በዓለ ደብረ ታቦርና ቡሄ

              ነሐሴ ፲፫ ቀን ፳፻፲፫ .


ጌታችን
ምሥጢረ መለኮቱን ለገለጠበት ለበዓለ ደብረ ታቦር እንኳን በሰላም አደረሰን!

ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን፣ ክብረ መንግሥቱንመግለጡን በማሰብ በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫ ቀን በዓሉ በድምቀት ይከበራል፡፡ ይህ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ዘንድቡሄበመባል ይታወቃል፡፡ ቡሄ ማለትመላጣ፣ ገላጣማለት ነው፡፡በአገራችን ክረምቱ፣ ጭጋጉ፣ ደመናው ተወግዶ የብርሃን ወገግታ የሚታይበት በዚሁ በዓል አካባቢ ስለ ኾነ በዓሉቡሄተብሎ ይጠራል፡፡ በዓለ ደብረ ታቦር ጌታችን ምሥጢረ መለኮቱን የገለጠበት፤ ብርሃን የታየበትና ድምፀመለኮቱ የተሰማበ  ዕለት ስለ ኾነየብርሃንወይምየቡሄበዓል ይባላል፡፡

ቡሄ ሲመጣ የክረምቱ ጨለማነት አልፎ ወደ ብርሃን፣ ወደ ጥቢ የሚያመራበት፤ ወደ መፀው የሚገባበት፤ ወገግታየሚታይበት፤ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚሸጋገርበት ወቅት በመኾኑ ከቡሄ በኋላ የጠነከረ ክረምትአይኖርም፡፡ ‹‹ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት›› እንዲሉ፡፡ በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎችየቡሄ ዕለት ማታ ምእመናን ችቦ ያበራሉ፡፡ ይህም በደብረ ታቦር ለታየው ብርሃነ መለኮት ምሳሌ ነው፡፡ ሕፃናቱ ይህበዓል ከመድረሱ በፊት ቀደም ብለው ጅራፍ ሲገምዱና ሲያጮኹ (ሲያኖጉ) ይሰነብታሉ፡፡ እናቶችም ለዚህ በዓልየሚኾን ዳቦ ለመጋገር ስንዴያቸውን ሲያጥቡ፣ ሲፈትጉ ይሰነብታሉ፡፡ በበዓሉ ዋዜማ (ነሐሴ ፲፪ ቀን) ሕፃናትበየቤቱ እየዞሩ ‹‹ቡሄ በሉ፤ ቡሄ በሉ፡፡ ቡሄ መጣ፤ መላጣ፤ ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ …›› እያሉ ይጫወታሉ፡፡በዚህ ጊዜ እናቶች ካዘጋጁት ዳቦ እያነሡ ይሰጧቸዋል፡፡ ሕፃናቱቡሄየሚሉትም ዳቦውን ነው፡፡

ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በገለጠበት ዕለት እረኞች ከብርሃኑ የተነሣ እየተገረሙና እየተደነቁ ወደ ቤትአልተመለሱም ነበር፡፡ የልጆቹን መዘግየት ያዩ ወላጆች ችቦ አብርተውና ዳቦ ይዘው ፍለጋ ወጥተዋል፡፡ቡሄለሚሉ ልጆች ሙልሙል ዳቦ የሚሰጠውና በበዓሉ ችቦ የሚበራውም ከዚህ ታሪክ በመነሣት ነው፡፡ ለክርስትናልጅ፣ ለአማች፣ ለምራት፣ ለዘመድ አዝማድ ዅሉ የቡሄ ዳቦ ይሰጣል፡፡ ልጆችም ዳቧቸውን እየገመጡ ጅራፍሲገርፉ ይውላሉ፡፡ የጅራፉ መጮኽ የድምፀ መለኮት ምሳሌ ሲኾን፣ ጅራፉ ሲጮኽ ማስደንገጡም ነቢያትናሐዋርያት በድምፀ መለኮት መደንገጣቸውንና መውደቃቸውን ያስታውሳል፡፡

መምህረ ሐዋርያት ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስቱን ተማሪዎቹን ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ በደብረ ታቦርምሥጢር መግለጡን በማስታዎስ የአብነት ተማሪዎች ከመምህራቸው ጋር በመኾን በዓለ ደብረ ታቦርን (ቡሄን) ያከብራሉ፤ ስሙን ይጠራሉ፡፡ የአብነት ተማሪዎች ‹‹ስለ ደብረ ታቦር›› እያሉ እኽል ከምእመናን በመለመንናገንዘብ በማዋጣት ጠላውን ጠምቀው፣ ዳቦውን ጋግረው፣ ቆሎውን ቆልተው ለደብረ ታቦር ዕለት ሊያስቀድሱየመጡትን ምእመናን በመጋበዝና እርስበርስ በመገባበዝ፣ እንደዚሁም ቅኔ በማበርከት በዓለ ደብረ ታቦርንበታላቅ ድምቀት ያከብራሉ፡፡ ይህም እስከ አሁን ድረስ በአብነት ትምህርት ቤቶች የሚሠራበት ነባር ትውፊትነው፡፡

ነገር ግን በአንድ አካባቢዎች በተለይ በከተማ ዙሪያ በዓለ ደብረ ታቦር (ቡሄ) ሃይማኖታዊ ትውፊቱን የለቀቀይመስላል፡፡ ለዚህም ልጆች የሚጫወቱበት መዝሙር ግጥሙና ዜማው ዓለማዊ መልእክት የሚበዛበት መኾኑ፤በወቅቱ ችቦ ከማብራት ይልቅ ርችት መተኮሱና በየመጠጥ ቤቱ እየሰከሩ መጮኹ፤ ወዘተ. የበዓሉን መንፈሳዊትውፊት ከሚያደበዝዙ ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም በዚህ በዓል ገንዘብለመሰብሰብ ብቻ የሚሽቀዳደሙ ነገር ግን የበዓሉን ታሪካዊ አመጣጥ የማያዉቁ ልጆችም ጥቂቶች አይደሉም፡፡

ስለዚህ ወላጆች ለልጆቻቸው የበዓለ ደብረ ታቦርን መንፈሳዊነት፣ የመዝሙሮቹን ያሬዳዊነትና አከባበሩን ከቤተክርስቲያን መምህራን በመጠየቅ ማስተማር፤ ልጆችም ከወላጆች ወይም ከመምህራን በመጠየቅ የበዓሉንአከባበር መረዳትና የዚህን በዓል መንፈሳዊ ትውፊት ሳይበረዝ ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባቸዋል፡፡ ‹‹ድምፅህንሰማና በብሩህ ደመና፤ የቡሄው ብርሃን ለእኛ በራልን …›› የሚለውንና ይህን የሚመስሉ መንፈሳውያንመዝሙራትን እየዘመሩ በየቤቱ በመዘዋወር የሚያገኙትን ዳቦና ገንዘብ ለነዳያንና ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡልጆችንም ማበረታታትና አርአያነታቸውን መከተል ይኖርብናል፡፡

መልካም በዓል ይኹንልን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡

መጽሐፈ ታሪክ ወግስ፣ / አፈወርቅ ተክሌ፤ ፳፻፭ .ም፣ ገጽ ፫፻፲፭፫፻፲፯፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ፤ ፳፻፯ .ም፣ ገጽ ፻፲፩፡፡