተጋባዥ የክብር እንግዶች አማካኝነት ተለኩሷል:: አስተዳዳሪው በዓሉ በአደባባይ እንዲከበር ከፍተኛ እገዛ ያደረገውን የከተማው መስተዳዳር አመስግነው፤ በዓሉ በጸሎት ተፈጽሟል። የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በ2004 ዓ.ም በወቅቱ የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ በነበሩት በብጹዕ አቡነ እንጦንስ ተባርኮ አገልግልቶ በመስጠት ላይ ይገኛል።

በበዓሉ ላይ የተገኙት የሄልሲንኪ ከተማ ምክትል ከንቲባ ሪትቫ ቬልያነን በበዓሉ ላይ በመገኝታቸው ከፍተኛ የሆነ የደስታና የመደነቅ ሰሜት እንደ ተሰማቸው እና  እንደዚህ አይነቱ ታላቅ በዓል በፊላንድ ሄልሲንኪ መከበሩ ብዙኃነትን  እንዲጨምር ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።