አዳም እና ሔዋን (ለልጆች) (ዘፍ 1፣2፣3)

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች?

በአለፈው በቀረበው ክፍለ ትምህርት እግዚአብሔር ለፈጠራቸው ፍጥረታት እንዳነበባችሁና እንደተረዳችሁ ተስፋ እናደርጋለን። በዚህ ጽሑፍ ደግሞ እግዚአብሔር በስድስተኛው ቀን ለፈጠራቸው አዳም እና ሔዋን እንደሚከተለው ቀርቦላችኋል።

እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ኑሮ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ከፈጠረለት በኋላ በስድስተኛው ቀን ዐርብ የመጀመርያውን ሰው አዳምን ፈጠረ። እግዚአብሔር ሲፈጥረውም በእራሱ መልክ እና ምሳሌ ፈጠረው፤ በምድር ላይ ለሚኖሩ ፍጥረታት ሁሉ ገዢ አደረገው። እግዚአብሔርምአዳም ብቻውን በመሆኑ ከጎኑ አጥንትን ወስዶ ሔዋንን ፈጠራት። በተፈጠሩበት ምድር አዳም አርባ ቀን ፣ ሔዋን ደግሞ ሰማንያ ቀን ከቆዩ በኋላ ወደ ኤዶም ገነት አስገባቸው። ይህን መሠረት አድርጋ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ወንዶች በተወለዱ በአርባ ቀናቸው ፣ ሴቶች በተወለዱ በሰማንያ ቀናቸው ተጠምቀው የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ታደርጋለች።

እግዚአብሔርም በገነት መካከል ያሉትን ፍሬዎች እንዲበሉ ፈቀደላቸው። ነገር ግን ዕፀ በለስ ተብላ የምትጠራውን ፍሬ እንዳይበሉ አዘዛቸው። ከዚህች ፍሬ ብትበሉ የሞት ሞትን ትሞታላችሁ ብሎ አስጠነቀቃቸው። አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ አክብረው ለ7 ዓመት ያህል ገነት ኖሩ። ሰይጣን ዲያብሎስ በእባብ በኩል የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ እንዲያፈርሱ ፈተና አመጣባቸው። ዲያብሎስ በእባብ አድሮ ወደ ሔዋን ቀርቦ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? አላት። እሷም ዕፀ በለስን ትበሉ ትሞታላችሁ እንደተባሉ ነገረችው። እባብም ለሔዋን ሞትን አትሞቱም ከእርስዋ በበላችሁ ጊዜ እንደ እግዚአብሔር ትሆናላችሁ ብሎ በሀሰት አታለላት።

ሔዋንም የእባብን ሽንገላ ሰምታ እውነት እንደ እግዚአብሔር የሚሆኑ መስሏት ለመብላት ወሰነች። ከፍሬውም ወሰደችና ከባልዋ ከአዳም ጋር አብረው በሉ። በበሉም ጊዜ ጸጋቸው ተገፈፈ፣ የክብር ልብሳቸውን አጡ፣ እነርሱም ዕራቁታቸውን እንደ ሆኑ አወቁ፤የበለስን ቅጠል ሰፍተው ለበሱ። ልጆች የእግዚአብሔርን ሕግና ትእዛዝ ስናፈርስ ጸጋችን ይገፈፋል፤ እግዚአብሔርም ያዝንብናል። አዳምና ሔዋንም የእግዚአብሔርን ድምፅ ሲሰሙ ፈርተው በገነት ዛፎች መካከል ተሸሸጉ። እግዚአብሔርም አዳምን ጠርቶ፦ ወዴት ነህ? አለው። እርሱም በገነት ድምፅህን ሰማሁ ዕራቁቴንም ስለ ሆንሁ ፈራሁ፥ ተደበቅሁም አለው። እግዚአብሔርም ዕራቁትህን እንደ ሆንህ ማን ነገረህ? ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍ በላህን? ሲለው አዳምም ከእኔ ጋር እንድትሆን የሰጠኸኝ ሴት እርስዋ ከዛፉ ሰጠችኝና በላሁ አለው። እግዚአብሔርም ሁላቸውንም በጥፋታቸው ምክንያት ረገማቸው። እግዚአብሔርም እባቡን ይህን ስላደረግህ ከእንስሳት ፣ ከምድር አራዊትም ሁሉ ተለይተህ አንተ የተረገምህ ትሆናለህ በሆድህም ትሄዳለህ፥ አፈርንም በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ትበላለህ ብሎ ረገመው። ሔዋንንም በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ በጭንቅ ትወልጃለሽ ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፥ እርሱም ገዥሽ ይሆናል ብሎ ረገማት። አዳምንም እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍ በልተሃልና ወደ መጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም ትመለሳለህና ብሎ ረገመው። እግዚአብሔርም በበደላቸው ምክንያት ከረገማቸው በኋላ ከ ገነት አስወጣቸው፥ አዳምም የተገኘባትን መሬት አርሶ መብላት ጀመረ።

አዳምና ሔዋን ከገነት ከወጡ በኋላ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ፣ ገነትን ያህል ቦታ በማጣታቸው በሰሩት ኃጢአት ተጸጽተው እግዚአብሔር እንዲምራቸው ሱባኤ (ጸሎት) ያዙ። እግዚአብሔር ጸሎታቸውን እና ልመናቸውን ተመልክቶ እንደሚምራቸው ቃል ኪዳን ገባላቸው። ቃል ኪዳኑም “ከልጅ ልጅህ ተወልጄ ከ5500 ዘመን በኋላ አድንሃለሁ” የሚለው ነበር።እግዚአብሔርም እንደተናገረ አልቀረም ከእናታችን ድንግል ማርያም ተወልዶ አዳምን ከእነ ልጅ ልጆቹ አዳነን።

በአጠቃላይ ልጆች ከአዳምና ሔዋን ታሪክ የምንማረው አታድርጉ የተባልነውን ነገር ማድረግ እንደለለብን፤እሱን አልፈን ግን ብናደርግ እስከ ሞት ድረስ መከራ ሊያመጣብን እንደሚችል መረዳት አለብን። እግዚአብሔር ደግሞ የይቅርታና የምሕረት አምላክ እንደሆነ እንረዳለን። ስለዚህ ለእግዚአብሔር ሕግና ትእዛዝ መታዘዝ ይኖርብናል።

ልጆች ከላይ በአነበባችሁት ታሪክ መሠረት ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ስጡ

. እግዚአብሔር አዳምንና ሔዋንን ምን ዕለት ፈጠራቸው ?

. አዳምና ሔዋን ወደ ገነት የገቡት በተፈጠሩ በስንተኛው ቀን ነው?

. አዳምና ሔዋንን እግዚአብሔር አምላካችን በገነት ምን እንዳይበሉ አዘዛቸው?

. አዳምና ሔዋንን ያሳታቸው ማን ነው?

. አዳምና ሔዋን በበደላቸው ምክንያት ምን ተፈረደባቸው?

. እግዚአብሔር ለአዳም የገባለት ቃል ኪዳን ምንድን ነው?