ግቢ ጉባኤ

ቨርችዋል ግቢ ጉባኤ በአውሮፖ በዚህ ይመዝገቡ:-
https://docs.google.com/forms/u/1/d/1kwZcBbi7PrnK1m-Iz6E8Njpdmy-sMURA8wf2pDWrR_k/viewform?edit_requested=true&pli=1 

የዐቢይ ጾም ሳምንታት (ለሕፃናት) – ክፍል አራት

፮. ገብር ኄር

በልደት አስፋው

ሚያዝያ ፮ ቀን ፳፻፲፫ዓ.ም

ሰላም ናችሁ ልጆች? ባለፈው ዝግጅት ስለ ደብረ ዘይት ተምረናል፡፡ ዛሬ ደግሞ ስለ ‹ገብር ኄር› እንማራለን፡፡ ስድስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት (እሑድ) ‹ገብር ኄር› ይባላል፡፡ ትርጕሙ ‹ታማኝ፣ በጎ፣ ደግ አገልጋይ› ማለት ነው፡፡ ልጆች! አንድ ባለጠጋ አገልጋዮቹ ነግደው እንዲያተርፉበት ለአንዱ አምስት፤ ለሁለተኛው ሁለት፤ ለሦስተኛው አንድ መክሊት ሰጣቸው፡፡ ልጆች! ‹መክሊት› የገንዘብ ስም ነው፡፡

ከዚያ በኋላ አምስት እና ሁለት መክሊት የተቀበሉት ሁለቱ አገልጋዮች በተሰጣቸው መክሊት ነግደው እጥፍ አትርፈው ለባለ ጌታው አስረከቡ፡፡ ስለዚህም ገብር ኄር (ታማኝ አገልጋይ) ተብለው ተመሰገኑ፤ ልዩ ክብርን አገኙ፡፡ አንድ መክሊት የተቀበለው አገልጋይ ግን የተቀበለውን መክሊት ቀብሮ ካቆየ በኋላ ምንም ሳያተርፍበት ለጌታው አስረከበ፡፡ ይህ አገልጋይ ‹ገብር ሐካይ› ይባላል፡፡ ‹ሰነፍ አገልጋይ› ማለት ነው፡፡ በመክሊቱ ባለማትረፉ የተነሣ ቅጣት ተፈርዶበታል፡፡

የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፳፭ ቍጥር ፲፬-፵፮ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ብታነቡት ሙሉ ታሪኩን ታገኙታላችሁ፡፡ ልጆች! ስድስተኛው የዐቢይ ጾም እሑድ ስለ እነዚህ አገልጋዮች እና ስለ መንፈሳዊ አገልግሎት ጥቅም ትምህርት የሚቀርብት ሳምንት በመኾኑ ‹ገብር ኄር› ተብሏል፡፡ እናንተም በተሰጣችሁ ጸጋ ብዙ ምግባር መሥራት አለባችሁ እሺ? መልካም ልጆች! ለዛሬው በዚህ ይበቃናል፡፡ በቀጣይ ደግሞ ስለ ኒቆዲሞስ እንማማራለን፡፡ ሰላመ እግዚአብሔር ከዅላችን ጋር ይኹን!

የዐቢይ ጾም ሳምንታት (ለሕፃናት) – ክፍል ሁለት

በልደት አስፋው

መጋቢት ፲፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ደኅና ናችሁ? እግዚአብሔር ይመስገን!፡፡ ልጆች! በልዩ ልዩ ምክንያት አልችል ብለን ዘግይተናል፡፡ በቅድሚያ በገባነው ቃል መሠረት ወቅቱን ጠብቀን ትምህርቱን ባለማቅረባችን እናንተን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡

ልጆች! የካቲት ፲፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ባቀረብንላችሁ ትምህርት ከሰባቱ አጽዋማት መካከል ዐቢይ ጾም አንዱ እንደኾነ፣ ዐቢይ ጾም ማለት ታላቅ ጾም ማለት እንደኾነ፣ ጾሙ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ጾም በመኾኑ ታላቅ እንደተባለ፣ ዕድሜአቸው ሰባት ዓመት ከኾናቸው ሕፃናት ጀምሮ ዅሉም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ዐቢይ ጾምን እና ሌሎችንም አጽዋማት መጾም እንደሚገባቸው፣ እንደዚሁም ስምንቱ የዐቢይ ጾም ሳምንታት (እሑዶች) ስማቸው ማን ማን እንደሚባል ነግረናችሁ ነበር፡፡

ልጆች! ሰባቱ አጽዋማት ማን ማን እንደሚባሉም ጠይቀናችሁ ነበር አይደል? መልሱንስ ጠይቃችሁ ተረዳችሁ? በጣም ጥሩ ልጆች! መልሱን እናስታውሳችሁ፤ ሰባቱ አጽዋማት የሚባሉት፡-

፩. ጾመ ነቢያት

፪. ጾመ ገሃድ (ጋድ)

፫. ጾመ ነነዌ

፬. ዐቢይ ጾም

፭. ጾመ ድኅነት (ረቡዕ እና ዓርብ)

፮. ጾመ ሐዋርያት

፯. ጾመ ፍልሰታ (የእመቤታችን ጾም) ናቸው፡፡

በአሁኑ ሰዓት ዐቢይ ጾምን እየጾምን ነው፡፡ የምንገኘውም ሦስተኛው ሳምንት ላይ ሲኾን ስሙም ‹‹ምኵራብ›› ይባላል፡፡ የሚቀጥለውና አራተኛው ሳምንት ደግሞ ‹‹መጻጕዕ›› ተብሎ ይጠራል፡፡

ልጆች! በዛሬው ዝግጅታችን ከመጀመሪያው እሑድ እስከ ሦስተኛው እሑድ (ከዘወረደ ጀምሮ እስከ ምኵራብ) ድረስ የሚገኙትን የዐቢይ ጾም ሳምንታት የሚመለከት ትምህርት ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ ትምህርቱን እንድከታተሉት በአክብሮት ጋብዘናችኋል!

፩. ዘወረደ

ልጆች! ከዐቢይ ጾም ሳምንታት መካከል የመጀመሪያው ሳምንት ‹‹ዘወረደ›› ይባላል፡፡ ዘወረደ ማለት ከላይ የመጣ፣ የወረደ ማለት ነው፡፡ ይህም አምላካችን ዓለምን ለማዳን ሲል ሥጋ መልበሱን (ሰው መኾኑን) ያመለክታል፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ ወርዶ፣ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቆ፣ ወንጌልን ለዓለም ካስተማረ በኋላ በፈቃዱ መከራ ተቀብሎ፣ በመስቀል ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ ከሙታን ተነሥቶ ዓለምን አድኗል፡፡ ልጆች! የመጀመሪያው ሳምንት የአምላካችን የማዳን ሥራ በስፋት የሚነገርበት ወቅት በመኾኑ ‹‹ዘወረደ›› ተብሎ ተሰይሟል፡፡

፪. ቅድስት

ሁለተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹‹ቅድስት›› ይባላል፡፡ ቅድስት ማለት የተለየች፣ የተመረጠች፣ የከበረች ማለት ነው፡፡ ልጆች! ለምን የተለየች፣ የተመረጠች፣ የከበረች እንደተባለች ታውቃላችሁ? ቅዱስ አምላካችን እግዚአብሔር ዓለምን (ሰውን) ለመቀደስ ሲል ወደ ምድር መምጣቱንና ዐቢይ ጾምን መጾሙን ለማስረዳት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሰንበትን ክብር ለማስገንዘብ ነው፡፡ ሰንበት ቅድስት፣ የተለየች፣ የተመረጠች፣ የከበረች ዕለት ናት፡፡ ስለዚህም ልጆች! ሁለተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹‹ቅድስት›› ተብሎ ይጠራል፡፡

፫. ምኵራብ

ልጆች! ሦስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ደግሞ ‹‹ምኵራብ›› ይባላል፡፡ ምኵራብ ማለት አዳራሽ ማለት ነው፡፡ ምኵራብ ድሮ የነበሩ የእግዚአብሔር ሰዎች መንፈሳዊ ትምህርት ይማሩበት የነበረ  ሥፍራ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ይህንን የጸሎት ሥፍራ ሰዎች የንግድ ቦታ አደረጉት፡፡ ይህንን ዓለማዊ ተግባር ሲፈጽሙ የነበሩትን ዅሉ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል፡፡ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት›› ብሎ ከምኵራብ አስወጣቸው፡፡ ከዚያም ቃለ እግዚአብሔር አስተማራቸው፡፡ ልጆች! የእግዚአብሔር ቤት የጸሎት ቤት እንጂ የንግድ መነገጃ ሥፍራ አለመኾኑን ከዚህ ታሪክ እንማራለን፡፡

ለዛሬው በዚህ ይቆየን፡፡ ቀጣዩን ትምህርት ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በሚቀጥለው ዝግጅት ይዘንላችሁ እንቀርባለን፡፡ እስከዚያው ድረስ ሰላመ እግዚአብሔር ከዅላችን ጋር ይኹን!

የዘመናት ለውጥ ለክርስቲያኖች የደወል ድምፅ ነው።

ጌታቸው በቀለ

ዘመን

ዘመን የሚለው ቃል አንድ ዓመትን ያመለክታል። በብዙ ሲሆን ዘመናት ይባላል። ይህም ከአንድ ዓመት በላይ የሆነ ጊዜን ለማሳየት ነው። በዘመን ውስጥ ዕለታት እና ወራት አሉ። አንድ ዓመት ማለት መሬት አንድ ጊዜ በፀሐይ ዙሪያ ለመዞር የሚፈጅባት ጊዜ ነው፡፡ ይህም 365 ከ1/4 (ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ቀን ከሩብ) ዕለታት ይፈጃል፡፡ አሁን ባለንበት የዓለማችን ግንዛቤ ምድር በራሷ ዛቢያ እየተሽከረከረች በፀሐይ ዙሪያም ትዞራለች፡፡ ምድር በፀሐይ ዙሪያ የምትዞረው ወደ ጎን 23 ተኩል ዲግሪ ያህል አጋድላ ነው፡፡ የቀን እና የሌሊት ርዝመት መለያየትም የሚከሰተው በዚህ ማጋደል ምክንያት ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ «ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ፣ ለዕለታት፣ ለዘመናትና፣ ለዓመታት ምልክት ይሆኑ ዘንድ» /ዘፍ.1. 14- 15/ ይላል።ይህም የቀንና የሌሊት መፈራረቅ የዕለታትና፣ የወራት፣ የዘመናትም መገኛ መስፈሪያዎች መሆናቸውን ያመለክታል።

አንድ ዕለት ማለት አንድ ቀንን (መዐልት) /የብርሃን ክፍለ ጊዜን/ እና አንድ ሌሊትን /የጨለማ ክፍለ ጊዜን/ ያካተተ፣ ፀሐይ ከወጣች በኋላ ተመልሳ እስከምትወጣ ድረስ ያለውን ጊዜ የያዘ ነው፡፡ እንደ ዓለም ጠበብት አገላለጽ አንድ ዕለት ማለት ምድር በራሷ ዛቢያ አንድ ጊዜ የምትሽከረከርበት ነው፡፡ ወር ወይንም ወርኅ ማለት በግእዝ ጨረቃ ማለት ነው፡፡ ሙሉ ጨረቃ ከወጣች በኋላ ድጋሜ ሙሉ ሆና እስከምትወጣ ድረስ ያለው ጊዜ አንድ ወርኅ ይባላል፡፡ ይህም ጨረቃ፣ መሬትን አንድ ጊዜ ዙራ ለመጨረስ የሚፈጅባት ጊዜ ነው፡፡ አንድ ወር ሃያ ዘጠኝ ተኩል ዕለታት ነው፡፡

የዘመን መለወጫ ዕለት ስያሜዎች

1.    ዱስ ዮሐንስ

የኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ ዕለት ስሙ ቅዱስ ዮሐንስ ይባላል። ቅዱስ ዮሐንስ የሚባልበትም ሁለት ምክንያት አለው። አንዱ፤ መጥምቁ ዮሐንስ በሄሮድስ አንቲጳስ ጊዜ ከጳጉሜን ፩ ቀን ጀምሮ ታስሮ ሰንብቶ በመስከረም ፩ ቀን ሞቱ ስለተወሰነበትና በመስከረም ፪ ቀን አንገቱ በሰይፍ ተቆርጦ በሰማዕትነት ስላረፈ ነው። በተጨማሪም ቅዱስ ዮሐንስ ለኦሪትና ለወንጌል መገናኛ መምህር ነበርና ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በዚህ ዕለት ላለፈው ዘመን መሸኛ፥ ለሚመጣው ዘመን መቀበያ እንዲሆን ብለው በመስከረም ፩ ቀን በዓሉ እንዲከበር ስላደረጉ በሱ ስም ቅዱስ ዮሐንስ እየተባለ ይጠራል። ሁለተኛው ምክንያት በአቆጣጠርም ተራ ወደ ኋላ ተመልሶ ቢቆጠር ዓለም የተፈጠረበት ዘመን ከአራቱ ወንጌላውያን አንዱ በሆነው በዘመነ ዮሐንስ የሚገጥም ሆኖ ስለሚገኝ ቅዱስ ዮሐንስ ተብሎ ይጠራል።

2.    እንቍጣጣሽ

ከጥፋት ውኃ በኋላ የነበሩ ኖኅና ልጆቹ ሰማዩ በደመና በመክበዱ ምክንያት “ማየ አይኅ እንደገና ይመጣ ይሆን?” እያሉ ሲደነግጡ ከርመው በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ሙሉ የፀሓይ ብርሃን ተመለከቱ። ምድር በአበባ አሸብርቃ የተገለጠችበትና በዚህም የእግዚአብሔርን ቸርነት፥ የቃል ኪዳኑን መጽናትም የተረዱበት ጊዜ ነው። ይህንንም ዕለት ቀድሞ ከአባቶቻቸው እንደ ወረሱት ጥንተ ብርሃን፥ ጥንተ ዓመት፥ ጥንተ ዕለት ብለው በዓል አድርገው አክብረውታል። ሲያከብሩትም እንግጫ ነቅለው፣ አበባ ጐንጕነው መጀመሪያ መሥዋዕት ይሠዉበት ከነበረው ቦታ ሄደው ለእግዚአብሔር አምኃ አቅርበዋል። ከዚያ በኋላ እርስ በራሳቸው የአበባ ስጦታ በመለዋወጥ አክብረውታል። ሲያከብሩትም ዕንቍጣጣሽ በሚል ቃል የመልካም ሞኞታቸውን ይገላለጡበት ነበር።

የታሪክ ጸሐፊዎች ‘ዕንቍጣጣሽ’ የሚለውን ቃል በልዩ ልዩ መልክ ተርጕመውት እናያለን። አንዳንዶች ንጉሡ ሰሎሞን ለሳባ ንግሥት የዕንቍ ቀለበት ሰጥቷት ነበርና ‹ዕንቍ ለጣትሽ› ማለት ነው ብለው ጽፈዋል። ሌሎች ደግሞ ‘እንቍጣጣሽ’ ማለት ‹ተንቈጠቈጠ፥ አንቈጠቈጠ› ከሚለው ቃል ተወስዶ ምድር በአበባ አጌጠች፥ ሰማይም በከዋክብት አሸበረቀ እንደ ማለት ሰማይን በከዋክብት ያስጌጠ አምላክ ምድርንም በአበቦች አጎናጸፋት ለማለት የተሰጠ ቃል ነው ይላሉ።

3.    መስከረም

ኖኅ በመርከብ ውስጥ በነበረ ጊዜ በዕብራውያን አቆጣጠር ስድስተኛ በሆነው በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ መርከቢቱ አራራት ከሚባለው ተራራ ላይ ዐርፋለች። በግእዝ ቋንቋ መርከብ ‹መስቀር› ይባላል። ከዘመን ብዛት በኋላ «ቀ» ወደ «ከ» ተለውጦ ‘መስከረም’ ተባለ እንጂ መስቀርም ምድር አገኘች፥ መርከብም ምድር ነካች ለማለት የተሰጠ የነካችበት ወሩ ስያሜ ነው።

4.    ርእሰ ዐውደ ዓመት

ርእሰ ዐውደ ዓመት የምንለው ‹ዐውድ› ማለት በግእዙ ቋንቋ ‹ዙሪያ፥ ክብ› የሆነ ነገር ማለት ነው። የዓመት ጠቅላላ መሠረታውያን ቀኖች የሚባሉት ሦስት መቶ ስድሳ አራት ቀኖች ናቸው። እነዚህም በኀምሳ ሁለት ሱባዔ ተከፍለው ለእያንዳንዱ ቀን በዓመት ውስጥ ለሰባቱ ዕለታት ኀምሳ ሁለት፣ ኀምሳ ሁለት ቀን ይደርሳቸዋል። ከነዚህ ቀኖች የተሳሳበ የሴኮንድ፥ የደቂቃ፥ የሰዓት ዕላፊ ተጠራቅሞ ሦስት መቶ ስድሳ ዐምስተኛዋን የዘመን ማገጣጠሚያ ቀን ያስገኛል። ይህቺ ቀን እንግዲህ ‹ዙሪያ፥ ክብ፣ መግጠሚያ› ናት ማለት ነው። በዚህች ቀን አማካይነት ወደ ዐዲሱ ዘመን መጀመሪያ እንተላለፋለን። ይህቺ ቀን ዕለተ ዐዕዋዲት፥ ዕለተ ምርያ፣ የመዘዋወሪያ ቀን፣ ወይም የመጨረሻ ቀን ተብላ ትጠራለች።

የዘመን መቀየር ክርስቲያኖችን የደወል ድምፅ ያህል ሊያነቃ ይገባል

ዘመን ሲቀየር ክርስቲያኖች ሊያስቡት የሚገባ ነገር አለ። እርሱም፦ ያለፈውን ዘመን እንዴት እንዳሳለፉት እና መጪውን እንዴት ሊያሳልፉ እንዳቀዱ ነው። ምክንያቱም የዘመን መቀየር በራሱ የእግዚአብሔር የደውል ድምፅ ነው። እግዚአብሔር ዓመቱን በወቅት ለይቶ አየሩን በፍቃዱ እያቀያየረ ያኖረናል። አንድም የእግዚአብሔር ሕልውና በፍጥረቱ ይገለጣልና በሠራው ሥራ እየተደመምን እንድናመሰግነው ሲሆን፣ በሌላ በኩል ዘመናችንን እያየን፣ ወደ ራሳችን እየተመለከትን ለንስሐ ሕይወት እንድንበቃ የተሰጠን ረቂቅ ደወል ነው። ቅዱስ ጴጥሮስየአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም፣ በስካርም፣ በዘፈንም፣ ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል’’ (1ኛ ጴጥ. 4፣3) እንዳለ፣ ያለፈው ዘመን የመንፈሳዊ ሕይወት አካሄድ እግዚአብሔርን ያስደሰተ ነው? ወይንስ ለሥጋችን ድሎት ብቻ የኖርንበት? ሌሎችን ወደ መንፈሳዊ ሕይወት ለመምጣት የጣርንበት ወይንስ ለሌሎች መሰናክል የሆንበት? ነውን እያልን የራሳችንን ያለፈ ዘመን አካሄድ የምንመረምርበት የደወል ድምፅ ነው።

በአጠቃላይ የዘመን መቀየር ክርስቲያኖችን የደወል ድምፅ ያህል ሲያነቃ ባለፈው ሕይወት ላይ ብቻ መሠረት ያደረገ ሊሆን አይገባም። ይልቁንም ደወሉ መጪውን ዘመን እንዴት ለመኖር እንዳሰብን ሊጠይቀን ይገባልል። ስላለፈው፣ ከመንፈሳዊ ሕይወት ለራቀ አኗኗራችን የምንጠየቀው በተሰጠን አዲስ ዘመን ማስተካከል ካልቻልን ነው። መጪው ዘመን በእጃችን ያለ፣ እግዚአብሔር እንደፈቃዱ የሰጠን፣ ዋጋ ያልከፈልንበት ስጦታ ነው። ይህም ከራሳችን አልፈን ሌሎችን ለመመለስ እንድንተጋ የተሰጠን የእግዚአብሔር ችሮታ ነው። በዮሐንስ ራዕይ 22፥15 ላይ እንደተፃፈው “አስማተኞች ሴሰኛዎችም ነፍሰ ገዳዮችም ጣዖትንም የሚያመልኩ፣ ውሸትንም የሚወዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ አሉ።” እንዳንባል ባለፈው ዘመን የነበሩንን፣ ከእግዚአብሔር ያጣሉንን የኃጢአት ተግባራት ሁሉ ልናስወግድበት እና የንስሓ ጊዜ አድርገን አዲሱን ዘመን ልንጠቀምበት ይገባናል።

የዘመኑ መለወጥ ደወል ሲሆን ደወሉን ሰምቶ ከክፉ መንገድ የሚመለስ በረከትን ያገኛል። በዘመኑ መቀየር ውስጥ የደወል ድምፁን እንዳልሰማ የሚያልፍ ደግሞ ከበረከት ይልቅ መርገምን ይቀበላል፤ ከጽድቅ ይልቅ ኲነኔ ይጠብቀዋል። በማቴዎስ ወንጌል 7፥24 ላይ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል። ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ፣ ነፋስም ነፈሰ፣ ያንንም ቤት ገፋው፣ በዓለት ላይም ስለተመሠረተ አልወደቀም። ይህንን ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል። ዝናብም ወረደ፣ ጎርፍም መጣ፣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት መታው፥ ወደቀም፥ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ።’’ ብሎ እንዳስተማረን። ስለዚህ ሁላችንም በዘመን መቀየር ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔር የደወል ድምፅ አስተውለን የበለጠ ቤተ ክርስቲያናችንን ለማገልገል የምንተጋበት፣ እና ለሰማያዊት ኢየሩሳሌም የበቃን የሚያደርገንን ሥራ የምናከናወንበት ዘመን ያድርግልን።  

ወስብሐት ለእግዚአብሔር።