በዓለ ልደቱ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ

በበኩረ ፍሥሐ ቀሲስ ኃይለኢየሱስ ተመስገን

ታኅሣሥ 28 ቀን 2010 ዓ.ም.

“እስመ ናሁ እዜንወክሙ ዓቢየ ዜና ዘይከውን ፍሥሐ ለክሙ ወለኩሉ ሕዝብ “ሉቃ ፪ ፥፲

ለወልደ እግዚአብሔር ሁለት ልደታት እንዳሉት እናምን ዘንድ ይገባናል። አንዱ ከዘመን ሁሉ አስቀድሞ ከእግዚአብሔር አብ የተወለደው ልደት ነው። ሁለተኛውም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በኋላ ዘመን የተወለደው ልደት ነው፡፡ሃይማኖተ አበው ዘባስልዮስ ምዕራፍ ፴፬ ቁጥር ፮ ክፍል ፭።

ከመዝ ነአምን ዘአልቦቱ እም በሰማያት፤ ወአብ በዲበ ምድር፣ በሰማይ ያለእናት ከአብ መወለዱን፣ በምድርም ያለ አባት ከድንግል ማርያም መወለዱን እናምናለን። ይህንንም አባቶቻችን ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ቅድመ ዓለም ከእግዚአብሔር አብ ያለ እናት፣ አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ የተወለደ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አካላዊ ቃል ፤ ድኀረ ዓለም ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አባት፣ መለወጥ ሳያገኛት ዘር ምክንያት ሳይሆን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ የተወለደ፤ ወልደ እግዚአብሔር በመለኮቱ ወልደ ማርያም በትስብእቱ ብለው አምልተው ያስተምሩናል።

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝ ፻፱፥፫ “ወለድኩከ እምከርሥ እምቅድመ ኮከበ ጽባሕ” ዓለም ሳይፈጠር አስቀድሞ ባሕርይ ዘእምባሕርይ አካል ዘእምአካል ወለድኩኽ ብሎ እንደገለጸው ዓለም ከመፈጠሩ ዘመን ከመቈጠሩ በፊት እግዚአብሔር ወልድ ከእግዚአብሔር አብ ፣ፍጡራን ተመራምረው በማይደርሱበት ጥበብ  ተወልዷል ይህም  ቀዳማዊ ልደት ነው።

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ደኃራዊ ልደት ስናነሳ ጌታ ለአዳም የገባው ቃልኪዳን፣ የነቢያት ትንቢት እና ሱባኤ፣ የንጽሕተ ንጹሐን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ለአምላክ እናትነት መመረጥ፣በብርድ ወራት የጌታ በከብቶች በረት መወለድ፣ ገጹ እሳት አካሉ እሳት የሆነውን አምላክ ግዕዛን የሌላቸው አድግ ወላህም እስትንፋሳቸውን መገበራቸው፣ ሰማይ ዙፋኑ ምድርም የእግሩ መረገጫ አኃዜ ዓለም በእራኁ ኩሉ እኁዝ ውስተ እዴሁ የሚባል አምላክ፣መላእክትና እረኞች በጎል ተጥሎ በጨርቅ ተጠቅልሎ አይተውት ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ ብለው ማመስገናቸው ፣ የሰብአ ሰገል አምኃ ከምናስባቸው ነገሮች መካከል ሲሆኑ በአጠቃላይ ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ፣ ሰው ሆኖ ያዳነበት ጥበቡ ድንቅ መሆኑን የምናስብበት ነው።

ነቢያት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተመረጠችው ከድንግል እንደሚወለድ፣ የእናቱ ድንግልናም ቅድመ ወሊድ ጊዜ ወሊድ ድኅረ ወሊድ ተፈትሖ የሌለበት ዘላለማዊ መሆኑን ፣ በቤተልሔም  በከብቶች በረት  እንደሚወለድ እግዚአብሔር ገልጦላቸው ተንብየዋል።

ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ “እነሆ ድንግል በድንግልና ጸንሳ በድንግልና ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች”  ኢሳ ፯፥፲፬ ብሎ በትንቢት እንደተናገረው፤ ስምዖን አረጋዊ በዘመኑ ደርሶ አይኖቼ ማዳንህን አይተዋልና ባሪያህን አሰናብተው እንዳለ፤ የአምላክ ከድንግል ማርያም መወለድ በመንፈስቅዱስ ግብር በድንግልና ነው።

የአምላክን መወለድ ፤ነገረ ሥጋዌ ተገልጦላቸው “አንቺም ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መኻከል ትኾኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ዘላለማዊ የኾነ በእስራኤል ላይ ገዢ የሚኾን ይወጣልኛል።” ሚክ ፭፥፪ ብለው ጌታ በቤተልሔም እንደሚወልድ በትንቢት ተናግረዋል።

ደረቅ ሐዲስ በሚባለው የትንቢት ቃሉ የሚታወቀው ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ በከብቶች በረት ስለመወለዱ “በሬ ገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ ዐወቀ” ኢሳ ፩፥፫ ብሎ በመንፈሰ ትንቢት ተናግሯል፡፡

ለስም አጠራሩ ክብር የክብር ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቀጠሮው ጊዜ አምስት ሽ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ለአዳም በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዷል።

ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ በማቴ ፩፥፩-፲፰ እንደጻፈልን  በሀገራቸው በዕብራውያን ዘንድ ሴትና ወንድ አቀላቅሎ መቁጠር የለምና ሥርዓት አፈረሰ ይሉኛል ብሎ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትውልድ በዮሴፍ አንጻር ነው የቆጠረው። ወአልዓዛርኒ ወለደ ማትያንሃ፤ ወማትያንኒ ወለደ ያዕቆብሃ፤ወያዕቆብኒ ወለደ ዮሴፍሃ ፈኃሪሃ ለማርያም እንተ እምኔሃ ተወልደ እግዚእ ኢየሱስ ዘተብህለ ክርስቶስ።

አልዓዛርም ማትያንን ወለደ፤ ማትያንም ያዕቆብን ወለደ፤ ያዕቆብም ክርስቶስ የተባለ ኢየሱስ ከሷ የተወለደ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አገልጋይዋ ጠባቂዋ የሚሆን፣ ዮስፍን ወለደ። ወንጌላዊው በዮሴፍ የቆጠረበት ምክንያትም የዮሴፍ አያት ማትያን እና የእመቤታችን አያት ቅስራ የአልዓዛር ልጆች ፣ወንድማማቾች በመሆናቸው በትውልድ ሐረጋቸው ከመገናኛው ጒንዱ ሦስተኛ ትውልድ በመሆናቸው ነው። ይህም ማለት ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ አልዓዛር  ቅስራን፤ ቅስራ ኢያቄምን፤ ኢያቄምም ክርስቶስ የተባለ ኢየሱስ ከሷ የተወለደ እመቤታችንን ወለደ ብሎ መቁጠሩ ነው

ይሁን እንጅ በመጽሐፈ ልደቱ  እንደገለጸው ተስፍ ከተሰጣቸው ትንቢት ከተነገረላቸው ውጭ  የሆኑትን ከአረማውያን ወገን ትዕማርን ፣ሩትን ፣ራኬብን አንስቷል።ይህም ጌታ ከሁሉም ወገን መወለዱን፤ የማያምኑትን አሕዛብ እና የሚያምኑትን ሕዝብ አንድ ማድረጉንም ያስረዳናል። ከዕብራውያን ሴቶች በጌታ የልደት መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰችው ቤርሳቤህ እመ ሰሎሞን ናት። ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ መምሕር በመሆኑ ግርማውን ሳይፈራ ቅዱስ ዳዊት ኦርዮን  አስግድሎ  ሚስቱን ቀምቶ ሰሎሞንን ከቤርሳቤህ እንደወለደ ጽፏል።

የጌታን የትውልድ መጽሐፍ ከተረዳን በኋላ ሌላ የምናስበው የክርስቶስ በብርድ ወራት በከብቶች በረት መወለድ ነው።እመቤታችን ጌታን የወለደችው ትኖርበት በነበረው በናዝሬት ሳይሆን በቤተልሔም በከብቶች በረት ውስጥ ነው። ሰው ሁሉ ከግብር እንዲቆጠር ከአውግስጦር ቄሣር ትእዛዝ በወጣ ጊዜ ዮሴፍ  ከቤተ ዳዊት ስለሆነ ይኖሩበት ከነበረው ከናዝሬት ዘገሊላ ወደ ቤተልሔም ዘይሁዳ ወጥተው /ሂደው/ ነበር። በፈጠረው ዓለም እንግዳ የሆነ ጌታ በከብቶች በረት ተወለደ።ክብራቸው ሲገፈፍ አዳምና ሔዋን በቅጠል እንደተሸሸጉ ወደቀድሞ ቦታቸው፣ ወደቀድሞ ርስታቸው፣ ወደ ገነት ይመልሳቸው ዘንድ ወልደ ማርያም ክርስቶስ በለሶን ቅጠልን ለብሷል። አድግና ላህም እስትንፋሳቸውን አሟሙቀውታል፤ በሬ ገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ ዐወቀ ያለው የነቢየ እግዚአብሔርም ትንቢት ተፈጽሟል

በጌታ መወለድ፣በጠፋው አዳም ወደቀድሞ ቦታ ገንት፣ወደቀድሞ ክብር ልጅነት መመለስ ደስ የተሰኙት መላእክትም የምሥራቹን ለእረኞች አብስረዋል ።

በሉቃ ፪፥፰፡፳ በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት  ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ።እነሆም የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ፤የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አንጸባረቀ፤እነሱም በታላቅ ፍርሃት ተዋጡ።መልአኩ አይዟችሁ አትፍሩ አላቸው፤ፍርሃታቸውን አርቆ ታላቁን የምሥራች ነገራቸው ።

መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለበት፤ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የሚያድል፤ የዓለም መድኃኒት የሚሆን፤የባሕርይ አምላክ ክርስቶስ በዳዊት ከተማ በዳዊት ባሕርይ መወለዱንም አበሰራቸው። ምልክቱንም ጨምሮ ገለጸላቸው ሕፃኑ አውራ ጣቱን ታስሮ በጨርቅ ተጠቅልሎ በበረት ተጥሎ ታገኙታላችሁ ብሎ ምልክቱንም ጨምሮ ገለጸላቸው። መላእክትም አምላክ ለሆነ ሥጋ ከሥላሴ ጋራ ባንድነት ምስጋና ይገባዋል የሰው ግዕዛኑ ይሰጠው ዘንድ በምድርም እርቅ ተወጠነ እያሉ አመሰገኑ። እረኞቹም እግዚአብሔር የገለጸልንን ነገር እንወቅ ብለው ፈጥነው ሄዱ ዮሴፍንና እመቤታችንን ሕፃኑንም በበረት ተኝቶ አገኟቸው። እረኞችም መላእክት የነገሯቸውን አይተው አደንቁ እመቤታችን ግን ይህን ነገር ታስተውለው ነበር በልቡናዋም ታኖረው ነበር።

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት ስናነሳ  ሰብአ ሰገልን አብረን እንዘክራቸዋለን፡፡  ሀብተ ትንቢት የታደለው ልበ አምላክ የተባለ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት  በመዝ ፸፩፥፲፡፲፩  ስለ ሰብአ ሰገል (የጥበብ ሰዎች) ትንቢት ተናግሯል፡፡

ነገስተ ተርሴስ ወደሰያት አምኃ ያበውኡ የተርሴስ የደስያት ነገሥታት እጅ መንሻ ያቀርቡለታል አንድም ሰብአ ሰገል ለጌታ ሦስቱን ንዋያት ይገብሩለታል፡፡

ነገስተ ሳባ ወዓረብ ጋዳ ያመጽኡ የሳባ የዓረብ ነገሥታት እጅ መንሻ ያመጡለታል፡፡

ወይሰግዱ ሎቱ ኩሎሙ ነገስተ ምድር ባራቱ መዓዝን ያሉ ነገሥት ሁሉ እየመጡ ይሰግዱለታል።

ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ በማቴ ፪፥፩፡፲፪  ሰብአ ሰገል ሄሮድስ ነግሦ በነበረበት ዘመን፣ የይሁዳ ዕጣ በምትሆን  በቤተልሔም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተወልዶ ሳለ፣የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት አለ እያሉ ከምሥራቅ ተነስተው ኮከብ እየመራቸው ኢየሩሳሌም እንደደረሱ ፣ሄሮድስ የሕዝቡን ጸሐፍትና ሊቃነ ካህናትን ጠይቆ በቤተልሔም እንዲወለድ ባወቀ ጊዜ ወደቤተልሔም እንደሰደዳቸው፣የብላቴናውን ነገር ጠይቃችሁ ያገኛችሁት እንደሆን  እሰግደለት ዘንድ በኔ በኩል ተመልሳችሁ ንገሩኝ እንዳላቸው፣ይመራቸው የነበረው ኮከብ ቤተልሔም አድርሷቸው ሕጻኑን ከእናቱ ጋር አግኝተው ደስ ብሏቸው እንደሰገዱለት፤  ሣጥናቸውን ከፍተው ወርቅ፣ ዕጣን እና ከርቤ በእጅ መንሻነት እንደሰጡት ፣ በመጨረሻም  በሄሮድስ በኩል እንዳይመለሱ ራእይ አይተው በሌላመንገድ መመለሳቸውን በታመነ የወንጌል ቃል ጽፎልናል፡፡

 

በማቴ ፪፥፲፩ ሰብአ ሰገል ወድቀው ሰገዱለት ሣጥናቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት የሚል ንባብ እናገኛለን፡፡የወርቅ፣ዕጣን እና ከርቤ ምሳሌነት በቤተክርስቲያናችን ትርጓሜ መጻሕፍት ተተንትኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህንንም ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ሲያብራራው አምላክ ነውና ዕጣን አመጡለት ንጉሥም ነውና ወርቅ አመጡለት ስለኛ በፈቃዱ ለተቀበለው መዳኛችን ለሆነ ሞቱም ከርቤ አመጡለት ይላል (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ)፡፡

በወንጌል ቅዱስ ትርጓሜ ላይም  ምሳሌ ህጹጽ ቢሆንም ወርቅን ጽሩይነት በሃይማኖት፣የዕጣንን ምዑዝነት በተስፋ፣የከርቤመራራነት እና የተለያየን አንድ ማድረግ በፍቅር በመመሰል  ሃይማኖት፣ተስፍ፣ ፍቅር ገንዘቦችህ ናቸው ሲሉ  ወርቅ ዕጣን ከርቤ  አመጡለት ብለው ሊቃውንት ተርጉመውልናል፡፡

የጌታን ልደት ስናከብር ለተዋሕዶ የተመረጠች ንጽሕት ዘር የመመኪያችን ዘውድ እመቤታችንን ክርስቶስን ስላስገኘሽልን እንወድሻለን እንላታለን ይህ ሁሉ ምስጢር የተገለጸለት አባ ሕርያቆስም “ኦ ማርያም በእንተዝ ናፈቅረኪ ወናዓብየኪ።እስመ ወለድኪ ለነ መብልዐ ጽድቅ ዘበአማን ወስቴ ሕይወት ዘበአማን። እመቤታችን ማርያም ሆይ ስለዚህ ነገር እንወድሻለን ከፍ ከፍም እናደርግሻለን። የጽድቅ መብልን፡ የሕይወት መጠጥን ወልደሽልናልና” ብሎ አመስግኗታል። እረኞች ከመላእክት ጋር በዘመሩበት በጌታችን ልደት አማላካችን መራራ፣ኃጢአት የበዛበትን ሕይዎታችን ያጣፍጥልን አንድነቱን ያድለን እግዚአብሄር ወልድን  የሰው ልጆች ፍቅር ነውና ወደዚህ ዓለም ያመጣው ፍቅሩን ሰላሙን ይስጠን፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር።