የልጆች አስተዳደግ በውጭው ዓለም*

በላቸው ጨከነ (ዶ/ር)

የካቲት 9 ቀን 2007 ዓ.ም.

ልጆች ብዙ ተባዙ” ሚለው አምላካዊ ቃል መሠረት ከእግዚአብሔር የሚገኘ በረከቶች ናቸው ቅዱስ ዳዊት ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናችው(መዝ ፻፳፮) እንዳለ። ቅዱሳን ጻድቃን፣ ጳጳሳት ካህናት፣ ነገሥታት እና መሣፍንት የሚገኙት ከዚሁ አምላካዊ በረከት ነው። በአለንበት ዘመን የአኗኗር ዘይቤ መቀየር ፣ የኑሮ ጫና እና የዓለም መቀራረብ የልጆችን አስተዳደግ ለሁሉም ወላጆች እና ለቅድስት ቤተክርስቲያን ፈታኝ አድርገውታል። በተለይ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖሩ ወላጆች ለሚኖሩበት ሀገር ባህል እና ሕግ እንግዳ ስለሚሆኑ ከቤተ ዘመድ ስለሚርቁ ፣ የስራ ጫና እና የጊዜ እጥረት ስለሚያጋጥማቸው የዓለም ነጋዴዎች ልጆችን ከሃይማኖትና ከሥነ ምግባር የሚያስወጡ ተለዋዋጭ ሸቀጦችን ስለሚያጐርፉና እለት እለት ለመሳለም የሚሿት ቅድስት ቤተክርስቲያን በቅርባቸው እንደልብ ስለማትገኝ የልጆችን አስተዳደግ የበለጠ ውስብስብ አድርጎታል። በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ዘመኑን ዋጅቶ ልጆችን በሀይማኖትና ግብረ ገብ ትምህርት ለማሳደግ ከወላጆች ብዙ ይጠበቃል።በዚህ ጽሑፍ የቀደሙ ወላጆችን የልጅ አስተዳደግ ከቅዱሳት መጻሕፍት ለአብነት አይተን በስደት ስንኖር ልጆቻንን እንዴት ማሳደግ እንዳለብን በሰፊው እንዳስሳለን።

በቅዱስ መጽሐፍ ብዙ እናቶች እና አባቶች ልጆቻቸውን በአግባቡ በማሳደግ በእግዚአብሔርም በሰውም ዘንድ ክብር አግኝተዋል።አባታችን አብርሃም ለልጆቹ እና በእርሱ ር ለሚተዳደሩት ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ እየፈጸመ የእግዚአብሔርን ሕግ እንዲያከብሩ በማዘዝ ሙሉ ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር እንዲሰጡ ያደረግ ነበር። በመሆኑም ይስሐቅ አባቱ አብርሃም በእግዚአብሔር ፊት ለሚያቀርበው መባዕ መሥዋዕት እስከመሆን ድረስ ታዘዘ (ዘፍ፳፪፲፪)በዚህም እግዚአብሔር አብርሃምን እንዲህ ብሎ ባረከው፦ “በራሴ ማልሁ ይላል፤ ይህን ነገር አድርገሃልና፥ አንድ ልጅህንም አልከለከልህምና በእውነት በረከትን እባርክሃለሁ፤ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ አበዛዋለሁ፤ ዘርህም የጠላቶችን ደጅ ይወርሳል፤ የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ፤ ቃሌን ሰምተሃልና(ዘፍ ፳፪) ልጅን በአግባቡ አሳድጎ ለሰውም ለእግዚአብሔርም ታዛዥ ማድረግ እንደዚህ በረከትን ያሰጣል።

የሙሴ እናት በስደት በነበረችበት ወቅት ለልጇ ለሙሴ የእግዚአብሔርን ፍቅር እንዲሁም እግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑ ወገኖቹ እስራኤላውያን የደረሰባቸውን ስደት፣ መከራ እና ስቃይ ከሕጻንነቱ ጀምሮ ትነግረው ነበር። እርሱም ይህንን በልቡ አኑሮት በጎልማሳነቱ ዕድሜ የንጉሥ ልጅ ተብሎ የሚኖርበትን የፈርዖንን ቤተ መንግሥት ትቶ ሄደ። ከዚያም ስደተኛ ሆኖ የአማቱን የዮቶርን በጐች እየጠበቀ መኖር ጀመረ።እግዚአብሔርም ከበግ ጠባቂነት ጠርቶ የእግዚአብሔርን በጐች ወገኖቹን እስራኤልን እንዲጠብቅ (እንዲመራ) መረጠው (ዘጸ )እግዚአብሔርም ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት በሙሴ መሪነት አወጣ። ታዲያ ሙሴይህንን ያደረገው ከእናቱ ለእግዚአብሔር መታዘዝን እና የወገንን ፍቅር ሰለተማረ ነበር

በአንጻሩ ግን ሊቀ ካህናት ኤሊ የራሱ ሕይወት የማይነቀፍ ቢሆንም ልጆቹ አፍኒን እና ፊንሐስ በእግዚአብሔር ፊት የማይገባቸውን በማድረጋቸው እና እርሱም እነርሱን አጥብቆ በመገሠጽ ከክፉ መንገድ እንዲመለሱ ባለማድረጉ ምክንያት በበረከት ፋንታ ሁሉም መርገም ደርሰባቸው ። እስራኤላውያን በፍልስጤማውን ተሸነፉ አፍኒን እና ፊንሐስ በጦር ሜዳ ሞቱ ታቦተ ጽዮን ተማረከች፤ ኤሊም ይህን ሁሉ መከራ በሰማ ወቅት ደንግጦ ሞተ (ኛሳሙ )የአፊኒንና የፊንሐስ ችግራቸው በእግዚአብሔር ቤት እየኖሩ እግዚአሔርን አለመታዘዝ እና የእግዚአብሔርን ቤት መደፋፈር ነበር። ሊቀ ካህናት ኤሊም ምንም እንኳን እርሱ የእግዚአብሔር ሰው ቢሆንም ልጆቹን በአግባቡ ሠርቶ ቀጥቶ ባለማሳደጉና ከክፉ ሥራቸው እንዲመለሱ ባለማድረጉ ምክንያት ለዚያ ሁሉ ወድቀት ተዳረገ።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስልጆች ሆይ፥ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፤ይህ የሚገባ ነውና። መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር፤ እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት። እናንተም አባቶች ሆይ፥ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው (ኤፌ ) እንዳለ።ለእናት አባቱ የሚታዘእና እድሜው የሚረዝም ልጅ ለማሳደግ ልጆቻችንን በመንፈሳዊ ሕይወት በፈሪሐ እግዚአብሔር ማሳደግ ይገባናል ያኔም አምላኩን የሚፈራ፣ በሥነምግባር የታነጸ ፣ ማንነቱን የሚያውቅ፣ በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ጥበብ የተካነ ፣ ለወላጆችም ሆነ ለቅድስት ቤተክርስቲያን እና ለሀገር የሚበጅ ልጅ ማፍራት ይቻላል

ልጆቻችንን እንዴት እናሳድግ?

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን በመላው ዓለም ተሰራጭተው ይገኛሉ።ብዙ ኢትዮጵያዊም በሔደበት ሀገር ቤተሰብ መሥርቶ፣ ልጅ ወልዶ እየኖረ ይገኛል። በተለይ ባለ ሁለት አሥርት ዓመታት ቊጥሩ በፍጥነት ጨምሯል በመሆኑም በመላው ዓለም የተበተነው ሕዝበ ክርስቲያን ልጁን እንዴት ያሳድግ?” የሚለውን ለመረዳት የሚከተሉትን ነጥቦች እንመልከት።

. ወላጆች ለልጆች ምሳሌ በመሆን

የሥነ ምግባር መሠረትነት ያለው አርአያነትን ለልጆች የማመላከት ሚና በቀዳሚነት የወላጆች ድርሻ ነው ። ልጅ ቀጥተኛ እና የቅርብ ግንኙነት የሚኖረው ከወላጁ ጋር ስለሆነ ወላጅ ብዙ ሥራ ይጠበቅበታል። ለምሳሌም፦ ቃለ እግዚአብሔርን፣ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን እንዲሁም የሀገርን ታሪክና መልካም ባሕልን ማስተማር፣የልጅን አጠቃላይ እንቅስቃሴ መከታተል፣ ፍላጐትና ዝንባሌውን መገምገም፣ አስፈላጊ ነገሮችን በአግባቡ ማቅረብ፣ ለመንፈሣዊ አካላዊ እና ማኅበራዊ እድገቱ ሳይታክቱ መትጋት ከሁሉም በላይ ወላጅን ይመለከታል፤ቤተሰብ የመጀመሪያው /ቤት ነው እንደሚባለው

በዘመናችን ልጆችን በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እምነት ኮትኩቶ እና ጠብቆ ማሳደግ አንዱ መሥዋዕትነት ነው። ልጆች ሁልጊዜ የሚጥሩት ወላጆቻቸውን ለመምሰል ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ለመንፈስ ቅዱስ ልጁ ጢሞቴዎስ፡– “ይህን እዘዝና አስተምር። በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም በንጽህናም ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን እንጂ” እንዳለ(፩ጢሞ ፲፪) ስለዚህ ወላጆች በመጾም፣ በመጸለይ፣ በመመጽወት፣ በአለባባስ እና በአነጋገር ለልጆቻቸው በተግባር ምሳሌ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ፍቅርን እና እንግዳ መቀበልን መልመድ ማየት አለባቸው፤ ወላጆች ይቅርታን ማድረግን፣ ስህተትን ማመንን ማስተማር አለባቸው ። በተጨማሪም መዝሙርን መስማት እና መዘመር ፣ ቅዱሳት ሥዕላትን መሳለም እና በፊታቸውም መጸለይ እና ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ ልጆች ከወላጆች የሚማሯቸው ናቸው። በአጠቃላይ ልጆች ይህንን ካደረጉ የወላጆቻቸው ነፀብራቅ ይሆናሉ

. ልጆቻችንን ወደቤተክርስቲያን በማምጣት

ቤተክርስቲያን እምነቷ ሥርዓቷ በሚታይ ክንውን እና በሚሰማ ጸሎትና ዜማ የሚገለጽ በመሆኑ ልጆች ወደ ቤተክርስቲያን ሲመጡ በቃል ከሚማሩት ይልቅ በማየት የሚማሩት ይበልጣል።ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ በትምህርታቸው እንዲህ ይሉ ነበር ወደ ቤተክርስቲያን ስትመጡ ልጆቻችሁን ይዛችሁ አሳዩቸው ሥዕሉን ይሳሙ፤ ቅዳሴ ጠበል ይጠጡ። በእምነቱ አሻሿቸውም መሰቀል እንዲስሙ አስተምሯቸው። ዕጣኑን ያሽትቱ የሚታጠነውን፤ ሥጋውን ደሙን ይቀበሉ፤ ቃጭሉን ይስሙ፤ ደወሉ ሲደወል ያድምጡ፤ ቄሳቸው ማን እንደሆነ ቤተክርስቲያናቸውም ምን እንደሆነች በውስጧም ምን ምን እንደሚሰራ ያጥኑ ልጆች በቤተክርስቲያን ሲገኙ እና ሲካፈሉ ነገረ ክርስትናውን በድርጊት በማየት እና በመስማት በቀላሉ እንዲማሩ ይረዳቸዋል። ልጆች ወደ ቤተክርስቲያን ሲመጡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስሕጻናትን ተዉአቸው ወደ እኔም ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው መንግሥተ ሰማያት እንደእነርሱ ላሉ ናትና (ማቴ ፲፱፲፬) ብሎ ይቀበላቸዋል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሕጻናት ልዩ ትኩረት አለው። (ማቴ. ፳፩ ፲፮) ቅዱስ ጴጥሮስን “…..ግልገሎቼን አሰማራ …” ደግሞም ሁለተኛ “…..ጠቦቶቼን ጠብቅ …” ሦስተኛም ጊዜ “….በጎቼን አሰማራ (ዮሐ ፳፩፲፭) እንዳለው። ከሰማይ ጠባቂ መላእክትን ያዝላቸዋል።ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ መላእክቶቻቸው በሰማያት ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁና (ማቴ ፲፰ )

. ለልጆች ጊዜ በመስጠት

ልጆች በሕይወታቸው ከሚያስደስታቸው ነገሮች አንዱ ከወላጆጋር አብሮ ጊዜ ማሳለፍ ነው። በተለይ ሁለቱም ወላጆች አንድ ላይ ሆነው ሲጫወቱ ሲስቁ ሲመገቡ እና ሲያወሩ ማየት በጣም ይናፍቃቸዋል። በአንድ ላይ መጸለይ እና መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ፣ የቤተሰብ የጋራ ጸሎት የቤተሰብ አባላት በየተራ የሚያዘጋጁት ዝክር መጀመር፣ ማታ በጋራ ቅዱሳት መጽሕፍትን ማንበብ፣ መንፈሳዊ ፊልምችን አብሮ ማየት (የአባቶችን ታሪክ፣ የጌታችንን የማዳን ሥራ ባለው ጊዜ ውስጥ ማስተማር)። ይህም ልጆችን በእግዚአብሔር አምላካቸው መተማመንን ያሳድርባቸዋል ። ከቤት ውጪም ልጆችን የተለያዩ ቦታዎች ይዞ ወጥቶ ማሳለፍ ያስፈልጋል። መጫወቻ ቦታ፣ የእንሳት ግቢ ታሪካዊ ቦታ፣ ሙዚየም፣ ገበያ እና ወደ ቤተ ዘመድ ቤት አብሮ መሔድ ያስፈልጋል። ከዚህም ልጅ መልካም ጠባይንና ጠቃሚ ማኅበራዊ እሴቶችን ይቀስማል

. በወላጆች ፍቅር አርአያነት

ልጆች ወላጆቻቸው እርስ በእርሳቸው ሲዋደዱ እና ሲተሳሰቡ ሲያዩ የደስታ ስሜት ይታይባቸል። በወላጆች መካከል አለመግባባት ቢኖር እን ልጆች በሌሉበት መወያየት ያስፈልጋል። የመላው ቤተሰብ ጉዳይ ከሆነ ደግሞ በጋራ መወያየት ልጆች ለወደፊት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ጥሩ ተሞክሮ ይሆናቸዋል። ወላጆች በልጆቻቸው ፊት እውነተኛ መሆን ይገባቸዋል።አብርሃም ሚስቱን ሳራን እመቤቴ ይላት እንደነበር ሷም ጌታዬ ትለው እንደነበር ሁሉ ዛሬም ልጆች ከእናታቸው እና ከአባታቸው አንደበት እመቤቴ እና ጌታዬ በሚል የመከባበር ስሜት መተሳሰብን እያዩ ሊያድጉ ይገባቸዋል።

. ልጅን በመምከር እና በመገሰጽ

ልጅን መምከር የአዎንታዊ ጠባያት መገንቢያና ከመጥፎ ሥነ ምግባር ማረሚያ ነው። ቅዱስ ጳውሎስአባቶች ሆይ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና ተግሳፅ አሳድጓቸው እንጂ እንዲበሳጩ አታድርጓቸው” (ኤፌ ፮፥፲፭) ሲል ጠቢቡ ሰሎሞንልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው በሸመገለ ጊዜም ከእርሱ ፈቀቅ አይልም። (ምሳ ፳፪፥፮) ብሏል። ዳግመኛም ጠቢቡ ሰሎሞን አስቀድሞእግዚአብሔር የወደደውን ይገሥጻልና፥ አባት የሚወድደውን ልጁን እንደሚገሥጽ” (ምሳ ፫፥፲፩ ፲፪) እንዳለ ልጆችን ሀይማኖት እና ምግባር ይዘው እንዲያድጉ ልንገስጻቸው እና ልንቀጣቸው ይገባል። በመሐፈ ሲራክልጁን የሚወድ ሰው በእርሱ ደስ ይለው ዘንድ መቅጣትን ቸል አይልም። (ሲራክ ፴፥ ) ቅጣት ሲባል ብዙ ጊዜ ወደ አእምሯችን የሚመጣው አካላዊ ቅጣት ነው። ምዕቡ ዓለም የልጆች አያያዝ ሕግ አንጻር ግን ይህ አግባብ ላይሆን ይችላል። አካላዊ ቅጣት ሳንቀጣ ልጆቻችን ከሰሩት ጥፋት ታርመው መልካም ምግባር እንዲኖራቸው የሚከተሉትን እንዲያደርጉ ወላጆች ይመከራሉ፦

የ ሚወደውን ነገር የጊዜ ገደብ በማስቀመጥ መከልከል። ፊልም ማየት፣ መዝናኛ ሥፍራ መሔድ፣ ዘመድ መጠየቅ፣ . . . በጥፋቱ ምክንያት ከነዚህ ነገሮች ማዕቀብ መጣል። ጥፋቱ እቃ መስበር መጣል፣ ማበላሸት ቢሆን ከራሱ በጀት ወስዶ ያንን ያጠፋውን ዕቃ መተካት። ለምሣሌ ለመዝናኛ፣ለተጨማሪ ነገሮች ከተመደበው፣ በባንክ ከተቀመጠው ገንዘብ መጠቀም እና በሠራው ጥፋት ምክንያት ጥቅሙን ማጣቱን ማስገንዘብ እና እንዳይደግመው መምከር። ሁልጊዜ የሚደረግለትን ነገር በጥፋቱ ምክንያት መከልከል (አለማድረግ)

ያደጉ ሀገሮች ስለ ልጆች መብት እና አያያዝ የጠበቀ ሕግ አላቸው። ከዚህ ሕግ ውጪ የሆነ ወላጅ ባለበት ሀገር ሕግ መሠረት ይቀጣል። የልጅ አያያዝ፣ አመጋገብ እና ጤንነት ምን እንደሚመስል የጤና ተቋማት እና የማኅበረሰብ አገልግሎቶች ክትትል ያደርጋሉ። በዚህ ክትትል ወቅት ልጅ ያለ አግባብ ከተያዘ ወይም ከተገረፈ የሀገሩ መንግሥት ልጁን ከወላጅ በመለየት ለአሳዳጊ ይሰጣል። ይህም በቤተሰቡ ውስጥ ትልቅ ችግር ይፈጥራል። ስለዚህ ወላጅ በውጪ ሀገር ልጁን በሚያሳድግበት ወቅት አጠቃላይ ስለ ልጅ አያያዝ ያለውን ሕግ እና ልጁን ሲቀጣ ስለሚያደርገው ጥንቃቄ መረዳት ይገባዋል። ከሁሉ በላይ ግን ልጅ እና ወላጅ በቋንቋ ተግባብተው ልጅ ቤተሰቡን አክብሮና ፈርቶ እንዲያድግ ከተደረገ ይህ ችግር በቀላሉ ይፈታል።

. ቋንቋን እና ማንነት በማስተማር

ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖሩ ወላጆች አንዱ ችግር ከልጆቻቸው ጋር የሚግባቡበት ቋንቋ ነው ልጆች አብዛኛውን ጊዜ የሚናገሩት ቋንቋ የሚኖሩበትን ሀገር ነው። በወላጆች የሀገሩን ቋንቋ አለማወቅ ምክንያት ልጆች የሚሰማቸውን ነገር በግልጽ ለወላጆቻቸው በሚገባ ያስረዱ አይመስላቸውም ይህም በመካከላቸው ክፍተት እንዲፈጠርና ልጆችም ራሳቸውን ለወላጆች ከመግለጽ እንዲቆጠቡ ያደርጋቸዋል ስለዚህም በራሳቸው መኖር ይጀምራሉ። ከዚህም በላይ ወላጆች ቤተክርስቲያናቸውን እና ማንነታቸውን ለልጆቻቸው ለማስረዳት ያዳግታቸዋል። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ወላጆች ልጆቻቸው የእነርሱን ቋንቋ እንዲናገሩ ማድረግ ከምንም በላይ አማራጭ የሌለው ነገር ነው። ልጆች የወላጆቻቸውን ቋንቋ መናገር ከቻሉ ከቤተሰብ ጋር በቅርብ ይነጋገራሉ፤ ወደ ቤተሰብ ከመጣ ሰው ጋርም በፍቅር ሊነጋገሩ ይችላሉ። ይህም ማንነታቸውን እና ሃይማኖታቸውን አንዲያውቁ ይረዳቸዋል። የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት አንድ ህጻን በተለይ እስከ ዓመት ባለው እድሜ ውስጥ ብዙ ቋንቋዎች መማር የሚችል በመሆኑ የሚኖበትን ሀገርም ሆነ የቤተሰቡን ቋንቋ በቀላሉ መያዝ ይችላ ቋንቋ የማስተማር ትልቁ ሥራ የወላጅ ነው ስለዚህ ወላጅ ማድረግ ያለበት በራሱ ቋንቋ ማናገር፣ወደ ትውልድ ሀገራቸው ልጆቻቸውን ይዘው ሄደው ከዘመዶቻቻው ጋር አብረው እረፍት እንዲያሳልፉ ማድረግ ቋንቋቸውን እና ባህላቸውን የሚማሩበት መጻሕፍትን እና ሲዲዎችን መጠቀም በቅድስት ቤተክርስቲያን የሕጻናት //ቤት እንዲማሩ ማድረግ ነው የትውልድ ሀገራቸውን ቋንቋ ማወቅ ከቤተሰባቸው ጋር ለመግባባት ብቻ ሳይሆን ልጆቹ ወደፊት ለሀገራቸው ለኢትዮጵያ ባዕድ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል፤ ባህላቸውን እና ታሪካቸውን በራሳቸው ቋንቋ እንዲያውቁ ያስችላቸዋል፤ ከዚህ በተጨማሪም ወደፊት በኢትዮጵያ በምርምር፣ በንግድ እ በዲፕሎማሲ ግንኙነት ሥራዎች እንዲሳተፉ ይረዳቸዋል። ነቢዩ ኤርምያስበውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጒርጒርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን (ኤር፲፫፥፳፫) እንዳለ ሁሉ ልጆቻችን የምግባር መልካቸው እንዳይለ ቋንቋቸውን እና ማንነታቸውን ማሳወቅ ግድ ይለናል።

. የዘመኑን ቴክኖሎ ልጆች በአግባቡ እንዲጠቀሙ በማድረግ

በአሁኑ ወቅት ቴክኖሎጂ ዓለምን በጣም አቀራርቧታል። በድምጽ እና ምስል ጠቃሚውም ጎጂውም ነገር በቴሌቪዥን፣ በድረ ገጽ፣ በእጅ ሰልክ፣ በመጽሔትና በጋዜጣ በየትኛውም ቦታ ይገኛል። እነዚህ የሚዲያ ውጤቶች በተለይ ባደጉት ሀገሮች ለልጅም ሆነ ለአዋቂ በቀላሉ የሚገኙ ናቸው። ልጆቻችን የሚያዩትን ፣ የሚሰሙትን እና የሚያነቡትን ነገር ጠንቅቆ ማወቅ እና መቆጣጠር ያስፈልጋል። በተለይ በቴሌቪዥን የሚያዩትን ነገር ለይቶ ማወቅና ጊዜ መገደብ ያስፈልጋል። በተጨማሪ ቴሌቪዥንን በአግባቡ ካልተጠቀሙ ፣ በፊልም የሚያይዋቸውን ወንጀሎች እየተለማመዱ ወደ ማከናውን ይመጣሉ ፤ ለምሳሌ ስርቆት፣ አደንዛዥ ዕጽ መጠቀም ፣ መደባደብ … ። በሚዲያ የሚተዋወቁ የመንገድ ላይ ምግቦች (fast foods) በማየትም ለጤና ጎጂ ለሆኑ ምግቦች ልዩ ፍቅር ይኖራቸዋል። ልጆች አብዛኛውን ጊዜያቸውን ከዘመኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋር ስለሚያሳልፉ እና ከማኅበረሰቡ ጋር ስለማይገናኙ የብቸኝነትን (ግለኝነት) ሕይወት ይለማመዳሉ። ይህንን ለመከላከል ወላጆች ሰለዘመኑ ቴክኖሎጂ በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል። በቤት ውስጥም የወላጅ መቆጣጠሪያ (Parental control) በኢንተርኔት መስመር ላይ መጠቀም ይኖርባቸዋል። እነዚህ ሁሉ መፍትሔዎች ችግሩን ቢያቀሉትም ፣ ፈጽሞ እንዳይከሰት ማድረግ ግን አይችሉም። ከእነዚህ መፍትሔዎች ጋር የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ልጆችን በጉዳዩ ዙርያ ጥቅም እና ጉዳቱን ለይቶ ማስተማር እና ከወላጅ የተደበቀ ነገር እንዳይኖር ማድረግ ያስፈልጋል።

ማጠቃለያ

በዚህ በአውሮፓ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ እና ትውልደ ኢትዮጵያ ስደቱ በአንጻራዊነት ቅርብ ዓመታት በመሆኑ ብዙዎቹ ልጆች ታዳጊ ናቸው ። ስለዚህ ለሚቀጡሉት አመታት ልጆቻችን ቤተክርስቲያናቸውን እና ማንነታቸውን እንዲያውቁ በትምህርታቸውም እንዲጠነክሩ ካደረገን አዲሱ ትውልድ በሃይማኖት እና በምግባር የታነአምላኩን የሚፈራ፣ ማንነቱን የሚያውቅ፣ በሥጋዊና በመንፈሳዊ ጥበብ የተካነና መንግሥተ ሰማያትንም ለመውረስም የተዘጋጀ ይሆናል::

ደት ስንኖር ለልጆቻችን ልናወርሳቸው የምንችለው ትልቅ ሀብት እግዚአብሔርን መፍራት ነው። በአሁን ወቅት ዓለም ለክርስቲያኖች ፈታኝ መድረክ ነች። ይህን ፈተና ለመወጣት ትልቁ ሀብት ደግሞ ፈሪሐ እግዚብሔር ነው። ፈሪሐ እግዚአብሔር ያለው ሰው ጥበብ ይሰጠዋል። የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” (ምሳሌ፯፥፩) እንዲል። ፈሪሐ እግዚአብሔር ያለው ሰው መላክት በዙሪያው ይሰፍራሉ፤ ያድኑትማል (መዝ፺፥፲፩) እንደ ዮሴፍ ወደ ኅጢ በተጋበዘ ወቅትሰው ባያይ እግዚአብ ያያል። (ዘፍ፴፱፥፯፲፫) ይላል ስለዚህ በልጆች አስተዳደግ ጠንክረን መስራት እና ፈሪሐ እግዚአብሔርን ማስተማር ያለብን ዛ ነው።

ዋቢ ሕፍት

የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፦ መጽሐፍ ቅዱስ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት አዲስ አበባ ፲፱፻፹፱ ..

ፈሰሴ ገ/ሃና ፣ በላቸው ጨከነ የልጆች አስተዳደግ በዚህ ዘመን ተግዳሮቶች እና መፍትሔዎች። ሎንዶን፳፻፮ ዓ.ም.

ማኅበረ ቅዱሳን ሐመር ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ዓመት ቁጥር ነሐሴ ፳፻፬ ..

ዘውዴ /እግዚአብሔር ኦርቶዶክሳዊ ቤተሰብ እና የልጆች አስተዳደግ። አኮቴት አሳታሚዎች አዲስ አበባ። ፳፻፬ ..

*ኢጲፋኒያ ዘኦርቶዶክስ ተዋ በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት በታላቋ ታኒያ ለበዓለ ጥምቀት በተዘጋጀ ልዩ ዕትም ላይ የታተመ።