የጌታችን ትንሣኤ

ልጆች ስለ ጌታ ከሞት መነሣት ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? እስቲ ትንሽ ስለ ትንሣኤው ልንገራችሁ:: ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አይሁድ ዓርብ ቀን በሐሰት ሰቅለው ከገደሉት በኋላ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ሥጋውን ከመስቀል ላይ አውርደው በንጹህ በፍታ ገንዘው በአትክልት ቦታ በሚገኝ አዲስ መቃብር ውስጥ ቀበሩት። ትልቅ ድንጋይም አንከባለው የመቃብሩን አፍ ዘጉት። በአይሁድ የታዘዙ ብዙ ጭፍሮች (ወታደሮች) የጌታችንን መቃብር ይጠብቁ ነበር።

ልጆች፣ ጌታችን ከሞት ሲነሣ የታዩትን ድንቃ ድንቅ ነገሮች ታውቃላችሁ? ይኸዉላችሁ በሦስተኛውም ቀን ሌሊት ታይቶና ተደርጎ የማይታወቅ የሚያስደንቅ ልዩ ነገር ተከሰተ፡፡ በአንድ ጊዜ በድንገት የመሬት መንቀጥቀጥ ሆነ፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዝግ መቃብር ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ።

ልጆች፣ የጌታችንን ትንሣኤ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማየት የታደለችውን ሴት ታውቋታላችሁ?  ስሟ መግደላዊት ማርያም ይባላል:: ነገሩ እንዲህ ነው:- እሁድ ማለዳ ገና ጨለማ ሳለ መግደላዊት ማርያም ወደ መቃብሩ ሄደች ድንጋዩም ከመቃብሩ ተንከባልሎ አየች። ልጆች የመቃብሩን ድንጋይ ማን እንዳንከባለለዉ ታውቃላችሁ? ቅዱሳን መላእክት ናቸው፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱን ሰዎች እንዲያውቁ ድንጋዩን አንከባለሉት፡፡ ማርያም ይህን ስትመለከት እየሮጠች ወደ ቅዱስ ጴጥሮስና ጌታችን ይወደው ወደ ነበረው ደቀመዝሙር (ቅዱስ ዮሐንስ) ሄዳ፣ “ጌታን ከመቃብር ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አናውቅም አለቻቸው” ዮሐ. 20፣3። ደቀመዛሙርቱም ወደ መቃብር ሄዱ፡፡መግነዙን አይተዉ ትንሣኤዉን አምነው ወደ ቤታቸው ሄዱ፡፡