ብሥራታዊዉ መልአክ

ክፍል ሦስት

ከማርታ ታከለ

የካቲት ፲፫ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

 

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችሁም ጋር ይሁን!

 

ባለፉት ክፍላት ስለ ቅዱሳን መላእክት አፈጣጠር፥ ቅዱስ ገብርኤል እውነተኛ አጽናኝ እና አረጋጊ መልአክ እንደሆነ፥ ስለ አዳምና ሔዋን አፈጣጠር፥ አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ስለማፍረሳቸውና ይኖሩባት ከነበረችው ከመልካሟ ስፍራ ከገነት እንደተባረሩ ተነጋግረናል። በመጨረሻም አዳምና ሔዋን በሱባኤና በጸሎት እግዚአብሔርን ይቅርታ ሲለምኑ ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ የሚል ቃል ኪዳን እንዳገኙ አይተናል።

በዛሬው ክፍልም በርእሳችን ያነሳነው ብስራታዊው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል  አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም እግዚአብሔር ለአዳም የገባውን ቃል አስቦ የምስራች ቃሉን አስይዞ ወደምድር እንደላከው እንነጋገራለን። ልጆች! ለመሆኑ እግዚአብሔር የላከው ይህ የደስታ ቃል ምን ነበር? ቅዱስ ገብርኤልንስ ወደማን ላከው?

የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ አምላክ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሊወለድ ፈቃዱ ሆነ፡፡ይህንንም የየምስራች ቃል ለቅዱስ ገብርኤል አስይዞ ወደ እርሷ ላከው። በዘመኑ ብዙ ደናግል መሲሑን/ አዳናችንን/ እንወልደዋለን ብለው ድንግልናቸውን ጠብቀው ይኖሩ ነበር።፡፡ የቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ከእነዚህ ደናግላን ለአንዲቱ የተነገረ ቢሆን ኖሮ ምኞታቸው እንደተፈጸመላቸው ይቆጥሩት ነበር፡፡ እመቤታችን ግን በንጽሕና እና በቅድስና ከቤተመቅደስ ስትኖር ለዚህ ክብር ራስዋን አስባ አታውቅም፡፡ በአምላክ ዘንድ ግን በንጽህናዋ፥ በቅድስናዋ እና በትህትናዋ ተመርጣ ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር የሰውን ነጻ ፈቃድ የሚያከብር ነውና ሊወለድ እንደወደደ በራሱ ፈቃድ ብቻ ልወለድ ሳይል ወደ ድንግል ማርያም  መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን ላከ፡፡

ቅዱስ ገብርኤልም በፍጹም ትህትና ከፍጥረት ሁሉ የከበረች ድንግልን አደግድጎ አመስግኖ እና አክብሮ ‘ደስ ይበልሽ ጸጋን የሞላብሽ ሆይ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው ፣ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ’ አላት፡፡

የእመቤታችን አስተዳደጓ በቤተ መቅደስ በመላእክቱ እቅፍ ነው፡፡ሦስት ዓመት ሲሆናት እናትና አባቷ ለቤተመቅደስ ከሰጧት በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ በአንድ ክንፉ አቅፎ በአንድ ክንፉ ደግፎ ሰማያዊ ምግብ እየመገበ አሳድጓታል።ስለዚህ ከእርሷ በፊትም ሆነ ከእርሷ በኋላ ያሉ ሰዎች የእግዚአብሔርን መልአክ ማየት አላስደነገጣትም። ነገር ግን የሰላምታው ቃል አስደነገጣት።እመቤታችን ሔዋንን ያሳተው የዲያቢሎስ ሽንገላ ወደ እርስዋ የመጣ ስለመሰላት ከመልአኩ የቀረበላት ሰላምታ አስደነገጣት፡፡ ‘ከሴቶች ሁሉ የተባረክሽ’ ያላትን ምስጋናም በደስታ አልተቀበለችውም፡፡ ‘እንዲህ ያለውን ሰላምታ እንደምን ይቀበሉታል’ ብላ አሰበች፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ‘ማርያም ሆይ! በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ’ በማለት አረጋጋት። ከዚያም ‘እነሆም ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም’ በማለት አዳምና ልጆቹ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲጠብቁት የነበረውን ምስራች አበሰራት።

እመቤታችን ግን አሁንም ጥያቄ ነበራት። ‘ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል?’ ብላ ጠየቀች።

ቅዱስ ገብርኤል ወደእመቤታችን ከመላኩ ከስድስት ወር በፊት ወደ ካህኑ ወደዘካርያስ ልጅ እንደሚወልድ እንዲነግረው ተልኮ መጥቶ ሲነግረው ዘካርያስ አላመነውም ነበር። ይህ ነገር እንዴት ይሆናል ብሎ ነበር። ቅዱስ ገብርኤልም ‘ቃሌን ስላላመንህ ይህ ነገር እስከሚሆን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ’ ብሎ የካህኑን የዘካርያስን አንደበት ዘግቶት ነበር። በእመቤታችን ፊት ግን የአምላኩ እናት ለመሆን ተመርጣለችና የተግሣጽን ቃል እንኳን አልተናገረም፡፡ ‘መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።እነሆ ኤልሳቤጥ ካንቺ ወገን የምትሆን ከሸመገለች ካረጀች በኋላ ጸነሰች። እነሆም ይህ ስድስት ወር ሆነ።ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም’ አላት፡፡ እርሷም ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር እንደሌለ ስለምታምን ከዚህ በኋላ አልተከራከረችውም። በታላቅ ትህትና ሆና ‘እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደቃልህ ይደረግልኝ’ በማለት ፈቃደኝነቷን ገለጸች።አምላክም በማኅጸንዋ አደረ፡፡

የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤልም ለአዳም ልጆች ለሁላችንም ከዚያ በፊት ያልተሰማ ከዚያ በኋላም የሚስተካከለው የማይኖር ድንቅ የደስታ ዜናን አብሳሪ ሆነ።

ልጆች! ይህ ቅዱስ መልአክ ዘወትር በእግዚአብሔር ፊት ስለሚቆም ለምድራችን አሁንም የደስታ የሰላም ብስራት እንዲያሰማት፥ እናንተንም በጥበብና በሞገስ በሃይማኖታችሁ ጸንታችሁ በእግዚአብሔር ቤት እንድታድጉ እንዲረዳችሁ ለምኑት!እኛን ሁላችንን ይረዱን ዘንድ መላእክትን ዘወትር በፊታችን እንዲሄዱ ያደረገ እግዚአብሔር ይመስገን። አሜን።

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር!

 

 

ምንጭ ፥  መጽሐፍ ቅዱስ፥ አክሲማሮስ፥ ገድለ አዳም፥ ድርሳነ ገብርኤል