ብሥራታዊዉ መልአክ

ክፍል ሦስት

ከማርታ ታከለ

የካቲት ፲፫ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

 

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችሁም ጋር ይሁን!

 

ባለፉት ክፍላት ስለ ቅዱሳን መላእክት አፈጣጠር፥ ቅዱስ ገብርኤል እውነተኛ አጽናኝ እና አረጋጊ መልአክ እንደሆነ፥ ስለ አዳምና ሔዋን አፈጣጠር፥ አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ስለማፍረሳቸውና ይኖሩባት ከነበረችው ከመልካሟ ስፍራ ከገነት እንደተባረሩ ተነጋግረናል። በመጨረሻም አዳምና ሔዋን በሱባኤና በጸሎት እግዚአብሔርን ይቅርታ ሲለምኑ ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ የሚል ቃል ኪዳን እንዳገኙ አይተናል።

በዛሬው ክፍልም በርእሳችን ያነሳነው ብስራታዊው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል  አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም እግዚአብሔር ለአዳም የገባውን ቃል አስቦ የምስራች ቃሉን አስይዞ ወደምድር እንደላከው እንነጋገራለን። ልጆች! ለመሆኑ እግዚአብሔር የላከው ይህ የደስታ ቃል ምን ነበር? ቅዱስ ገብርኤልንስ ወደማን ላከው?

የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ አምላክ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሊወለድ ፈቃዱ ሆነ፡፡ይህንንም የየምስራች ቃል ለቅዱስ ገብርኤል አስይዞ ወደ እርሷ ላከው። በዘመኑ ብዙ ደናግል መሲሑን/ አዳናችንን/ እንወልደዋለን ብለው ድንግልናቸውን ጠብቀው ይኖሩ ነበር።፡፡ የቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ከእነዚህ ደናግላን ለአንዲቱ የተነገረ ቢሆን ኖሮ ምኞታቸው እንደተፈጸመላቸው ይቆጥሩት ነበር፡፡ እመቤታችን ግን በንጽሕና እና በቅድስና ከቤተመቅደስ ስትኖር ለዚህ ክብር ራስዋን አስባ አታውቅም፡፡ በአምላክ ዘንድ ግን በንጽህናዋ፥ በቅድስናዋ እና በትህትናዋ ተመርጣ ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር የሰውን ነጻ ፈቃድ የሚያከብር ነውና ሊወለድ እንደወደደ በራሱ ፈቃድ ብቻ ልወለድ ሳይል ወደ ድንግል ማርያም  መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን ላከ፡፡

ቅዱስ ገብርኤልም በፍጹም ትህትና ከፍጥረት ሁሉ የከበረች ድንግልን አደግድጎ አመስግኖ እና አክብሮ ‘ደስ ይበልሽ ጸጋን የሞላብሽ ሆይ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው ፣ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ’ አላት፡፡

የእመቤታችን አስተዳደጓ በቤተ መቅደስ በመላእክቱ እቅፍ ነው፡፡ሦስት ዓመት ሲሆናት እናትና አባቷ ለቤተመቅደስ ከሰጧት በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ በአንድ ክንፉ አቅፎ በአንድ ክንፉ ደግፎ ሰማያዊ ምግብ እየመገበ አሳድጓታል።ስለዚህ ከእርሷ በፊትም ሆነ ከእርሷ በኋላ ያሉ ሰዎች የእግዚአብሔርን መልአክ ማየት አላስደነገጣትም። ነገር ግን የሰላምታው ቃል አስደነገጣት።እመቤታችን ሔዋንን ያሳተው የዲያቢሎስ ሽንገላ ወደ እርስዋ የመጣ ስለመሰላት ከመልአኩ የቀረበላት ሰላምታ አስደነገጣት፡፡ ‘ከሴቶች ሁሉ የተባረክሽ’ ያላትን ምስጋናም በደስታ አልተቀበለችውም፡፡ ‘እንዲህ ያለውን ሰላምታ እንደምን ይቀበሉታል’ ብላ አሰበች፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ‘ማርያም ሆይ! በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ’ በማለት አረጋጋት። ከዚያም ‘እነሆም ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም’ በማለት አዳምና ልጆቹ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲጠብቁት የነበረውን ምስራች አበሰራት።

እመቤታችን ግን አሁንም ጥያቄ ነበራት። ‘ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል?’ ብላ ጠየቀች።

ቅዱስ ገብርኤል ወደእመቤታችን ከመላኩ ከስድስት ወር በፊት ወደ ካህኑ ወደዘካርያስ ልጅ እንደሚወልድ እንዲነግረው ተልኮ መጥቶ ሲነግረው ዘካርያስ አላመነውም ነበር። ይህ ነገር እንዴት ይሆናል ብሎ ነበር። ቅዱስ ገብርኤልም ‘ቃሌን ስላላመንህ ይህ ነገር እስከሚሆን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ’ ብሎ የካህኑን የዘካርያስን አንደበት ዘግቶት ነበር። በእመቤታችን ፊት ግን የአምላኩ እናት ለመሆን ተመርጣለችና የተግሣጽን ቃል እንኳን አልተናገረም፡፡ ‘መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።እነሆ ኤልሳቤጥ ካንቺ ወገን የምትሆን ከሸመገለች ካረጀች በኋላ ጸነሰች። እነሆም ይህ ስድስት ወር ሆነ።ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም’ አላት፡፡ እርሷም ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር እንደሌለ ስለምታምን ከዚህ በኋላ አልተከራከረችውም። በታላቅ ትህትና ሆና ‘እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደቃልህ ይደረግልኝ’ በማለት ፈቃደኝነቷን ገለጸች።አምላክም በማኅጸንዋ አደረ፡፡

የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤልም ለአዳም ልጆች ለሁላችንም ከዚያ በፊት ያልተሰማ ከዚያ በኋላም የሚስተካከለው የማይኖር ድንቅ የደስታ ዜናን አብሳሪ ሆነ።

ልጆች! ይህ ቅዱስ መልአክ ዘወትር በእግዚአብሔር ፊት ስለሚቆም ለምድራችን አሁንም የደስታ የሰላም ብስራት እንዲያሰማት፥ እናንተንም በጥበብና በሞገስ በሃይማኖታችሁ ጸንታችሁ በእግዚአብሔር ቤት እንድታድጉ እንዲረዳችሁ ለምኑት!እኛን ሁላችንን ይረዱን ዘንድ መላእክትን ዘወትር በፊታችን እንዲሄዱ ያደረገ እግዚአብሔር ይመስገን። አሜን።

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር!

 

 

ምንጭ ፥  መጽሐፍ ቅዱስ፥ አክሲማሮስ፥ ገድለ አዳም፥ ድርሳነ ገብርኤል

 

 

ብሥራታዊዉ መልአክ

ክፍል ሁለት

ከማርታ ታከለ

የካቲት ፫ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

        እንደምን አላችሁ ልጆች? ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችሁም ጋር ይሁን!

 

ዛሬ በክፍል አንድ መጨረሻ ላይ ያነሳናቸውን ጥያቄዎች በመመለስ እንጀምራለን።

 

ቅዱስ ገብርኤልና ሌሎችም ቅዱሳን መላእክት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ለቁጣም ሆነ ለምህረት ወደሚልካቸው ቦታ እየተላላኩ መኖር ጀመሩ።ለቁጣም ሆነ ለምህረት የሚልካቸው በምድር ወደሚኖሩ ሰዎች ዘንድ ነበር።እነዚህ በምድር የሚኖሩ ሰዎች ማን ፈጠራቸው? ከየት መጡ?ለምንስ በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ይኖሩ ነበር አልን?

 

እግዚአብሔር አምላክ  ከዕለተ እሁድ አንስቶ እስከ ዕለተ አርብ ድረስ ሰማይንና ምድርን የሚታየውንና የማይታየውን ሁሉ ፈጠረ። በስድስተኛው ቀን ሁሉን ፈጥሮ ካዘጋጀ በኋላ ‘ ሰውን እንደመልካችን እንደምሳሌያችን እንፍጠር’ ብሎ ከሌሎቹ ፍጥረታት በተለየ መልኩ አዳምንና ሔዋንን ፈጥሮ የብርሃን ልብስ አልብሶ በገነት አስቀመጣቸው። ሌሎች ፍጥረታት ሁሉ እንዲገዙላቸው አደረገ። ልምላሜዋ ካማረ እና ብዙ ፍሬዎች ካሉባት ገነት ሲያስቀምጣቸው ግን አንድ ትዕዛዝ አዘዛቸው።በገነት ካሉት እጽዋት ሁሉ እንዲበሉ ነገር ግን በገነት መኻከል ካለችው ከዕፀ በለስ ፍሬ እንዳይበሉ አዘዛቸው። እነርሱም ትዕዛዙን አክብረው በደስታና በሐሴት በገነት መኖር ጀመሩ።

 

በዚህ ጊዜ በክፍል አንድ ታሪኩን ያየነው ሀሰተኛው መልአክ ሳጥናኤል በአዳም ላይ ቂም ያዘበት። እግዚአብሔር በእርሱ ምትክ እንደፈጠረውና ብዙ ክብር እንደሰጠው በማየቱ አዳምንና ሔዋንን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያጣላበትን ጊዜ ሲጠብቅ ኖረ።ከዕለታት በአንዱ ቀንም እባብ ሌሎች እንስሳት እንደሚያደርጉት አዳምንና ሔዋንን እጅ ለመንሳት ወይም ስም ሳይወጣለት ቆይቶ ኖሮ አዳም ለሌሎቹ እንስሳት ሁሉ ስም እንዳወጣላቸው ስም እንዲያወጣለት ወደ ገነት ሲሄድ ሳጥናኤል ያገኘዋል።ወዴት እንደሚሄድ ይጠይቀውና እሱም ወደዛው ስለሚሄድ አብረው ጉዟቸውን ይቀጥላሉ። ትንሽ እንደተጓዙ ‘ይህች ወደገነት የምታደርስ መንገድ አድካሚ ናት በየተራ እየተዛዘልን እንሂድ’ብሎ ሳጥናኤል እባብን ይጠይቀዋል በነገሩ ስለተስማማ ቀድሞ እሱ ይሸከመዋል። ትንሽ ከሄዱ በኋላ ያወርደውና በተራው እባብ ላይ ወጥቶ ይታዘልበታል። በዛውም ተፈጥሮው ረቂቅ መንፈስ ስለሆን በሰውነቱ ይገባል።

 

እባብም በገነት ፈሳሾችና አትክልቶች መኻከል ተቀምጣ ወደነበረችው ወደ ሔዋን መጣ። ‘ንግስተ ሰማይ ወምድር  ሆይ ሰላም ላንቺ ይሁን’ ብሎ ሰላምታ አቀረበላት። ሔዋንም ንግስተ ምድር እንጂ ንግስተ ሰማይ አይደለሁም ብላ በማስተካከል ፈንታ እባብ ባቀረበላት በዚህ አዲስ ሰላምታ ደስ ተሰኘች።እባብም  በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? አላት። ሔዋንም ለእባቡ ‘በገነት ካለው ከዛፍ ፍሬ እንበላለን፤ ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ፥ እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም’ ብሎ እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው ነገረችው።  እባብም ‘ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ’ አላት ።

 

በዚህ ጌዜ ሔዋን ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ አየች ከፍሬውም ወሰደችና በላች። ለአዳምም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ።

 

በዚህ ጊዜ የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ። ዕራቁታቸውን እንደ ሆኑ አወቁ። የበለስንም ቅጠሎች ሰፍተው ለራሳቸው ግልድም አደረጉ።ቀኑ በመሸ ጊዜ የእግዚአብሔርን ድምፅ ከገነት ውስጥ ሲመላለስ ሰሙ። አዳምና ሚስቱም ከእግዚአብሔር ፊት በገነት ዛፎች መካከል ተሸሸጉ። እግዚአብሔር አምላክም አዳምን ጠርቶ ‘ወዴት ነህ?’ አለው። እርሱም ‘በገነት ድምፅህን ሰማሁ፤ ዕራቁቴንም ስለ ሆንሁ ፈራሁ፥ ተሸሸግሁም።’ ብሎ መለሰ እግዚአብሔርም ‘ዕራቁትህን እንደ ሆንህ ማን ነገረህ? ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍ በውኑ በላህን?’ ብሎ ጠየቀው አዳምም አለ ‘ከእኔ ጋር እንድትሆን የሰጠኸኝ ሴት እርስዋ ከዛፉ ሰጠችኝና በላሁ።’ አለ። እግዚአብሔር አምላክም ሴቲቱን ‘ይህ ያደረግሽው ምንድር ነው?’ አላት። ሴቲቱም ‘እባብ አሳተኝና በላሁ።’ አለች።

 

እግዚአብሔር አምላክም እባቡን ‘ይህን ስላደረግህ ከእንስሳት ከምድር አራዊትም ሁሉ ተለይተህ አንተ የተረገምህ ትሆናለህ፤ በሆድህም ትሄዳለህ፥ አፈርንም በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ትበላለህ። በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ’ አለው።ለሴቲቱም ‘በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ፤ ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፥ እርሱም ገዥሽ ይሆናል’ አላት።አዳምንም ‘የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ።እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ። ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ፤ አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም ትመለሳለህ’ አለው። እግዚአብሔርም አዳምንና ሔዋንን ትዕዛዙን አላከበሩምና ከገነት አስወጣቸው፥ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በዔድን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ።

 

ከዚህ በኋላ አዳምና ሔዋን በተድላና ደስታ ይኖሩባት ከነበረችው ከገነት ተባረው ከገነት ፍጹም ከተለየችው ምድር ላይ ራሳቸውን አገኙ። በዚያም በጣም በሀዘንና በለቅሶ መኖር ጀመሩ። አዳምም ራሱን እስኪስትና በድን እስኪሆን ጊዜ ድረስ ደረቱን እየመታና እያለቀሰ ከእግዚአብሔር ይቅርታን ይለምን ነበር። ሔዋንም በእኔ ምክንያት ይህ ሁሉ ቅጣት መጣብን እግዚአብሔርን አሳዘንን።እግዚአብሔርን ያህል ጌታ ገነትን ያህል ቦታ አጣን እያሉ። ብዙ ሱባኤና ጸሎት ያዙ። እግዚአብሔርም አጥብቀው ይቅርታውን ስለፈለጉ፥ ‘ከ5500 ዘመን በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ’ በማለት ቃል ኪዳን ገባላቸው። እነርሱም ልጆች ወልደውና ብዙ ሆነው የማዳኑን ቀን ሲጠባበቁ ኖሩ።

 

ስለዚህ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም በጨለማና በሞት ጥላ ሲኖሩ ለቆዩት የአዳም ልጆች ቅዱስ ገብርኤል የምስራች ዜና ይዞ እንዲወርድ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ።

 

ልጆች ቅዱስ ገብርኤል የምስራቹን ሊናገር የመጣው ወይም የተላከው ወደማን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ይህንን በቀጣይ ክፍል እንመለከተዋለን።

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክብር!

ብስራታዊው መልአክ

ከማርታ ታከለ

ጥር ፳፮ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ክፍል አንድ

 

እንደምን አላችሁ ልጆች? የእግዚአብሔር ሰላም ከሁላችሁም ጋር ይሁን!

 

ዛሬ ስለ አንድ ቅዱስ የእግዚአብሔር መልአክ ታሪክ እነግራችኋለሁ።ይህ መልአክ ብስራታዊው መልአክ ይባላል። ብስራት ማለት ምስራች ወይም ደስ የሚል ዜና ማለት ነው።ብስራታዊ ማለት ደግሞ ባለምስራች ወይም ደስ የሚያሰኝ ዜና የሚናገር የሚያሰማ ማለት ነው።የዚህ ቅዱስ መልአክ ስሙ ገብርኤል ይባላል።ልጆች! ታዲያ ቅዱስ ገብርኤል ምን ደስ የሚያሰኝ ዜና አሰምቶ ብስራታዊ ተባለ?

 

ከላይ ያነሳነውን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ስለዚህ ቅዱስ መልአክ እና ስለሌሎች መላእክት አፈጣጠር በአጭሩ ልንገራችሁ፥

 

መላእክት በመጀመሪያው ቀን በዕለተ እሁድ ተፈጥረዋል። በተፈጠሩም ጊዜ ብርሃን አልነበረም። አንዱ መልአክ ሌላውን በሚነካው ጊዜ ሁሉም  ማን ፈጠረን? የሚለውን ጥያቄ መጠየቅ ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ከሁሉም በላይ የነበረው መልአክ ሳጥናኤል ነበር። ከበላዩ ማንም እንደሌለ ሲረዳና ሁሉም እሱ ከነበረበት በታች እንደሆኑ ሲያውቅ አንድ ነገር ተናገረ። ‘የፈጠርኳችሁ እኔ ነኝ’ አላቸው።የመጀመሪያውንም ሀሰት ተናጋሪ ሆነ።እሱ እንዳልፈጠራቸው እያወቀ ሁሉም ማን እንደፈጠራቸው አለማወቃቸውን ተመልክቶ ሀሰትን ከራሱ አመንጭቶ ተናገረ።

 

በዚህ ጊዜ ዛሬ ታሪኩን የምነግራችሁ ቅዱሱ መልአክ ገብርኤል ‘የፈጠረንን እስክናውቅ ድረስ በያለንበት ጸንተን እንቁም’ በማለት ሌሎች መላእክትን እንዲጸኑና ተረጋግተው የፈጠራቸው እስኪገለጥ እንዲጠብቁ ተናገረ። በዚህ ጊዜ ሳጥናኤልን ያመኑና የተከተሉ መላእክት አሉ። ገብርኤልን ሰምተው የፈጠራቸው እስኪገለጥ ጸንተው የቆሙ መላእክት አሉ። በመኻል ደግሞ መወሰን ሳይችሉ ቀርተው እየዋለሉ ያሉ መላእክት ነበሩ።

 

ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ‘ብርሃን ይሁን!’ አለ። ብርሃንም ሆነ። መላእክትም ፈጣሪያቸውን አወቁ። ሳጥናኤልም የመላእክት ሳይሆን የሀሰት ፈጣሪ መሆኑ ተጋለጠ። በሰራው ስህተት ጸጸት የማያውቅ አመጸኛ በመሆኑ የራሱን ሠራዊት ይዞ ከገብርኤልና ከሚካኤል ከሌሎችም የመላእክት አለቆችና ሠራዊቶቻቸው ጋር ተዋጋ። እነርሱም ሳጥናኤልን አሸነፉት። ሳጥናኤልን ያመኑትና መወሰን አቅቷቸው ሲወላውሉ የነበሩት መላእክት ሁሉ ከሰማይ ተጣሉ። ከክብራቸውም ተዋርደው ተባረሩ። ቅዱስ ገብርኤልና ሌሎች ቅዱሳን መላእክት ግን ከነክብራቸው የፈጠራቸውን እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ለመኖር ቻሉ።

 

ልጆች ቅዱስ ገብርኤልን ብስራታዊ መልአክ የምንለው ከላይ ባየነው ታሪክ ይመስላችኋል? አይደለም። ከላይ ባየነው ታሪክ ውስጥ መለእክትን እንዲጸኑና እንዲረጋጉ አድርጓል። በዚህም ሌሎች መላእክት ሳጥናኤልን ሰምተው ከክብራቸው ከመዋረድና ከመላእክት ዓለም ከመባረር አድኗቸዋል። ታዲያ ብስራታዊ ለምን ተባለ?

 

ከብዙ ዘመን በኋላ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ ወደ ምድር ተላከ። ታላቅ የምስራች፥ ታላቅ የደስታ ዜናም ይዞ ነበር።የሰው ልጆች ሁሉ ለዘመናት በተስፋ ሲጠብቁት የነበረውን ዜና የምስራች ይዞ ከሰማይ ወረደ።በጨለማ በሞት ጥላ ውስጥ ይኖሩ ለነበሩት የሰው ልጆች ወደ ህይወት የሚያመጣ ወደ ብርሃን የሚያወጣ የምስራች ዜና ይዞ ከሰማይ አየሩን በክንፎቹ እያማታ ወደምድር ወረደ።

 

ልጆች! በዛሬው ክፍል ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ። ቅዱስ ገብርኤል ከተፈጠረ ከብዙ ጊዜ በኋላ የምስራች ይዞ ወደ ምድር መጣ ብለናል። ምስራቹን ከማምጣቱ በፊት ምን ይሠራ ነበር? ምስራቹን ያመጣላቸው የሰው ልጆች እነማን ናቸው?ለምንስ በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ይኖሩ ነበር አልን? ቅዱስ ገብርኤልን ብስራታዊ ያሰኘው የብስራት መልእክትስ ምን ይሆን?

 

በቀጣይ ክፍል መልሱን እናገኛለን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር!

በእንግሊዝ ሀገር የቨርችዋል ግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ተመረቁ

ከዩኬ ንዑስ ማእከል 

ነሐሴ ፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ተመራቂ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች (በከፊል) ከአባቶች ጋር

በማኅበረ ቅዱሳን አዉሮፓ ማእከል በዩናይትድ ኪንግደም ን/ማእከል አስተባባሪነት ላለፉት ሦስት ዓመታት ተከታታይ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ሲማሩ የነበሩ 11 የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ሐምሌ 24 ቀን 2013 ዓ/ም በአባቶች ቡራኬ ተመረቁ። በለንደን ደብረ ገነት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አዳራሽ በተካሄደዉ በዚህ የተማሪዎች ምርቃት መርሐ ግብር ላይ ካህናት አባቶች፣ ተመራቂ ተማሪዎችና የተመራቂ ቤተሰቦች፣ ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች፣ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት፣ ሌሎች የግቢ ጉባኤ እንዲሁም የሰ/ት/ቤት ተማሪዎች የተገኙ ሲሆን ሌሎች የአዉሮፓ ማእከል አባላት እና ታዳሚዎች መርሐ ግብሩን በዙም (Zoom) ተከታትለዋል። የአዉሮፓ ማእከል ሰብሳቢ ዲ/ን ፈንታ ጌቴ ለተመራቂዎች የ’እንኳን ደስ ያላችሁ’ መልእክት አስተላልፈዋል። በዚህም ተመራቂዎች ወደ ማኅበረ ቅዱሳን ተቀላቅለዉ የማኅበሩን አገልግሎት እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።

ትምህርት በመልአከ ሰላም ቀሲስ አዲስ ሲሰጥ

በዚህ የምረቃ መርሐ ግብር ላይ፣ መልአከ ሰላም ቀሲስ አዲስ አበበ የለንደን ደብረ ገነት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይና የስብከተ ወንጌል ኃላፊ ትምህርት ሰጥተዋል። በተጨማሪም ተማራቂዎችና የፍሬ ሃይማኖት ሰ/ት/ቤት ተማሪዎች መዝሙር ያቀረቡ ሲሆን በግቢ ጉባኤ በመምህርነት ከሚያገለግሉት አባቶች መካከል መልአከ ሣህል ቀሲስ ዶ/ር ያብባል ሙሉዓለም እና ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ፍስሐ ለተመራቂዎች መልእክት አስተላልፈዋል።

 

ለተመራቂዎች የመስቀል ስጦታ በአባቶች ሲሰጥ

 

ለተመራቂዎች የመስቀል ስጦታ በአባቶች አማካኝነት ተበርክቷል። በን/ማእከሉ የተተኪ ትዉልድ እና ግቢ ጉባኤ ክፍል ተወካይ ለመርሐ ግብሩ ታዳሚዎች መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን በዚህም ለግቢ ጉባኤዉ ስኬት አስተዋጽኦ ያደረጉትን መምህራንና ሌሎች አካላትን በሙሉ አመስግነዋል። ለምረቃ መርሐ ግብሩ የቤተ ክርስቲያኑን አዳራሽ ለፈቀደው የቤተ ክርስቲያኒቱ ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት ምስጋናቸዉን አቅርበዋል።

የተተኪ ትዉልድ ንዑስ ክፍል ባለፈዉ ዓመት ዕድሜያቸዉ ሰባት ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ከሦስት መቶ በላይ የሚደርሱ ህጻናትን፣ በየዕድሜያቸዉ ለይቶ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በእንግሊዘኛ ቋንቋ ሲሰጥ መቆየቱን አስታዉሰዉ ትምህርቱን በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል። በግቢ ጉባኤ ንዑስ ክፍልም እንዲሁ አዳዲስ የአንደኛ ዓመት ተማሪዎችን ለመመዝገብ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጸዉ ይህንን የምዝገባ መልእክት በማስተላለፍ ሁሉም አካላት እንዲተባበሩ ጠይቀዋል።

የ’ቨርችዋል’ ግቢ ጉባኤዉ በዩኬ በመጀመሩ ምክንያት የዘንድሮ ተመራቂዎች ሁሉም ከዩኬ ሲሆኑ፣ ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ፣ ግቢ ጉባኤዉ በሌሎች የአዉሮፓ አገሮች ያሉ ተማሪዎችን ያካተተ በመሆኑ አሁን ላይ ወደ አዉሮፓ ግቢ ጉባኤነት ያደገ መሆኑን ገልጸዋል።

የዐቢይ ጾም ሳምንታት (ለሕፃናት) – ክፍል አራት

፮. ገብር ኄር

በልደት አስፋው

ሚያዝያ ፮ ቀን ፳፻፲፫ዓ.ም

ሰላም ናችሁ ልጆች? ባለፈው ዝግጅት ስለ ደብረ ዘይት ተምረናል፡፡ ዛሬ ደግሞ ስለ ‹ገብር ኄር› እንማራለን፡፡ ስድስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት (እሑድ) ‹ገብር ኄር› ይባላል፡፡ ትርጕሙ ‹ታማኝ፣ በጎ፣ ደግ አገልጋይ› ማለት ነው፡፡ ልጆች! አንድ ባለጠጋ አገልጋዮቹ ነግደው እንዲያተርፉበት ለአንዱ አምስት፤ ለሁለተኛው ሁለት፤ ለሦስተኛው አንድ መክሊት ሰጣቸው፡፡ ልጆች! ‹መክሊት› የገንዘብ ስም ነው፡፡

ከዚያ በኋላ አምስት እና ሁለት መክሊት የተቀበሉት ሁለቱ አገልጋዮች በተሰጣቸው መክሊት ነግደው እጥፍ አትርፈው ለባለ ጌታው አስረከቡ፡፡ ስለዚህም ገብር ኄር (ታማኝ አገልጋይ) ተብለው ተመሰገኑ፤ ልዩ ክብርን አገኙ፡፡ አንድ መክሊት የተቀበለው አገልጋይ ግን የተቀበለውን መክሊት ቀብሮ ካቆየ በኋላ ምንም ሳያተርፍበት ለጌታው አስረከበ፡፡ ይህ አገልጋይ ‹ገብር ሐካይ› ይባላል፡፡ ‹ሰነፍ አገልጋይ› ማለት ነው፡፡ በመክሊቱ ባለማትረፉ የተነሣ ቅጣት ተፈርዶበታል፡፡

የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፳፭ ቍጥር ፲፬-፵፮ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ብታነቡት ሙሉ ታሪኩን ታገኙታላችሁ፡፡ ልጆች! ስድስተኛው የዐቢይ ጾም እሑድ ስለ እነዚህ አገልጋዮች እና ስለ መንፈሳዊ አገልግሎት ጥቅም ትምህርት የሚቀርብት ሳምንት በመኾኑ ‹ገብር ኄር› ተብሏል፡፡ እናንተም በተሰጣችሁ ጸጋ ብዙ ምግባር መሥራት አለባችሁ እሺ? መልካም ልጆች! ለዛሬው በዚህ ይበቃናል፡፡ በቀጣይ ደግሞ ስለ ኒቆዲሞስ እንማማራለን፡፡ ሰላመ እግዚአብሔር ከዅላችን ጋር ይኹን!

የዐቢይ ጾም ሳምንታት (ለሕፃናት) : – ክፍል ሦስት

በልደት አስፋው

መጋቢት ፳፪ ቀን ፳፻፲፫ዓ.ም

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ባለፈው ዝግጅታችን ከመጀመሪያው እሑድ እስከ ሦስተኛው እሑድ (ከዘወረደ ጀምሮ እስከ ምኵራብ) ድረስ የሚገኙትን የዐቢይ ጾም ሳምንታት የሚመለከት ትምህርት አቅርበንላችሁ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ አራተኛውን የዐቢይ ጾም ሳምንት (መጻጕዕን) የሚመለከት ትምህርት ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ መልካም ንባብ!

፬. መጻጕዕ

ልጆች! አራተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹‹መጻጕዕ›› ይባላል፡፡ መጻጕዕ ማለት በሽተኛ ማለት ነው፡፡ ይህ ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት በበሽታ ተይዞ የነበረውን ሰው የፈወሰበት ዕለት ነው /ዮሐ.፭.፩-፱/፡፡

ልጆች! ቤተሳይዳ የምትባል አንዲት የጠበል መጠመቂያ ሥፍራ ነበረች፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ወደዚያች መጠመቂያ ሥፍራ እየመጣ ውኃውን ከባረከው በኋላ ቀድሞ ገብቶ የተጠመቀ በሽተኛ ካለበት ከማንኛውም ደዌ (በሽታ) ይፈወስ ነበር፡፡ በዚያ ሥፍራ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ከበሽታው ለመፈወስ ብሎ ሲጠባበቅ የነበረ አንድ መጻጕዕ (በሽተኛ) ነበር፡፡ ውኃው በተናወጠ ጊዜ ሌሎች ቀድመው ገብተው እየተፈወሱ ሲሔዱ እሱ ግን ለሰላሣ ስምንት ዓመት በዚያ ቆየ፡፡

ከዚያ በኋላ ጌታችን በዚያ ሥፍራ ሲያልፍ ይህንን መጻጕዕ ተኝቶ አየው፡፡ በዚህ ጊዜ ለብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ ‹‹ልትድን ትወዳለህን?›› ብሎ ከጠየቀው በኋላ እምነቱንና ጽናቱን አይቶ ‹‹ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሒድ›› አለው፡፡ በጌታችን ቃል ሰውዬው ወዲያውኑ ከበሽታው ዳነ፤ አልጋውንም ተሸክሞ የእግዚአብሔርን ቸርነት እየመሰከረ ሔደ፡፡ በአጠቃላይ አራተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት የመጻጕዕ ታሪክ የሚነገርበት፤ እንደዚሁም የአምላካችን ቸርነቱ፣ ይቅርታው፣ መሐሪነቱ የሚታወስበት ዕለት ነው፡፡

ልጆች! ደብረ ዘይትን የሚመለከት ትምህርት ደግሞ በሌላ ቀን እናቀርብላችኋለን፡፡ ለዛሬው ከዚህ ላይ ይቆየን፡፡ እስከዚያው ድረስ ሰላመ እግዚአብሔር ከዅላችሁ ጋር ይኹን!

የዐቢይ ጾም ሳምንታት (ለሕፃናት) – ክፍል ሁለት

በልደት አስፋው

መጋቢት ፲፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ደኅና ናችሁ? እግዚአብሔር ይመስገን!፡፡ ልጆች! በልዩ ልዩ ምክንያት አልችል ብለን ዘግይተናል፡፡ በቅድሚያ በገባነው ቃል መሠረት ወቅቱን ጠብቀን ትምህርቱን ባለማቅረባችን እናንተን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡

ልጆች! የካቲት ፲፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ባቀረብንላችሁ ትምህርት ከሰባቱ አጽዋማት መካከል ዐቢይ ጾም አንዱ እንደኾነ፣ ዐቢይ ጾም ማለት ታላቅ ጾም ማለት እንደኾነ፣ ጾሙ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ጾም በመኾኑ ታላቅ እንደተባለ፣ ዕድሜአቸው ሰባት ዓመት ከኾናቸው ሕፃናት ጀምሮ ዅሉም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ዐቢይ ጾምን እና ሌሎችንም አጽዋማት መጾም እንደሚገባቸው፣ እንደዚሁም ስምንቱ የዐቢይ ጾም ሳምንታት (እሑዶች) ስማቸው ማን ማን እንደሚባል ነግረናችሁ ነበር፡፡

ልጆች! ሰባቱ አጽዋማት ማን ማን እንደሚባሉም ጠይቀናችሁ ነበር አይደል? መልሱንስ ጠይቃችሁ ተረዳችሁ? በጣም ጥሩ ልጆች! መልሱን እናስታውሳችሁ፤ ሰባቱ አጽዋማት የሚባሉት፡-

፩. ጾመ ነቢያት

፪. ጾመ ገሃድ (ጋድ)

፫. ጾመ ነነዌ

፬. ዐቢይ ጾም

፭. ጾመ ድኅነት (ረቡዕ እና ዓርብ)

፮. ጾመ ሐዋርያት

፯. ጾመ ፍልሰታ (የእመቤታችን ጾም) ናቸው፡፡

በአሁኑ ሰዓት ዐቢይ ጾምን እየጾምን ነው፡፡ የምንገኘውም ሦስተኛው ሳምንት ላይ ሲኾን ስሙም ‹‹ምኵራብ›› ይባላል፡፡ የሚቀጥለውና አራተኛው ሳምንት ደግሞ ‹‹መጻጕዕ›› ተብሎ ይጠራል፡፡

ልጆች! በዛሬው ዝግጅታችን ከመጀመሪያው እሑድ እስከ ሦስተኛው እሑድ (ከዘወረደ ጀምሮ እስከ ምኵራብ) ድረስ የሚገኙትን የዐቢይ ጾም ሳምንታት የሚመለከት ትምህርት ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ ትምህርቱን እንድከታተሉት በአክብሮት ጋብዘናችኋል!

፩. ዘወረደ

ልጆች! ከዐቢይ ጾም ሳምንታት መካከል የመጀመሪያው ሳምንት ‹‹ዘወረደ›› ይባላል፡፡ ዘወረደ ማለት ከላይ የመጣ፣ የወረደ ማለት ነው፡፡ ይህም አምላካችን ዓለምን ለማዳን ሲል ሥጋ መልበሱን (ሰው መኾኑን) ያመለክታል፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ ወርዶ፣ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቆ፣ ወንጌልን ለዓለም ካስተማረ በኋላ በፈቃዱ መከራ ተቀብሎ፣ በመስቀል ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ ከሙታን ተነሥቶ ዓለምን አድኗል፡፡ ልጆች! የመጀመሪያው ሳምንት የአምላካችን የማዳን ሥራ በስፋት የሚነገርበት ወቅት በመኾኑ ‹‹ዘወረደ›› ተብሎ ተሰይሟል፡፡

፪. ቅድስት

ሁለተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹‹ቅድስት›› ይባላል፡፡ ቅድስት ማለት የተለየች፣ የተመረጠች፣ የከበረች ማለት ነው፡፡ ልጆች! ለምን የተለየች፣ የተመረጠች፣ የከበረች እንደተባለች ታውቃላችሁ? ቅዱስ አምላካችን እግዚአብሔር ዓለምን (ሰውን) ለመቀደስ ሲል ወደ ምድር መምጣቱንና ዐቢይ ጾምን መጾሙን ለማስረዳት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሰንበትን ክብር ለማስገንዘብ ነው፡፡ ሰንበት ቅድስት፣ የተለየች፣ የተመረጠች፣ የከበረች ዕለት ናት፡፡ ስለዚህም ልጆች! ሁለተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹‹ቅድስት›› ተብሎ ይጠራል፡፡

፫. ምኵራብ

ልጆች! ሦስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ደግሞ ‹‹ምኵራብ›› ይባላል፡፡ ምኵራብ ማለት አዳራሽ ማለት ነው፡፡ ምኵራብ ድሮ የነበሩ የእግዚአብሔር ሰዎች መንፈሳዊ ትምህርት ይማሩበት የነበረ  ሥፍራ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ይህንን የጸሎት ሥፍራ ሰዎች የንግድ ቦታ አደረጉት፡፡ ይህንን ዓለማዊ ተግባር ሲፈጽሙ የነበሩትን ዅሉ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል፡፡ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት›› ብሎ ከምኵራብ አስወጣቸው፡፡ ከዚያም ቃለ እግዚአብሔር አስተማራቸው፡፡ ልጆች! የእግዚአብሔር ቤት የጸሎት ቤት እንጂ የንግድ መነገጃ ሥፍራ አለመኾኑን ከዚህ ታሪክ እንማራለን፡፡

ለዛሬው በዚህ ይቆየን፡፡ ቀጣዩን ትምህርት ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በሚቀጥለው ዝግጅት ይዘንላችሁ እንቀርባለን፡፡ እስከዚያው ድረስ ሰላመ እግዚአብሔር ከዅላችን ጋር ይኹን!

ዐቢይ ጾም ለሕጻናት

በልደት አስፋው

                                                       መጋቢት ፩ ቀን ፳፻፲፫  ዓ.ም

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ባለፈው ሳምንት ስለ ነቢዩ ዮናስ እና ስለ ነነዌ ሰዎች የጻፍንላችሁን ታሪክ አነበባችሁት? ጎበዞች፡፡ ከታሪኩ ውስጥ ያልገባችሁ ትምህርት ካለ ከቤተ ክርስቲያን መምህራን በመጠየቅ መረዳት ትችላላችሁ፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን ደግሞ ስለ ዐቢይ ጾም አጭር ትምህርት ይዘንላችሁ ቀርበናል፤

ልጆች! ‹‹ዐቢይ ጾም›› ማለት ታላቅ ጾም ማለት ነው፡፡ ዐቢይ ጾም በቤተ ክርስቲያናችን በዐዋጅ እንዲጾሙ ከታወጁ ከሰባቱ አጽዋማት መካከል አንዱ እና ዋነኛው ነው፡፡ ጾሙ ታላቅ የተባለበት ምክንያትም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ጾም በመኾኑ ነው፡፡

ልጆች! ይኽንን ጾም ዕድሜአቸው ሰባት ዓመት ከኾናቸው ሕፃናት ጀምሮ ዅሉም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች እንዲጾሙት የቤተ ክርስቲያናችን ሕግ ያዝዛል፡፡ እንዴት ነው ታዲያ ሰባት ዓመትና ከዚያ በላይ የኾናችሁ ሕፃናት አጽዋማትን እየጾማችሁ ነው አይደል? እየጾማችሁ ከኾነ በጣም ጎበዞች ናችሁ ማለት ነው፤ በዚሁ ቀጥሉ፡፡

ዕድሜአችሁ ለመጾም ደርሶ መጾም ያልጀመራችሁ ካላችሁ ደግሞ ከቤተሰቦቻችሁ ጋር ተመካክራችሁ እስከምትችሉበት ሰዓት ድረስ በመጾም ጾምን ከልጅነታችሁ ጀምራችሁ ተለማመዱ፤ የጾሙ ተሳታፊዎችም ኹኑ እሺ? በሕመም ምክንያት መድኀኒት የምትወስዱ ከኾነ ግን መድኀኒታችሁን ስትጨርሱ ትጾማላችሁ፡፡

ልጆች! የዘንድሮው (የ፳፻፱ ዓ.ም) ዐቢይ ጾም የሚጀመረው መቼ እንደ ኾነ ታውቃላችሁ? የካቲት ፲፫ ቀን ነው፡፡ የሚፈታው ማለትም የሚፈሰከው ደግሞ ከአምሳ አምስት ቀናት በኋላ ሚያዝያ ፰ ቀን ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ዓመት የፋሲካ በዓል ሚያዝያ ፰ ቀን ይውላል ማለት ነው፡፡

በዐቢይ ጾም ውስጥ የሚገኙት አምሳ አምስቱ ቀናት በስምንት ሳምንታት (እሑዶች) የተከፋፈሉ ናቸው፡፡ የእያንዳንዱ ሳምንት ወይም እሑድ መጠሪያ ስሞችም የሚከተሉት ናቸው፤

የመጀመሪያው ሳምንት (እሑድ) – ዘወረደ

ሁለተኛው ሳምንት (እሑድ) – ቅድስት

ሦስተኛው ሳምንት (እሑድ) – ምኵራብ

አራተኛው ሳምንት (እሑድ) – መጻጕዕ

አምስተኛው ሳምንት (እሑድ) – ደብረ ዘይት

ስድስተኛው ሳምንት (እሑድ) – ገብር ኄር

ሰባተኛው ሳምንት (እሑድ) – ኒቆዲሞስ

ስምንተኛው ሳምንት (እሑድ) – ሆሣዕና

ተብለው ይጠራሉ፡፡

የፋሲካ በዓል የሚከበርበት የመጨረሻው የዐቢይ ጾም እሑድ ደግሞ ትንሣኤ ወይም ፋሲካ ይባላል፡፡

ልጆች! እንደ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ እነዚህን ሳምንታት (እሑዶች) የሚመለከት ትምህርት በየሳምንቱ እናቀርብላችኋለን፡፡ እስከዚያው ድረስ ከቤተ ክርስቲያን መምህራን ወይም ደግሞ ከወላጆቻችሁ ጠይቃችሁ ሰባቱ አጽዋማት የሚባሉት ማን ማን እንደ ኾኑ አጥንታችሁ ጠብቁን እሺ?

በሉ እንግዲህ ልጆች በሌላ ዝግጅት እስከምንገናኝ ድረስ ሰላመ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይኹን፡፡

ይቆየን

የጥምቀት በዓል በዮርዳኖስ ወንዝ

ጥር 11 ቀን 2013..

ከወልደ ኢየሱስ /ቤካ ፋንታ/

ልጆችዬ እንኳን ለጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ! ዛሬ ስለ ታላቁ በዓል ስለ ጥምቀት ብዙ የምነግራችሁ ነገር አለኝ፡ ፡ በደንብ ተከታተሉኝ እሺ፡፡

በገዳም ውስጥ ለሠላሳ ዓመት ለብቻው ሆኖ እግዚአብሔርን እያመሰገነ የሚኖር የእግዚአብሔር አገልጋይ ነበር፡፡ ስሙም ቅዱስ ዮሐንስ ይባላል፡፡ ልጆችዬ የቅዱስ ዮሐንስ ልብስ ምንድር መሰላችሁ የግመል ቆዳ ነበረ፣ የሚበላው ደግሞ በበረሃ የሚገኝ ማር ነው፡፡ በገዳም ሲኖር ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን በደስታ እየዘመረ ያመሰግነው ነበር፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን ከሚኖርበት ገዳም ተነሥቶ ዮርዳኖስ ወደሚባል ወንዝ እያስተማረ መጣ፡፡ ትምህርቱም “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ፡፡” የሚል ነው፡፡ ያን ጊዜ ይህንን ትምህርት የሰሙ በጣም ብዙ ሕፃናት፣ ወጣቶች እና ትልልቅ ሰዎች ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ተሰብስበው መጡና ያጠፉትን ጥፋት፣ የበደሉትን በደል፣ የሠሩትን ኃጢአት ሁሉ እየነገሩት /እየተናዘዙ/ በጸበል አጥምቀን አሉት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም የዮርዳኖስን ወንዝ በእግዚአብሔር ስም ሲባርከው ጸበል ሆነ፡፡ ከዚያም የተሰበሰቡትን ሁሉ ወንዶችን ሴቶችን እና ሕፃናትን በጸበሉ አጠመቃቸው፡፡

ልጆችዬ ከዚያም ምን ሆነ መሰላችሁ? ፈጣሪያችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሊጠመቅ መጣ፡

  • አጥማቂው ቅዱስ ዮሐንስም ኢየሱስ ክርስቶስን ሲያየው ፈጣሪዬ ሆይ አጥምቀኝ አለው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን አይሆንም አንተ አጥምቀኝ ብሎት በጥር 11 በቅዱስ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ፡፡ ስለዚህም አምላካችን በዚህች ቀን ስለተጠመቀ ዛሬ የምናከብረው የጥምቀት በዓላችን የተባረከ ሆነ፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ ከውኃ ሲወጣ በጣም የሚያስደንቅ ተአምር ታየ፡፡ ሰማያት ተከፈቱ፤ ከሰማዩ ውስጥም መንፈስ ቅዱስ በነጭ ርግብ ተመስሎ መጣና በጌታችንነ በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በራሱ ላይ ተቀመጠ፡፡ ከዚያም አንድ ታላቅ ድምፅ ከሰማይ ውስጥ ተሰማ፡፡ እንዲህ የሚል “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፡፡”

ልጆችዬ ዛሬም እኛ ክርስቲያኖች ከጥር ዐሥር ጀምረን ነጭ የሀገር ልብስ ለብሰን ቅዱሱን ታቦት አጅበን እየዘመርን፣ እልል እያልን የምንዘምረውና በጸበል የምንጠመቀው በመስቀልም በአባቶቻችን ካህናት የምንባረከው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ በሁሉም ቤተ ክርስቲያን ያሉት ታቦታት ጥር አሥር ቀን ከየቤተ ክርስቲያኑ ወጥተው ወደ ጥምቀተ ባሕር /ጸበሉ ቦታ/ ሄደው እየተዘመረ፣ እየተጸለየ በምስጋና ይታደራል፡፡ በነጋታው ጥር 11 በጠዋት ውኃው ተባርኮ ጸበል ይሆናል፡፡ በሥፍራው የተሰበሰቡትን ክርስቲያኖች ሁሉንም በጸበሉ እየረጩ ያጠምቋቸዋል፡፡ በመጨረሻም የእግዚአብሔር ማደሪያ ቅዱስ ታቦቱ በካህናቱ ዝማሬ በምእመናን እልልታ ታጅቦ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመለሳል፡፡

አሁን ደግሞ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፡

  1. ቅዱስ ዮሐንስ የሚኖረው በየት ነበር?
  • ጌታችን መድኃኒጻችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው የት ነው?
  • ኢየሱስ ክርስቶስን ያጠመቀው ማን ነው?
  • ቅዱስ ዮሐንስ ያጠመቃቸው ወገኖች እነማን ናቸው?

ልጆችዬ ከመሰናበቴ በፊት ለዛሬ የምታነቡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ልንገራችሁ፡፡ ይኸውም የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ሦስት ነው፡፡ ስለተከታተላችሁኝ የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡ እመቤታችን ድንግል ማርያም ታሳድግልኝ፡ ፡ መልካም የጥምቀት በዓል ይሁንላችሁ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለደነ ዳግመ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ፣ ዳግመኛም ከውሃነ ከመንፈስ ወለደን።

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ