ጰራቅሊጦስ

በቀሲስ ኃይለኢየሱስ ተመስገን

ግንቦት 26 ቀን 2009 ዓ.ም.

በቅዳሴ ጸሎት ካህናት ከሚጸልዩት ጸሎት ውስጥ “ወቡሩክ መንፈስ ቅዱስ ጰራቅሊጦስ መጽንዒ ወመንጽሔ ኩልነ” የሚል እናገኛለን ሁላችንን የሚያነጻ፣ የሚያጸና መንፈስ ቅዱስም ቡሩክ ነው ማለት ነው። በዚህ ጸሎት ላይ ጰራቅሊጦስ የሚለው ቃል ከሦስቱ አካላት አንዱ ለኾነው ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መጠሪያ እንደሆነና የሚያነጻ፣ የሚያጸና መሆኑን ይገልጣል።

ጰራቅሊጦስ (Gr.παράκλητος, Lat.paracletus) የሚለውንም ቃል በሥርዓተ ቅዳሴ እና በቅዱስ ወንጌል ትርጓሜ ናዛዚ (የሚያጽናና)፣ ከሣቲ (ምሥጢርን የሚገልጥ)፣ መጽንዒ (የሚያጸና)፣ መንጽሒ(የሚያነጻ) ፣ መስተፍሥሒ (የሚያስደስት ደስታን የሚሰጥ) ፣ መስተሥርይ (ኃጢአትን ይቅር የሚል)  ብለው ቅዱሳን አበው ሊቃውንት ተርጉመውልናል። ጰራቅሊጦስ የሚለውን  ቃል በመጽሐፍ ቅዱስም  ላይ እናገኘዋልን። ለአብነትም የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል

  • ዮሐ. ፲፬፥፲፮ “ወአነ እስእሎ ለአብ ይፈኑ ለክሙ ጰራቅሊጦስሃ ካልአ ዘይሄሉ ምስሌክሙ እስከ ለዓለም” ለዘላለም ከናንተ ጋር የሚኖር  ጰራቅሊጦስን ይልክላችኋል ካልአ ባለውም አበው ሊቃውንት አንድ ገጽ የሚል ሰባልዮስን ረተውበታል።
  • ፩ ዮሐ. ፪፥፩ “ወእመኒ ቦ ዘአበሰ ጰራቅሊጦስ ብነ ኀበ አብ ኢየሱስ ክርስቶስ” በድሎ ንስሐ የገባ ሰው ቢኖር ኃጢአታችንን የሚያስተሠርይልን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ ዘንድ የሚሰድልን ጰራቅሊጦስ አለን።

የብሉይ ኪዳን  የእንስሳት መሥዋዕት ሲያበቃ ፶ኛው ቀን ይሰባሰብ የነበረው የአይሁድ ጉባኤም መንፈስ ቅዱስ ከወረደበት ዕለት ጀምሮ ተበትኗል።  መሥዋዕተ ኦሪቱ በአማናዊው መሥዋዕት በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም እንደ ተለወጠ ኹሉ ጉባኤ አይሁድም በኢየሩሳሌም ከተማ በተሰበሰቡ በቅዱሳን ሐዋርያት ጉባኤ ተለውጧል።

  • ሐዋ.፪፥፩-፲፭ ወአመ ተፈጸመ መዋዕለ ዸንጠቈስጤ እንዘ ሀለዉ ኵሎሙ ኅቡረ አሐተኔ።

የበዓለ ጰራቅሊጦስን ሁናቴ የሚያስረዳንም  ይህ በሐዋርያት ሥራ ላይ የተጠቀሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው። ከበዓለ ዸንጠቈስቴ በፊት ያለው ፯ ሳምንት (፵፱) ቀን በተፈጸመ ጊዜ በበዓለ ጰራቅሊጦስ ማለዳ ኹሉም በአንድ ቦታ ተሰብስበው ሳሉ

መጽአ ግብተ እምሰማይ ድምፅ ከመ  ድምፀ ነፋሰ ዓውሎ

እንደ ዐውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ ድንገት ከሰማይ መጣ ይላል። ነፋስ  ረቂቅ ነው መንፈስ ቅዱስም ረቂቅ ነውና ፤ ነፋስ  ኃያል ነው መንፈስ ቅዱስም ኃያል ነውና፤ ነፋስ  ፍሬውን ከገለባው ይለያል  መንፈስ ቅዱስም ጻድቃንን ከኃጥአን ይለያልና፤ ነፋስ  በምልዓት ሳለ አይታወቅም ባሕር ሲገሥጽ ዛፍ ሲያናውጥ ነው እንጅ  መንፈስ ቅዱስም በምልዓት  አይታወቅም ቋንቋ ሲያናግር ምስጢር ሲያስተረጉም ነውና፤  ነፋስ  መንቅሂ  ነው መንፈስ ቅዱስም መንቅሂ ነውና፤ ነፋስ  መዓዛ ያመጣል  መንፈስ ቅዱስም መዓዛ ጸጋን ያመጣልና፤ በነፋስ  ጥቅመ ሰናዖርን ሐራ ጰራግሞንን  አጥፎበታል ከዚያ ወዲህ ለመዓት እንጅ ለምሕረት አልተፈጠረም እንዳይሉ ለምሕረትም እንደተፈጠረ ለማጠየቅ እንደ ዓውሎ ነፋስ  ድምጽ ተሰማ አለ

ወመልአ ኵሎ ቤተ ኀበ ሀለዉ ይነብሩ ። ያሉበትንም ቦታ ሞላው።

ወአስተርአይዎሙ  ልሳናት  ክፉላት ከመ እሳት ዘይትከፈል ። ወነበረ ዲበ ኵሎሙ ።

እሳት ከአንዱ ፍና አምሳ ስልሳ ፍና እንዲያበሩበት የተከፋፈሉ የእሳት ላንቃዎች ታያቸው በኹሉም ላይ ተቀመጡባቸው (አደረባቸው)። እሳት ከአንዱ ፍና አምሳ ስልሳ ፍና ቢያበሩለት ተከፍሎ እንደሌለበት መንፈስ ቅዱስም ተከፍሎ ሳይኖርበት እስከምጽአት ድረስ ሲሰጥ ይኖራል። በእሳት ሰብአ ሰዶምን ሰብአ ገሞራን ከእስራኤል አንዱን ኅብር ደቂቀ ቆሬን አጥፍቶበታል  ከዚያ ወዲህ ለመዓት እንጅ ለምሕረት አልተፈጠረም እንዳይሉ ለምሕረትም እንደተፈጠረ ለማጠየቅ።

ወተመልኡ ኵሎሙ መንፈሰ ኃይል ።

ኃይል የሚሆናቸው ሀብትን፣ ሀብት የሚሆናቸው ዕውቀትን ገንዘብ አደረጉ።

ወአኀዙ ይንብቡ ዘዘዚአሆሙ በነገረ ኵሉ በሐውርት ።

ሁሉም በየራስ በየራሳቸው በሰብዓ ሁለት ቋንቋ መናገር ጀመሩ

በከመ  ወሀቦሙ መንፈስ ቅዱስ  ይንብቡ ።

ይናገሩ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ሀብቱን እንዳደላቸው መጠን በሐዋርያት ሰባ ሁለት ቋንቋ አልተከፈለባቸውም የቀሩት ግን ካሥራ አምስት በታች የወረደ የለም እንጅ እንደመጠኑ ኻያም ኻያ አምስትም ሠላሳም አርባም ሃምሳ ስሳም ተገልጦላቸዋል።

ወሀለዉ በኢየሩሳሌም ሰብእ ኄራን አይሁድ ይነብሩ እምኵሉ አሕዛብ ዘመትሕተ ሰማይ ።

ከሰማይ በታች ባለ ባራቱ ማዕዘን ካሉ አሕዛብ ተለይተው መጥተው በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ደጋግ ሰዎች ኢየሩሳሌም  ነበሩ ከምርኮ መልስ በኋላ እስራኤል በወደዱት አገር በሕጋቸው ይኖራሉ ለበዓል ይወጣሉ በዓለ ፋሲካን አክብረው ከዚያ አያይዘው ሰባት ሱባኤ ቈጥረው በአምሳኛይቱ ቀን በዓለ ሰዊትን ለማክበር አገር የቀረበው በየሀገሩ እየሄደ አገር የራቀበት ሥንቁን ይዞ ከዚያው ይሰነብታል በዚች ቀን የሄዱትም ተመልሰው ያሉትም ተሰብስበው ባንድነት ሳሉ

ወሰሚዖሙ ዘንተ ቃለ ተጋብአ ኵሎሙ ድንጉፃኒሆሙ  በሰባ ሁለት ቋንቋ  ሲናገሩ ሰምተዋቸው የአንክሮ ድንጋጤ እየደነገጡ ተሰበሰቡ

እስመ ሰምዕዎሙ ይነብቡ ኵሎሙ በነገረ በሐውርቲሆሙ በየሀገራቸው ቋንቋ ሲናገሩ ሰምተዋቸዋልና

ወደንገፁ ወአንከሩ ወይቤሉ አኮኑ ሰብአ ገሊላ እሉ ኵሎሙ  እሊህ ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን

እፎኑ እንከ ንሰምዖሙ ይነብቡ በነገረ ኵሉ በሐውርቲነ   በየሀገራችን ቋንቋ ሲናገሩ እንደምን እንሰማቸዋለን ብለው የአንክሮ ድንጋጤ ደነገጡ እሊህ የገሊላ ሰዎች ስንኳን የሌላ አገር ቋንቋ ያገራቸውን ቋንቋ ስንኳ ያላከናወኑ ናቸውና

እንዘ  ፍጥረትነ ጰርቴ ወሜድ ወኢላሜጤ ። ወእለኒ ይነብሩ ማእከለ አፍላግ ። ይሁዳ ወቀጳዶቅያ ወፎኖጦስ ወእስያ ። ወፍርግያ ወጱንፍልያ ። ወግብጽ ወደወለ ልብያ ። ወእለሂ እምቀርኔን ወእለሂ መጽኡ እምሮሜ አይሁድ ወፈላስያን ። ወእለ እምቀርጤስ ወዓረብ ።

እኛ የጳርቴና፣ የሜድ፣ የኢላሜጤም ሰዎች፣በሁለት ወንዝም መካከል በይሁዳ፣ በቀጶዶቅያ፣ በጳንጦስ፣ በእስያ፣በፍርግያ፣ በጵንፍልያ፣ በግብፅ፣ በቀሬና አጠገብ ባሉት በሊቢያ አውራጃዎች የምንኖር፣ ከሮም የመጣን አይሁድና ወደ ይሁዲነት የገባን፣ የቀርጤስና የዐረብ ሰዎች ስንሆን፣ ሰዎቹ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በየቋንቋችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን።

ወናሁ ንሰምዖሙ  ይነብቡ በነገረ በሐውርቲነ ዕበያቲሁ  ለእግዚአብሔር  በየሀገራችን ቋንቋ ሲናገሩ እንሰማቸዋለን የእግዚአብሔር ቸርነቱ ብለው አደነቁ

ወደንገፁ ኵሎሙ   ሁሉም የአንክሮ ድንጋጤ ደነገጡ

ወኃጥኡ ዘይብሉ ወዘይነብቡ  ለራሳቸው የሚናገሩት ለሌላው የሚመልሱት ምላሽ ቸገራቸው

ወተበሀሉ በበይናቲሆሙ ምንትኑ እንጋ ዝ  እርስ በርሳቸው ይህ ምንድን ነው ተባባሉ

ወመንፈቆሙሰ  ሰሐቅዎሙ  እኩሎቹ ግን ሣቁ ያደነቁ ከብሔረ አሕዛብ የመጡ ምዕመናን አይሁድ ናቸው የዋሀን ይላቸዋልና የሣቁ በከተማ የሚኖሩ እኩያን ሰቃልያነ አምላክ አይሁድ ናቸው

ወይብሉ እሉሰ ፃዕፈ ጸግቡ ወሰክሩ ።

እሊህሰ ያልፈላ ጉሽ ጠጅ ጠጥተው የሆነ ያልሆነውን ይቀባጥራሉ ብለው መጥላት ምቀኝነት ፈራሽ ነገር አናገራቸው ለልማዱ ጉሽ ጠጅ ቢጠጡት ከናላ ይወጣል ስንኳን የማያውቁትን ቋንቋ ሊያናግር የሚያውቁትን ስንኳ ቋንቋ ያስጠፋል እንዲህም ብለው በተናገሩ ጊዜ ፍጡራንን ብቻ ሰድበው የቀሩ አይደለም የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ለወይን ሰጥተው ፈጣሪንም ተናግረዋልና

ወቆመ ጴጥሮስ  ምስለ ዐሠርቱ ወአሐዱ ወከልሐ በቃሉ ቅዱስ  ጴጥሮስ ካሥራ አንዱ ጋር ቁሞ በመንፈስ ቅዱስ በተገለጠለት ቃሉ ተናገረ

ወይቤ አንትሙ ሰብአ ይሁዳ ወእለሂ ትነብሩ ኢየሩሳሌም ኵልክሙ አእምሩ ዘንተ ወስምዑኒ ቃልየ  እናንት የይሁዳ ሰዎች፤ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁላችሁም ፤ ይህን ነገር ዕወቁ፤ የምነግራችሁን ነገር ስሙ

አኮ ከመ ትትሐዘብዎሙ አንትሙ ስኩራን እሙንቱ ዘትብሉ እናንተ ጠጥታችሁ ሰክራችኋል እያላችሁ እንደምትጠረጥሯቸው አይደለም

እስመ ነግህ  ብሔሩ ወሶቤሁ ሠለስቱ ሰዓት  ጊዜው ነግህ ነውና እልፍም ቢል ከቀኑ ሦስተኛ ሰዓት ነውና ይላል

በቅዱስ ጴጥሮስ ትምህርት የተማረኩ አሕዛብም ምን እናድርግ  ብለው በጠየቁት ጊዜ ከክፋታቸው ተመልሰው፣ ንስሐ ገብተው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዲጠመቁ ነገራቸው፡፡ በዚያችም ሰዓት ሦስት ሺህ ሕዝብ በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ተጠምቋል  ይህም ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላ ያደረባቸው የማሳመን ጸጋና ተአምራትን የማድረግ ኃይላቸው እንደ በዛላቸው ያመላክታል፡፡

በቅዳሴ እግዚእ እና በዮሐ. ፲፬፥፲፯  ፈነዎ ለጰራቅሊጦስ መንፈሰ ጽድቅ  የጽድቅ መንፈስ የሆነ  ጰራቅሊጦስን ላከው የሚል ኃይለ ቃል እናገኛለን ።መንፈሰ ሐሰት አለና ከዚያ ሲለይ መንፈሰ ጽድቅ ይለዋል ።

ቅዱስ ዮሐንስ በመልዕክቱ “አኃዊነ ለኩላ መንፈስ ኢትእመኑ አላ አመክርዋ ለመንፈስ ለእመ እምኀበ እግዚአብሔር ይእቲ፣ ወንድሞች ሆይ መንፈስን ሁሉ አትመኑ ነገር ግን መናፍስት ለእግዚአብሔር ሆነው እንደሆነ መርምሩ” (፩ዮሐ ፬፡፩) ይለናል።

ሐሰተኛ ነቢያትና መምህራን በሐሰተኛው መንፈስ እየተነዱ   ክቡሩን የሰው ልጅ  ትርጉም አልባ በሆነ ጩኸት በምግባር በሃይማኖት ሲያጎሰቁሉት  እንደ እንስሳ ሣር ሲያስግጡት ይስተዋላልና ሐዋርያት በጽናት ያገኙት  መንፈሰ ጽድቅ በዋዛ ፈዛዛ የሚገኝ አለመሆኑን ምእመናን ማወቅ ይገባቸዋል።

ምንጭ (ወንጌል ቅዱስ ትርጓሜ  ፣መጽሐፈ ቅዳሴ፣መጻሕፍተ ሐዲሳት ሠለስቱ ትርጓሜ )