አብርሃ ወአጽብሐ

ግንቦት 30 ቀን 2006 ዓ.ም

ቅዱሳን ነገስታት አብርሃ ወአጽብሐ አባታቸው ታዜር እናታቸው ሶፍያ/አህየዋ/ በቅድስና የሚኖሩ እግዚአብሔርን በቅድስና በንጽህና የሚያገለግሉ ነገር ግን ልጅ ያላገኙ መካኖች ነበሩ። ስለሆነም ጌታ ሆይ ደስ የሚያሰኝህ በትዕዛዝህም የሚኖር ልጅ ስጠን እያሉ እግዚአብሔርን ይለምኑ ነበር፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን ስለ እግዚአብሔር ቸርነት ሲነጋገሩ ንግስት ሶፍያ የሐና እመ ሳሙኤልን ጸሎት በመጥቀስ እሷም እንደ ሐና ሱባኤ ገብታ ፈጣሪዋን እንድትለምን ንጉሱን ጠየቀችው፡ ንጉሱም “ ኦ ብእሲቶ ሰናየ ኁለይኪ” አንቺ ሆይ መልካም አስበሻል በማለት በምክሯ ተስማምቶ ሱባኤ ገብታ ፈጣሪዋን በጸሎት እንድትጠይቅ ፈቀደላት፡፡ ንግስት ሶፍያም የካቲት 18 ቀን ሱባኤ ገብታ ፈጣሪዋን መለመን ጀመረች፡፡ ከጸሎቷም ጥቂቱ “ በኪሩቤል ላይ የምትኖር፣ የቀለያትንም (ጥልቅ ባህርንም) የምትመለከት ጌታዬ ፈጠሪዬ ሆይ አቤቱ ጸሎቴንና ልመንያን ስማኝ፣ ልቅሶየንም አድምጥ ቸላ አትበለኝ” የሚል ነበር፡፡

ደጓ ንግስት ሶፍያ በብዙ ጸሎትና እንባ ሱባኤዋን ለመጨረስ ስትቃረብ፣ አንድ ራእይ ተገለጠላት፣ እሱም ከተራራ ላይ የተተከለች ረዥም ዛፍ አየች፡፡ ፍሬዋም ጫፍ እስከ ጫፍ የሞላ ነበር፡፡ ጫፎቿም ምድርን የሚሸፍኑ ነበሩ፡፡ አንድ ሰው፣ ብርሃን ለብሶ ብርሃን ተጎናጽፎ፣ በእጁም ትምህርተ መስቀል ያላት የወርቅ ዘንግ ይዞ መጣ፡፡ ሁለት መሰላልም ይዞ መሰላሎቹን ከዛች ዛፍ ግራና ቀኝ አቆማቸው፡፡ ንግስት ሶፍያ ግን የዚህ ራእይ ምስጢር አልረዳ ቢላት ተጨነቀች፣ ምስጢሩን ይገልጽላት ዘንድም ፈጣሪዋን ለመነች፡፡ የለመኑትን የማይነሳ እግዚአብሔርም የራሱ ባለሟል የሆነውን የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን ላከላት፡ መልአኩም ብርሃን ተጎናጽፎ ነበርና ከመልአኩም ግርማ የተነሳ የነበርችበት ቦታ ሁሉ ብርሃን ሆነ፡፡ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም በቀኝዋ ቁሞ ራእይዋን ተረጎመላት እንዲህም አላት፣ ያየሻት ዛፍ ወንጌል ናት፣ ዛፍዋ የተተከለችባት ተራራም ኢትዮጵያ ናት፣ የዛፏ ፍሬም ሃይማኖት ነው፣ ምድርን ያለበሱ ቅርንጫፎችም መምህራን ናቸው፣ ብርሃን ለብሶ መሰላሎቹን በዛፍዋ ግራና ቀኝ ሲያስቀምጥ ያየሽው ሰውም ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ተብሎ የሚጠራው ፍሬምናጦስ ነው፡፡ በእጁ የያዛት የወርቅ ዘንግም ጥምቀት ናት፣ እነዚህም ሁለቱ መሰላሎችም ልጆችሽ ናቸው፣ በመሰላሉ የሚወጡ የሚወርዱ ሰዎችም ምእመናን ናቸው፡፡ የሚበሉትም ፍሬ የክርስቶስ ስጋና ደም ነው ብላት ከእርሷ ተሰወረ፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታም መላአኩ ቅዱስ ሚካኤል ለንጉሡ በራእይ ተገልጾ “ ንጉሥ ሆይ እግዚአብሔር የሰጠህን እነዚህን እንቁዎች እንካ ተቀበል” ብሎት ተሰወረ፡፡ እግዚአብሔር ይሁን ብሎ የወደደውና የፈቀደው አይቀርምና እግዚአብሔር ንግስት ሶፍያንና ንጉሥ አዜርን በበረከት ስለጎበኘ ሶፍያ ጸነሰች፡፡ የጽንሷም ወራት በተፈጸመ ጊዜ ታህሳስ 29 ቀን በ 312 ዓ ም መንታ ልጆችን ወለደች፡፡ ሕጻናቱ ከተወለዱበት ቀን ጀምሮ እንደ አዋቂ ሰው በፍቅር ተጠምደው አንዱ ለሌላው በማሰብ ጡት እየያዙ አንደኛው ለሁለተኛው ይሰጣጡ ነበር፡፡ እንደ ሕጻናት ጸባይ አላለቀሱም፡፡ ነገር ግን “ ይትባረክ እግዚብሔር አምላከ አበዊነ” የአባቶቻችን አምላክ እግዚብሔር ይመስገን እያሉ ያመሰግኑ ነበር፡፡

እንደሙሴ ስርዓትም ወደ ቤተ መቅደስ ወሰዷቸው፡ እግዚአብሔር ተግዳሮትን /ሽሙጥን/ ከእኛ አራቀ ሲሉ ስማቸውንም አዝጓጉ ብለው ጠሯቸው፡፡ አዝጓጉ እግዚአብሔርን እንዲያገለግሉ በብፅዓት የተወለዱ ስለነበር በተወለዱ በአምስት አመታቸው በታላቅ ክብርና ሥነ ስርዓት ወደ ቤተ መቅደስ ገቡ፡፡ ኑሯቸውና ዕድገታቸው በቤተ መቅደስ ሆነ፡፡ መጻሕፍተ ኦሪትንም እየተማሩ አደጉ፡፡

አዝጓጉ በተወለዱ በ 12 አመታቸው ፣ ቤተ መቅደስ በገቡ በ 7 አመታቸው አባታቸው ንጉሥ ታዜር/ ሠይፈ አይዕርድ/ አረፈ፡፡ ምንም እንኳ እናታቸው ሶፍያ / አህይዋ/ ለጥቂት ጊዜ መንግስቱን ስትመራ እንደቆየች ቢታወቅም ፣ መንግስቱን ለዘለቄታው ለሚመራ ማስተላለፍ ግድ ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜ ግን ሁለት ዐበይት ችግሮች ተከሰቱ፡፡ እነሱም አንደኛ ልጆቹ የብፅዓት ልጆች በመሆናቸው ቤተ መቅደስ መግባታቸው፣ ሁለተኛ የንጉስ ልጅ ይሾም ቢባልም ልጆቹ በአንድ ጊዜ የተወለዱ መንትያዎች በመሆናቸው ለማንኛቸው መስጠት እንደሚቻል አሳሳቢና አስቸጋሪ ጉዳይ መስሎ ነበር፡፡ ግን ሰው የሚቸገረው እንደ ራሱ ፈቃድ እየተመራ በራሱ ውሳኔ ሲጓዝ እንጂ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሲሆን መፍትሔው ከእግዚአብሔር በመሆኑ ችግሩ ከባድ አልሆነም፡ በዚህ መሰረት ህዝቡ ሊቀ ካህናቱን ፍቃደ እግዚአብሔርን ጠይቅልን አሉት፡፡

ሊቀካህናቱ ወደቤተ መቅደስ ገብቶ የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ የአባቶቻችን አምላክ ፈጣሪዬ እግዚአብሔር ሆይ ሙሴን በደብረ ሲና፣ ሳሙኤልን በቤተ መቅደስ እንደተነጋገርካቸው ጸሎቴንና ልመናዬን ስማኝ ህንም ከእኔ አትመልስ ፈቃድህን የሚነግረኝን ደገኛውን መልአክህን ላክልኝ ብሎ ጸለየ፡፡

እግዚአብሔር ልመናውን ሰማና መልአኩ ሚካኤልን ላከለት እንዲህም አለው፦ እግዚአብሔር እነዚህ ሁለቱን ልጆች አንግሥ፣ ሁለቱንም በአንድ መንበር አስቀምጣቸው ብሎሃል አለው፡፡ ልጆቹ ግን እኛስ ለእግዚአብሔር የብፅዓት ልጆች ሁነን ተሰጠናልና መንገሥ አይገባንም፣ ሌላ ንጉሥ ፈልጉ አሉ፡፡ ህዝቡም እጅግ አዘኑ፡፡

ነገር ግን ነገሩ ፈቃደ እግዚአብሔር ስለነበር መልአኩ መጥቶ በዘመናችሁ ብዙ ሥራ ይሠራ ዘንድ አለውና፣ በእጃችሁም አብያተ ክርስትያናት ይታነጻሉና እሺ በእጄ በሉ፡ የሊቀካህናቱንም ቃል ስሙ አላቸው፡፡ እነሱም የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን አሉ፡፡ ሥርዓተ ንግሥናቸውም በታላቅ ክብርና ሥርዓት ተፈጽሞላቸው ስመ መንግሥታቸውም ኢዛና እና ሳይዛና ተብለው ነገሡ፡፡ በአንድ መንበር ሁለቱም እንደ አንድ ሰው ሁነው ነገሡ፡፡ በሚያስደስትና በሚያስደንቅ ፍቅር ኢትዮጵያን መምራት ጀመሩ፡፡ በክፋት የተነሳባቸውን ጠላት አልተበቀሉም፡፡ በዘመናቸው ፍትህ አልተጓደለም፣ ድሀ አልተበደለም እንደ ነገስታት ሥርዓት በቤታቸው በር ዘብ አላቆሙም በገፊና በተገፊ ይፈርዱ ዘንድ ባደባባይ ይቀመጡ ነበር እንጂ፡፡ ኢትዮጵያ በዘመናቸው የታወቀች ሆነች /የዒዛና አገር ተብላ/ ዜናቸው በየአህጉሩ ሁሉ ተሰማ፡፡ በዘመናቸውም አመፀኛ ቀማኛ አልነበረም፡፡ ግን ወጣቶቹ ነገስታት አንድ ነገር ያስጨንቃቸው ነበር ይህን ጭንቀታቸውንም ለሊቀካህኑ ነገሩት፡፡ እኛን የሚያስጨንቀን ስለመንግስታችን አይደለም፡ ስለጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ነው እንጂ አሉት፡፡ እሱም ጌቶች ይህስ ሚስጥር ለእኔም ድንቅ ነው አላቸው፡፡ ነገር ግን በአልዓሜዳ የመጣ ፍሬምናጦስ የሚባል አንድ ሰው፡ እሱም እናተ የኢትዮጵያ ሰዎች ግዝረትና እምነት አላችሁ ጥምቀትና ቁርባን የላችሁም እያለ ይናገራል አላቸው፡፡

እነርሱም ፍሬምናጦስን አስጠርተው ስለነገረ ትስብእቱ ምስጢር እንዲያስረዳቸው ጠየቁት፡ እሱም ነብያት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው/ተመርተው/ አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ፡ ይወለዳል ካሉበት ጀምሮ የልደቱን፣ የጥምቀቱን፣ የትምህርቱን፣ የስቅለቱን፣ የሞቱን፣ የትንሳኤውንና የዕርገቱን ምስጢር በሚገባ አስተማራቸው፡፡ ሐዋርያትም በጌታ ተሾመው ዓለምን ዙረው ማስተማራቸውን ተረከላቸው፡፡ እነርሱም ፍሬምናጦስን ይህን ሥርዓት በሀገራችን እንድታስፋፋ አሉት፡፡ እርሱም በወቅቱ ስልጣነ ክህነት አልነበረውምና ይህን ስራ ለመስራት ስልጣነ ክህነት ያስፈልጋል አላቸው፡፡

ነገሥታቱም ደብዳቤ ጽፈው ወደ እስክንድርያው ፓትርያሪክ እንዲሾምላቸው ፣ ሀገራቸውንም ተዘዋውሮ እንዲያስተምርላቸው፣ ገጸበረከት በማስያዝ ፍሬምናጦስን ከብዙ ሊቃውንት ጋር ላኩት፡፡ ቅዱስ አትናቲዎስም ደብዳቤውን ባነበበ ጊዜ እጅግ ተደስቶ ፍሬምናጦስን አቡነ ሰላማ በማለት ሹሞ ወደ ኢትዮጵያ ሰደደው፡፡ ቅዱስ አትናቲዎስ ለአቡነ ሰላማና አብረው ለነበሩት ሊቃውንት መጻሕፍተ ብሉያትን፣ መጻሕፍተ ሐድሳትንና የሥርዓተ ቤተ ክርስትያን መጻሕፍትንና ሌሎች ንዋያተ ክዱሳትን አስይዞ ለነገስታቱ ደብዳቤ ጽፎ ከብዙ ገጸ በረከት ጋር በታላቅ ክብር ሸኘው፡፡

አቡነ ሰላማ ከቅዱስ አትናቲዎስ የተላከውን ደብዳቤ ለነገሥታቱ ካቀረበና የጉዞውን ነገር ሁሉ ካስረዳ በኋላ የማጥመቅ ሥራውን ቀጠለ፡፡ ከሁሉ በፊትም ነገስታቱ ተጠመቁ ኢዛና አብርሃ፣ ሳይዛናም አጽብሐ ተባሉ፡፡ ቀጥሎም ሰራዊቱና ህዝቡ ሁሉ ተጠመቁ፡፡ ሥራተ ቁርባንም ድንኳን አስተክለው ተፈጸመላቸው፡፡

አብርሃ ወአጽብሐ በአክሱምና በ አካባቢው ህዝቡን አስተመረው ካጠመቁ በኋላ ጌታችን መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመላእክት ጋር ተገልጾ በተራራው ላይ / አሁን መከየደ እግዚኦ ተብሎ በሚጠራው ቦታ/ ቆሞ ታያቸውና በዚህ ቦታ ቤተክርስትያን ስሩልኝ አላቸው፡፡ ነገር ግን ቦታው የውኃ መከማቻ ባህር ስለነበር ከየት እንስራ አሉት፡፡ ጌታችንም ከገነት ትንሽ አፈረ አምጥቶ በውኃው ላይ በተነ፡፡ ያችም ባህር እንደ በርሃ ደረቅ ሆነች ጌታችንም ቤተክርስትያኔን ከዚህ ቦታ ሥሩ ብሎ አዝዟቸው ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡

ነገሥታቱም የቤተ መቅደስ ሥራ ወደሚችሉት ወደ ጢሮስ ንጉሥ የኪራንም ልጆች እንዲልክላቸውና እንዲያንጹላቸው ከብዙ ወርቅና ገንዘብ ጭምር ደብዳቤ ላኩ፡፡ በዛም ወራት የግሪክ ጥበበኞችና የጢሮስ ብልሃተኞች መጡ፡፡ የጠቢባኑም ቁጥር ሃያ አራት ነበሩ፡፡ እነሱም 12 የግሪክ/ፅርዕ/ ጥበበኞች፣ 12 የኪራም የልጅ ልጆች የሆኑ የጢሮስ ብልሃተኞች ነበሩ፡፡ ጠቢባኑም በእየምድባቸው በአንዲት ቦታ የ12 ቤተ መቅደስ መሠረት ጀመሩ፡፡ መሠረቱን ሲያከናውኑ ጌታችን ለነገስታቱ ታያቸው እነሱም ባዩት ጊዜ ሰገዱለት፡፡ ይቺ የምታሰሯት ቤተ መቅደስ እንደ ኢየሩስዓለም ያለች ሰማያዊ ናት ብሎ ባርኳቸው ተሠወረ፡፡

ይህ ቤተ መቅደስ ስራው ሁሉ በግሩም ሁኔታ ተከናውኖ ለ600 ዓመታት አገልግሎ ት ሲሰጥ ከቆየ በኋላ በ10ኛው መቶ ክፍለዘመን በአንበሳ ውድም ዘመነ መንግስት እርሱን ድል ነስታ 40 ዓመታት በነገሰችው በዮዲት ጉዲት ተቃጥሏል፡፡

አብርሃና አጽብሐ በመላው ሀገሪቱ እየተዘዋወሩ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ከመፈጸማቸው በተጨማሪ ለ154 አብያተ ክርስትያናትን ያሳነጹ ሲሆን ከእነዚህም 44ቱ አስደናቂ ናቸው፡፡ ባለ44 ምሰሶ ከፍልፍል ድንጋይ የተሰሩ ሲሆኑ ከነዚህም ውስጥ በገልአርታ የሚገኘው ሰው የማይከፍተው ሰው የማይዘጋው የቀመር አርባዕቱ እንስሳ በተክርስትያን ይገኝበታል፡፡

እነዚህ ጻድቃን ነገስታት ሀገሪቱን ተከፋፍለው በወሎ፣ በሽዋ የየካ ሚካኤል / አዲስ አበባ/ ፣ በከፋ የብሐ ጊዮርጊስን፣ በሰላሌ የዋሻ ሚካኤልን፣ በጎጃም የዲማ ጊዮርጊስን፣ በጎንደር ስማዳ የጃን ሚካኤል ቤተ ክርስትያንን አሳንጸው እየተዘዋወሩ እያገለገሉ ነበርና ታላቁ አብርሃ በ374 ዓ ም ጥቅምት 4 ቀን እለተ እሁድ ዐረፈና ተቀበረ፡፡ ወንድሙ አጽብሐ ደግሞ ጥቅምት 4 ቀን 379 ዓ ም ዐረፈ፡፡ ሁለቱም ነገስታት ልደታቸውም ሆነ ሞታቸው አንድ ቀን ነበር፡፡ አመተ ምህረቱ ግን ይለያያል፡፡ በሞቱም ጊዜ በመቃብራቸው ላይ ቀስተ ደመና ተተክሎ ታይቷል፡፡ እነዚህ ነገስታት ለሀገራችን ብርሃንን የገለጹ ባለውሌታዎቻችን ሲሆኑ የኦሪቱን ስርዓት በሐዲስ ስርዓት የለወጡ ቅዱሳን ናቸው፡፡

ጌታችንም ለእነዚህ ቅዱሳን ነገስታት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ ዝክራችሁን የዘከረ፣ ስማችሁን የጠራ እምርላችኋለው፡፡ በስማችሁ ቀዝቃዛ ውኃ ያጠጣ እኔ የህይወት ውኃ አጠጣዋለሁ፡፡ በስማችሁ ለተራበ እንጀራ ያበላ እኔ የህይወት እንጀራ አበላዋለሁ፡፡ በስማችሁ ቤተ ክርስትያን ያሳነጸ በመግስተ ሰማያት ቤት እሰጠዋለሁ፡፡ በስማችሁ ማህሌት የቆመ የመላእክትን ማህሌት አሰማዋለሁ በማለት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል፡፡

የአብርሃ ወአጽብሐ ረድኤታቸው፣ በረከታቸውና አማላጅነታቸው አይለየን።አሜን!!!