የዳውሮ ኮንታ ሀገረ ስብከት የአብነት ትምህርት ቤት ግንባታ ፕሮጀክት አሕጽሮት

የዳውሮ ኮንታ ሀገረ ስብከት የአብነት ትምህርት ቤት ግንባታ ፕሮጀክት አሕጽሮት

የፕሮጀክቱ ቦታ ፦ የዳው ኮንታ ሀገረ ስብከት ስርስድስት ወረዳ ቤተክህነቶች ሲገኙ የአብነት ትምህርት ቤት ግንባታው የሚካሄደው የሃገረስብከቱ መቀመጫ በሆነው በተርጫ ከተማ ላይ በሚገኘው በአቡነ ተክለሃይማኖት ደብር ላይ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ ማቋቋም ያስፈለገበት ምክንያት፦ ሀገረስብከቱ በመናፍቃን የተከበበ እና ጥቂት የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታዮች ብቻ ያሉበት ከመሆኑም በላይ አገልጋይ ካህናት ሆኑ ዲያቆናት የሚመጡት ከሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በመሆኑ፣ እነዚህ አገልጋዮች ከአካባቢው ነዋሪ ጋር በቋንቋ መግባባት ስለማይችሉ ከቤተክርስቲያን አገልግሎት ውጪ የሃይማኖት ትምህርት መስጠት ባለ መቻላቸው ምዕመኑን ለማስተማር እና ሃይማኖቱን ጠብቆ እንዲኖር ማድረግ አልተቻለም፡፡ ስለዚህ በሀገረ ስብከቱ ላይ የሚቋቋመው የአብነት ትምህርት ቤት ተማሪዎቹ ተመልምለው የሚገቡት ከሁሉም ወረዳ ቤተክህነቶች ስለሚሆን ተምረው ሲጨርሱም ወደ መጡበት አካባቢ ተመልሰው ምዕመኑን በቅስና እና በድቁና ከማገልገላቸውም በላይ በሚገባው ቋንቋ የወንጌል ትምህርት ሊሰጡት ስለሚችሉ በሃይማኖቱ ፀንቶ እንዲኖር የሚኖራቸው አስተዋፅዖ ከፍተኛ ይሆናል፡፡

የፕሮጀክቱ ግብ ፦ በሀገረስብከቱ የአብነት ትምህርት ቤት ግንባታ በማካሄድ የቤተክርስቲያን ካህናት እና ዲያቆናት በማፍራት የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት እንዲከፈቱ እና መንፈሳዊ አገልግሎት በተጠናከረ መልኩ እንዲሰጡ ማድረግ ሲሆን፤ የፕሮጀክቱ ዓላማ በየሁለት ዓመት ግብረ ድቁና ተምረው የሚያጠናቅቁ 40 የአብነት ትምህርት ተማሪዎችን ተቀብሎ የአብነት ትምህርት ማስተማር የሚያስችል የአብነት ትምህርት ቤት መገንባት እና ከአብነት ትምህርቱ ጎን ለጎን መሰረታዊ ትምህርተ ሐይማኖት ትምህርት እና የስብከት ዘዴን ማግኘት እንዲችሉ ማድረግ ነው፡፡

የአብነት ትምህርት ቤቱ ግንባታ የሚያጠቃልለው፦ ለ40 ተማሪዎች የሚሆን አንድ ጉባኤ ቤት፤ አምስት የተማሪዎች ማደሪያ፣ መመገቢያ አዳራሽ፣ ማብሰያ ቤት ፣ የመጸዳጃ እና ገላ መታጠቢያ ቤቶችን ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ፕሮጀክቱ የውስጥ ቁሳቁስ ግዢንም ያጠቃልላል፡፡

ለፕሮጀክቱ የገንዘብ ምንጭ ፦ በአውሮጳ የሚገኙ ምእመናን፤ የአብነት ትምህርት ቤቱ ግንባታ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን፣ የሚፈጀውም የገንዘብ  ብር 2,500,000 ብር (62, 500 EUR ) ይሆናል፡፡

የፕሮጀክቱ አስፈፃሚ ፦በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት እና መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት ማስተባበሪያ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ ከተጠናቀቀ በኃላ በባለቤትነት ተረክቦ ለተፈለገው አገልግሎት እንዲውል የሚያደርገው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የዳውሮ ኮንታ ሀገረ ስብከት ይሆናል፡፡

ፕሮጀክቱ በታለመለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ተባባሪ የሚሆኑት፤ የፕሮጀክቱ ባለቤት የሆነው የዳውሮ ኮንታ ሀገረ ስብከት፣ የአካባቢው ወረዳ ቤተክህነት፣ በማኅበረ ቅዱሳን የተርጫ ማዕከል፣ በአውሮጳ የሚኖሩ በጎ አድራጊ ምዕመናን እና የተለያዩ መንፈሳዊ ማኅበራት ይሆናሉ፡፡

ለገዳማት እና አብነት ት/ቤቶች ድጋፉ ለማድረግ የሚከተሉትን ዘዴዎች ይጠቀሙ  :-

 1. በቀጥታ በባንክ ወደ ማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማእከል ሂሳብ በማስተላለፍ

Mahibere Kidusan In Europa

BAN : DE14 3704 0044 0307 803 700

BIC : COBADEFF

Reason : Donation gedamate code 001

Commercial Bank

Bank address : Maternusstr.5; 50996 Cologne, Germany

 

 1. ፔይ ፓልን በመጠቀም ወደ አውሮፓ ማዕከል ባንክ አካውንት በማስተላለፍ።

ለተጨማሪ መረጃ እና ጥያቄ በ eu.monasteries@eotcmk.org ይጻፉልን።

የቴክኖሎጂ ውጤቶች ና የሉላዊነት ጫና በልጆች አስተዳደግ

በላቸው ጨከነ ተስፋ (ዶ/ር)

መግቢያ

“ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው። ” (መዝ፻፳፮፥፫)  ከእግዚአብሔር የተሰጡንን በረከት በሚገባው ተንከባክቦ፣ አስተምሮ  እና ጠብቆ ማሳደግ የወላጆች ትልቅ ሥራ ነው። ቅዱስ መጽሐፍ “እንግዲህ እነዚህን ቃሎች በልባችሁና በነፍሳችሁ አኑሩ። ልጆቻችሁንም አስተምሯቸው። በቤትህም ስትቀመጥ በመንገድም ስትሄድ ስትተኛም ስትነሳም አጫውቷቸው። እርሷንም እንዲሰጣቸው እግዚአብሔር ለአባቶቻችሁ በማለላቸው ምድር እንደ ሰማይ ዘመን በምድር ላይ ዘመናችሁ የልጆቻችሁም ዘመን ይረዝም ዘንድ በቤትህ መቃኖችና በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው።” (ዘዳ 11፥18) እንዳለ ልጆችን ጠብቆ እና ተንከባክቦ ማሳደግ የወላጆች ትልቁ ድርሻ ነው።

ዛሬ በተለይ  ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖሩ ወላጆች ለሚኖሩበት ሀገር ባህል እና ሕግ እንግዳ መሆን፣ ከልጆች ጋር የመግባቢያ ቋንቋ ችግር፣ ከቤተ ዘመድ መራቅ፣ የሥራ ጫና እና የጊዜ እጥረት፣ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጫና እና ዕለት ዕለት ቅድስት ቤተክርስቲያን በቅርባቸው እንደልብ ስለማያገኙ  የልጆችን አስተዳደግ የበለጠ ውስብስብ አድርጎታል። በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ዘመኑን ዋጅቶ ልጆችን በሃይማኖትና በግብረ ገብ ትምህርት ለማሳደግ ከወላጆች ብዙ ይጠበቃል። በዚህ አጭር ጽሑፍ  የቴክኖሎጂ ውጤቶች በልጆች አስተዳደግ ላይ የፈጠሩትን  ችግሮች እና የመፍቴሔ ሐሳቦች ለውላጆች ግንዛቤ ከመፍጠረ አንጻር ቀረበዋል።

የዘመኑን የልጆች አስተዳደግ ውስብስብና አስቸጋሪ ካደረጉት ነገሮች አንዱ የመረጃ ቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ በቴሌቪዥን እና በኢንተርኔት የሚተላለፉ መልክቶች ናቸው። ቴክኖሎጂ የራቀውን በማቅረብ የተወሳሰበውን በማቅለል ሕይወትን የተሻለች ማድረጉ አሌ የማይባል ቢሆንም የጎንዮሽ ውጤቱም ደግሞ በተለይ ለልጆች የዚያኑ ያህል የከፋ ነው። በአግባቡ እስካልተጠቀምንበት ድረስ። ክፉና ደጉን በአግባቡ ባለየው በልጆች አዕምሮ ላይ የሚያሳርፈው ተጽዕኖ ደግሞ የከፋ ነው። በአዳጊነት የዕድሜ ክልል የሚገኙ ተማሪዎችን ነፍስ ካወቁ በኋላ ከትምህርታቸው የሚያዘናጋቸው፣ ከእንቅልፍ፣ ከማኅበራዊ መስተጋብር ያራራቀቸው፣ ቁምነገር እንዳይሠሩ የሚያዘናጋቸው አየሆነ ነው። የተክኖሎጂ ውጤቶች ብለን የምንመድባቸው የቪዲዮ ጌም መጫወት፣  ፊልሞች ማየት፣ የቴሌቪዥን መረሐ ግብሮች፣ ኢንተርኔት በተለይም የፌስ ቡክ ቻት፣ ዘፈን ማድመጥ፣ የተለያዩ ጨዋታዎች መመልከት የመሳሰሉት ናቸው።

የአንተርኔት እና የቴሌቪዥን ለልጆች ያለው ጉዳት  

ልጆች ከሕፃንነት ጀምሮ አስቸጋሪ ሱስ የሚሆንባቸው የቴሌቪዥን ሥርጭት በተለይም ፊልም መመልከት ነው። ዕድሜ ሳይለዩ የሚለቀቁ የቴሌቪዥን ሥርጭቶችን ያለ ከልካይ የሚመለከቱ ሕፃናት ከፍተኛ ተፅዕኖ ይፈጠርባቸዋል። የተፅዕኖው ውጤትም አፍራሽ ወይም ገንቢ ሊሆን ይችላል። በየትኛውም የዕድሜ ክልል ያሉ ልጆች የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ያለ ገደብ እንዲመለከቱ መፍቀድ ወይም ፍጹም ቴሌቪዥን እንዳይመለከቱ መከልከል ተገቢ አይደለም። ሁለቱም ጽንፎች የየራሳቸው የጎንዮሽ/ጎጂ/ ውጤት አላቸው።

ልጆች በኮምፒውተሮቻቸው እና በስልካቸው ለእነርሱ የማያስፈልጉ ነገሮች ይደርሳቸዋል ከማያውቁት ጓደኛ ወይም ከማያውቁት ሰው ሊደርሳቸው ይችላል። ሌላው የኢንተርኔት ችግር ልጆች በሳይበር አባላጊዎች (አማጋጮች) የተጋለጡ ይሆናሉ። ድምጻቸውን በመቅረጽ ለሌሎች አዳኞች ያስተላልፋሉ፤ ይሸጣሉ። ልጆችን የእነርሱ ባሪዎች በመሆን የተጠየቁትን በሙሉ እንዲፈጽሙ አለበለዘያ የያዙትን ምስል እና ድምፅ ለወላጅ፣ ለጓደኛ አና ለትምህርት ቤት አንደሚሰጡ በመግለጽ ያስፈራራሉ። ልጆችም በዚህ ምክንያት ራሳቸውን እስከ ማጥፋት፣ ለጭንቀት እና ለአደንዛዥ እፅች መጋለጥ ይደርሳሉ። ልጆች በሳይበር ዝሙት እስከ መፈጸም ይደርሳሉ። የተለያዩ ማስተዋቂያዎችን ያያሉ፤ ያለ አቅማቸው የተለያዩ ነገሮችን ይገዛሉ። አላስፈላጊ የሆኑ ፋይሎች፣ ቫይረሶች ወደ ኮምፒውተር ሊወርዱ ይችላሉ።

በዘረፉ ጥናት ያደረጉ ምሁራን አብዛኛ ጊዚያቸውን በእንተርኔት እና በቴሌቪዥን የሚያሳልፉ ልጆች የሚከተሉት ችግሮች ያጋጥሟቸዋል ይሉናል፦

 • የጥናት ጊዜያቸውን በመሻማት ትምህርታቸው ላይ ጫና ይፈጥራል። ከአሰቡበት ሳይደረሱ ሊቀሩ ይችላሉ።
 • በሚዲያ የሚያዩትን እና በንግድ የሚተዋወቁ ነገሮችን በማየት አቅማቸው ከሚፈቅደው በላይ ለማግኘት ይመኛሉ፤ በብልጭልጭ ነገር እንዲታለሉ ይሆናሉ።
 • በፊልም የሚያቸውን ወንጀሎች እየተለማመዱ ወደ ማከናውን ይመጣሉ (ለምሳሌ ስርቆት፣ ሃሺሽ መጠቀም፣ መደባደብ) በሚዲያ የሚተዋወቁ የመንገድ ላይ ምግቦች (fast foods) በማየት ለምግቦች ልዩ ፍቅር ይኖርቸዋል። ይህም ሰውነታቸው ከመጠን በላይ እንዲሆን ስለሚያደርግ የጤና መታወክ ያስከትልባቸዋል።
 • አብዛኛውን ጊዜያቸውን ብቻቸውን ከሚዲያ ጋር ስለሚያሳልፉ ከቤተሰብ እና ከማኅበርሰቡ ጋር እንዳይገናኙ በማድርግ ምናባዊ (virtual) ዓለምን እንዲኖሩ የብችኝነትን/ግለኝነት/ ሕይወት ያለማምዳል።
 • የንባብ ክህሎታቸው ዝቅተኛ ይሆናል፤ ከንባብ ከሚገኘው በረከትም ተቋዳሽ አይሆኑም።
 • አካላዊ እንቅስቃሴ ሳያደርጉ ቁጭ ብለው ስለሚውሉ ጥንካሬ አይኖራቸውም።
 • የትኩረት አቅማቸው ዝቅተኛ ይሆናል፣ ለፈጠራና ለምርምር ጊዜ አይኖራቸውም።
 • በዕድሜያቸው መጫወት ያለባቸውን ያህል አይጫወቱም። ከእህት እና ወንድማቸው ከጓደኞቻቸው ጋር የሚጫወቱበት ጊዜ አያገኙም።
 • ሕይወትን በቴሌቪዥን መስኮት ሽው እልም ስትል እያዩ ቀላል አድርገው ያስቧትና ሲጋፈጧት ከባድ ትሆንባቸዋለች።
 • ልጆች ብዙ ክሂሎችን የሚያዳብሩት በማየት ሳይሆን በመሥራት ነውና የሥራ ጊዜያቸውን ይሻማሉ።
 • ከአካባቢያቸው ጋር የሚኖራቸው መስተጋብር የተወሰነና ዝቅተኛ ይሆናል። አካባቢያቸውንም በደንብ እንዳያውቁት እንቅፋት ይሆንባቸዋል።
 • እየበሉ ሳይንቀሳቀሱ ስለሚቆዩ በዘመኑ አሳሳቢ ለሆነው ውፍረት (obesity) ይጋለጣሉ፤ በዚህ ሳቢያ ለሚከሰቱ የጤና ችግሮች ሊጋለጡ ይችላሉ።
 • ለወደፊት ለጾታ ግንኑኝነት ያለቸው አመለካከት የተዛባ ይሆናሉ፤ ተጨባጩን ዓለም ሳይሆን ሰው ሠራሹን ዓለም ናፋቂ ይሆናሉ፤ ሁል ጊዜ አዲስ ነገር ናፋቂዎች ይሆናሉ።
 • የሥነ ልቦና ጫና ያደርግባቸዋል፤ በትምህርት ቤት አና በቤተሰብ ያለው ግንኙነት የሻከረ ነው፤ ብቸኝነት ያጠቃቸዋል። ራሳቸውን እሰከ ማጥፋት ይደርሳሉ። ሱስ ስለሚሆንባቸው ሁልጊዜ ያያሉ። ሌሎችንም ወደ እዚህ ይመራሉ።
 • እራሳቸውን በደንብ ስለማይጠብቁ በመልካቸው፣ በአለባበሳቸው እና በቤተሰባቸው ማንጓጠጥ (bullying) ይደርስባቸዋል።

የመርጃ ቴክኖሎጂውን ለልጆቻን አንዴት አንጠቀም?

በአደጉ ሀገሮች ይህን ችግር ለመቆጣጠር በመንግሥት፣ የኢንተርኔት መስመር አከራዮች እና በትምህርት ቤት የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ። ወላጆችም በቤት የወላጅ መቆጣጠሪያ (Parental control) ይጠቀማሉ። ለቤተሰቡ ሁሉ የየራሱ መግቢያ እና ማለፊያ ይኖረዋል፤ ወላጅ ብቻ የሚጠቀምባቸውን ፋይሎች እና ሌሎች መረጃዎችን ልጆች እንዳያይዋቸው ይረዳል። ወላጅ የሚፈልጉትን ድረ ገጾች ብቻ መምረጥ እና ሌሎችን በኮምፒውተሩ እንዳይከፍቱ ማድረግ ይችላል። ወይም ወላጅ መክፈት የሌለባቸውን ድረ ገጾች ወሳኝ ቃላቶችን በመጠቀም መከላከል ይቻላል። የተወሰኑት ሶፍቴዎሮች ልጆች የድምፅ እና የምስል መልእክት ኮምፒዊተሮችን ተጠቅመው እንዳያሰተላልፉ ይረዳል። የልጆችን አጠቃላይ በኢንተርኔት ላይ ያላቸውን እንቅስቃሴ ሪፖርት ያደርጋል። ምን ድረ ገጽ እንደጎበኙ፣ ለምን ያህል ሰዓት፣ ከማን ጋር አንደተገናኙ ያሳያል። ወላጆች ለልጆቻቸው ለምን ያህል ጊዜ ኮምፒውተር ላይ መቀመጥ እንዳለባቸው ገደብ ለማድረግ ይረዳል፤ ልጆች ከተፈቀደላቸው በላይ ሲጠቀሙ ለወላጆች መልእክት ይሰጣል። እነዚህ ሁሉ መፍትሔዎች ችግሩን ቢያቀሉትም ፈጽሞ እንዳይከሰት ማድረግ አልቻሉም።

ከእነዚህ መፍትሔዎች ጋር የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ወላጆች ከልጆች ጋር የቀረበ ግንኙነት እንዲኖራቸው ማድረግ፤ ምንም ከወላጅ የተደበቀ ነገር እንዳይኖር ማድረግ ያስፈልጋል። ልጆችን ከወላጅ በላይ ማንም ሊረዳቸው እና ሊግባባቸው አይችልም። የተከሰቱትን ችግሮች ሁሉ ለመፍታት የተከሰተውን ነገር ልጆች በግልጽነት እንዲያወያዩን ማድረግ ከዚህ ከኢንተርኔት አጠቃቀም ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት መፍትሔ ይሆናል። ልጆች ስለሚነግሩን ነገር ለመረዳት ስለ ኢንፎርሜሺን ቴክኖሎጂ መሠረታዊ እውቀት ሊኖረን ይገባል። ልጆች 13 (አሥራ ሦስት) ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ሶሻል ሚድያ (ፌስ ቡክ፣ ትዊተር) መጠቀም እንደማይችሉ ማስረዳት። ልጆች ከእኛ በላይ እንዲሚያውቁ ሆነው ሊሰማቸው አይገባም። ወላጆች ልጆች ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ላይ ሳይሆን ቴክኖሎጀውን በመሥራት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ልጆችን በተላያየ ቦታ የሚዘጋጁ ሳይንስ ነክ የሆኑ ዓውደ ርዕይዎችን እንዲዩ  ማደረግ ይገባል።

በአግባቡ እየመረጡ የልጆች ተሌቪዥን ሥርጭት እና የተመረጡ ፊልሞች እንዲመለከቱ ቢደረግ በርካታ ቁምነገሮች ሊቀስሙ፣ መልካም የሚባል ማኅበራዊ፣ ሞራላዊ እሴቶችን ሊያዳብሩ ይችላሉ። ውጤታማ የቴሌቪዥን አጠቃቀም የሚከተሉትን ተግባራት ይጠይቃል:-

 • ልጆች ምን ማየት እንዳለባቸው መለየት (አመፅ፣ ድብደባ፣ የአዋቂዎችን ጉዳይ እንዳይመለከቱ መጠንቀቅ)።
 • ቤተሰባዊ ጉዳዮች ላይ እና በሕፃናት ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ እና የሚያተኩሩ ዝግጅቶችን እንዲመለከቱ ማበረታት።
 • ተፈጥሮን ማወቅ፣ ማድነቅ የሚችሉባቸውን፣ ተፈጥሮን የሚያስቃኙ ዝግጅቶችን እንዲመለከቱ ማገዝ።
 • በቀን ውስጥ ቴሌቪዥን የሚመለከቱበትን የሰዓት ገደብ መወሰን፣ ጥሩ ነገር ሲሠሩ እንደ ሽልማት እንዲሆናቸው ማድረግ።
 • አብሮ እየተመለከቱ ስለሚተላለፈው ነገር አንዳንድ ጥያቄዎችን በማቅረብ የሚያዩትን ነገር መረዳታቸውን መገምገም።
 • በሚያዩት ነገር እና በእውኑ ዓለም መካከል ያለውን ልዩነት ማስረዳት።
 • ልጆች የግል መረጃዎችን (ኢሜይል፣ ስልክ፣ የቤት አዳራሻ) ለማያውቁት ሰው መቼም መስጠት የለባቸውም።
 • መቼም ልጆች የግል ማለፊያዎችን (Password) ለማንም መስጠት የለባቸውም። ማለፊያዎችን (Password) በየጊዜው መቀየር መቻል አለባቸው።
 • በሶሻል ሚድያ የሚለቋቸው ጽሑፎች፣ ፎቶግራፎች ሰውን የሚያናዳዱ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ፤ የሌሎችንም ፎቶግራፍ ባሌቤቱን ሳይስፈቅዱ አለማስቀመጥ።
 • ከማን እንደተላከ የማይታወቅ የኢሜይል መልእክት ልጆች መክፈት የለባቸውም።
 • የገንዘብ ነክ መረጃዎችን ልጆች ከወላጆች ጋር ብቻ እንዲጠቀሙ ማድረግ ለባንኮች ክፍያ ለመጠቀም ልጆች የማያውቁት ተጨማሪ ማለፊያ መጠቀም።
 • በኢንተርኔት ጓደኝነት የሚጠይቁ ሰዎችን የሚያውቋቸውን ብቻ ማድረግ።
 • ልጆች በኢንተርኔት ብቻ ጊዜያቸውን እንዳያጠፉ ሌሎች በኮምፒውተር የሚሠሩ ነግሮችን ማዘጋጀት።
 • ሰለ ቤተሰብእ የእረፍት ጉዞ፣ በቤት ስለሚዘጋጅ ዝግጅት፣ አብረው ሰለሚኖሩ ስዎች መረጃ በሶሻል ሚዲያ ማውጣት የለባቸውም።

ማጠቃለያ

ለልጆች የሰውነት ቅመምን፣ የሕይወትን ጣዕምና ትርጉምን እንዲሁም የስኬትን መንገድ የማመላከት ሚና በቀዳሚነት የወላጅ ድርሻ መሆኑን ወላጆችም፣ ልጆችም፣ ባለሙያችም የሚያሰምሩበት ጉዳይ ነው።

በአጠቃላይ ልጆች በተጠመዱባችው ሱሶች አማካይነት ጸያፍ ንግግሮችን፣ ደባል ሱሶችን፣ አመፅን፣ ልቅ ወሲባዊ  ድርጊቶችን፣ ኢ-ሥነ ምግባራዊ ተግባሮችን ይማራሉ፤ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ልማዶች ወረዋቸው በዕድሜያቸው ሊሠሯቸው የሚገቧቸውን ሥራዎች እንዳይሠሩ ይከለክሏቸዋል። ከመደበኛው ትምህርታችው ያዘናጋቸዋል። እነዚህን የቴክኖሎጂ አፍራሽ ተፅዕኖዎች ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ባይቻልም መቀነስ ግን ይቻላል። ወላጆች ልጆቻቸውን ከነዚህ ነገሮች ለመታደግ ጠንካራ ሥራ ይጠበቅባቸዋል፤ በጊዜያቸው በሕይወታቸው በማንነታቸው እና በውጤታቸው ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ውጤት ከግምት በማስገባት የኤሌክትሮኒክስ አጠቃቀማቸው ላይ ገደብ ማበጀት፣ ልምድ ማካፈል፣ ዕድሜያቸውን ያላገናዘቡ መልእክቶችን እንዳይታደሙ መጠንቀቅ፣ ከሚመለከቷቸው ነገሮች ጠቃሚ ቁም ነገሮችን ብቻ እየመረጡ እንዲጠቀሙ ግንዛቤያቸውን ማዳበር፣ የራሳቸውን ማንነትና የማኅበረሰባቸውን ማኅበራዊ እሴቶች እንዲያውቁ ማድረግ፣ ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ መከታተል፣ ትምህርታቸውን በአግባቡ መከታተላቸውን መገምገም ወዘተ የወላጆች ሓላፊነት ሊሆን ይገባዋል።

* ፈሰሴ ገብረሐና ፣ በላቸው ጨከነ – የልጆች አስተዳደግ በዚህ ዘመን ተግዳሮቶች እና መፍትሔዎች። ሎንዶን ፳፻፮ ዓ.ም. ከታተመው መጽሐፍ ለዚህ መጽሔት የተዘጋጀ
** ይህ ጽሑፍ በኢ/ኦ/ተ/ቤት ክርስቲያን በሰ/ምዕራብ አውሮፓ ሀገር ስብከት በፊንላንድ የሄልሲንኪ ደበረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በ፳፻፲ ዓ.ም. ባሳተመው መጽሔት ላይ የወጣ ነው።

ሆሣዕና

በዲ/ን ብሩክ አሸናፊ

መጋቢት 23 ቀን 2010 ዓ.ም.

ሆሣዕና ማለት መድኃኒት ማለት ነው። ሆሣዕና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ እና በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ከሕዝቡም ብዙዎች ልብሳቸውንና የዘንባባ ዝንጣፊ በመንገድ እያነጠፉለት የሚቀድሙትም የሚከተሉትም ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ሥም የሚመጣ ቡሩክ ነው ሆሣዕና በአርያም እያሉ እያመሰገኑት ወደ ኢየሩሳሌም የገባበትና የለዋጮችን ገበታዎችና የርግብ ሻጮችን ወንበሮች ገልብጦ ቤተ መቅደሱን ያነጻበት እና ለአምልኮ ብቻ የቀደሰበት በዓል ነው።

ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ሊገባ በቀረበ ጊዜ በደብረ ዘይት አጠገብ ከምትገኝ ቤተ ፋጌ ሲደርስ ሰው ሁሉ ከማዕሠረ ኃጢአት የሚፈታበት ጊዜ እንደደረሰ ለማጠየቅ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ በዚያም አህያ ከውርንጫዋ ጋር ታስራ ታገኛላችሁ ፤ ፈታችሁ አምጡልኝ ፤ ማንም አንዳች ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ ሲል ላካቸው። መንደር የሲዖል ፣ አህያይቱና ውርንጫይቱ የአዳምና የልጆቹ ፣ በመንደር መታሰራቸው አዳምና ልጆቹ በመርገመ ሥጋ በመርገመ ነፍስ ተይዘው በሲዖል በባርነት መኖራቸውንና ጌታችንም የሲዖል ባርነት አስወግዶ ነጻነትን የሚያድልበት ጊዜ እንደቀረበ ያጠይቃል። ዛሬም እኛ ልጆቹ በማዕሰረ ኃጢአት ተይዘን ከእርሱ ስንርቅ ከማዕሰረ ኃጢአት ፈትተው ወደርሱ የሚያቀርቡንን ካህናትን ሰጥቶናል። Read more

ዐቢይ ጾም

በታምራት ኃይሉ

የካቲት 5 ቀን 2010 ዓ.ም.

ጾም ማለት ሰውነትን ከሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ መከልከል፣ ለሥጋ የሚመቸውን ነገር መተው ማለት ነዉ፡፡ ጌታችን መጾም ሳያስፈልገው የጾመው በጾም መሣሪያነት ዲያቢሎስን ድል ታደርጋላችሁ ሲለን ነው፡፡  እርሱ ድል አድርጎታል ካልጾሙ ካልጸለዩ ሰይጣንን ድል ማድረግ እንደማይቻል ጌታ አስተምሮናል፡፡ ጾም ፊትን ወደ እግዚአብሔር ማቅናት እንደሆነ በሰብአ ነነዌ ታውቋል እነዚህ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር የተመለሱት በጾም ነውና፡፡ ኃጢያታቸዉ እጅጉን ገዝፎ ቅድመ እግዚአብሔር ስለደረሰ የጌትነቱ ቁጣ አስቀድሞ ከመምጣቱ በፊት ንስሐ እንዲገቡ መሐሪ እግዚአብሔር ነብዩ ዮናስን ላከላቸዉ፡፡ ህዝቡም የነብዩ ዮናስን ስብከት ሰምነተው በክፉ ሥራቸዉ ተጸጽተዉ ከሊሒቅ እስከ ደቂቅ ማቅ ለብሰው ጾሙ፣ ሕፃናትና  እንስሳትም የንስሀቸዉ ተካፋይ እንዲሆኑ አደረጉ፡፡ በዚህ ግዜ የፍጥረቱን መዳን እንጂ መጥፋቱን የማይወድ እግዚአብሔር ቁጣዉን በትዕግስት መዓቱን በምሕረት መልሶ በይቅርታ ጎበኛቸው ከተቃታዉ መቅሠፍት አዳናቸዉ (ዮና  ፫ ፡ ፭-፲ )፡፡ ወደ እግዚአብሔር በጾም በጸሎት የተመለሱ ድኅነትን እንዳገኙ ሁሉ ያልተመለሱ ደግሞ ጠፍተዋል፡፡ ለምሳሌ ሰብአ ሰዶም ገሞራ እንደ ነነዌ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ባለመመለሳቸዉ እሳት ከሰማይ ወርዶ አቃጥሎ አጥፍቶአቸዋል (ዘፍ ፲፱፡፳፫)፡፡  Read more

ዕረፍተ ሶልያና

በዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ 

ጥር  21 ቀን 2010 ዓ.ም.

 

የቤተክርስቲያናችን ዓይን ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ለአምልኮ መቅረዝ ለምስጋና ማኅቶት በሆነው የድጓ ድርሰቱ የእመቤታችንን የከበረ ዕረፍት ከዘመነ አስተርእዮ ምስጢር ጋር እያዛመደ እንዲህ አስፍሮታል።

∽†∽ “ጊዜ ዕረፍታ ለሶልያና፣ ወረደ ወልድ እም ዲበ ልዕልና፣ ጠሊሳነ ንግሥ ሶቤሃ ከደና ” ∽†∽

ድጓ: መነሻው “ድግ” ነው የሚሉ ዓይናማ ሊቃውንት “ድጋ ለቤተክርስቲያን” ብለው ድርሰቱ የተዋህዶ መደገፊያ መሆኑን ይነግሩናል። ምንጩን  ደግደገ ካለው አንስተው ድግዱግ በሚለው ደቃቅ ለማለት ስበው ረቂቅ ማለትም ነው ይላሉ ፤ እንደ ሊቃውንቱ ሀተታ ከጽሕፈቱ ረቂቅነት ከምልክቱ ብዛት የተነሣ የተሰጠው መጠሪያ ነው። በሌላ አገባብም በዘይቤው የዓመቱ መዝሙራት ተወጣጥተው ተሰብስበው ይገኙበታልና ድጓ እስትጉቡእ ወይም ስብስብ ማለትም ይሆናል።

ሊቁ በዚህ የድጓ ድርሰቱ፦ የነቢያቱን የትንቢት ማረፊያ፣ የሐዋርያቱን የስብከት መነሻ፣ የነገረ ድኅነት ጥልቅ ማብራሪያ፣ የሆነውን ነገረ ማርያምን በልዩ መንገድ ያስረዳናል። በተለይም የሥላሴ ማደሪያ የቤተ ክርስቲያን አንደበት ለሥጋ ለባሽ ሁሉ ትምክኅት የሆነች እመቤታችን በዘመነ አስተርእዮ በጥር ፳፩ ቀን የተከናወነው የከበረ “ዕረፍተ ሶልያና” በምን ክስተት እንዳለፈ እንዳንዘነጋው ሁሉን ከሚያስብ ከማይዘነጋ ልጇ እንድታማልደን እየተማጸነ ጭምር አብራርቶ ይዘግባል። Read more

በዓለ ልደቱ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ

በበኩረ ፍሥሐ ቀሲስ ኃይለኢየሱስ ተመስገን

ታኅሣሥ 28 ቀን 2010 ዓ.ም.

“እስመ ናሁ እዜንወክሙ ዓቢየ ዜና ዘይከውን ፍሥሐ ለክሙ ወለኩሉ ሕዝብ “ሉቃ ፪ ፥፲

ለወልደ እግዚአብሔር ሁለት ልደታት እንዳሉት እናምን ዘንድ ይገባናል። አንዱ ከዘመን ሁሉ አስቀድሞ ከእግዚአብሔር አብ የተወለደው ልደት ነው። ሁለተኛውም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በኋላ ዘመን የተወለደው ልደት ነው፡፡ሃይማኖተ አበው ዘባስልዮስ ምዕራፍ ፴፬ ቁጥር ፮ ክፍል ፭። Read more

“ወይንሳዕ መስቀለ ሞቱ ወይትልወኒ – የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ይከተለኝ”

በዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ

መስከረም 16 ቀን 2010 ዓ.ም.

ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና በቃል መነገሩ፣ በኅሊና መዘከሩ፣ በሰው ልብ መታሰቡ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት መዘገቡ ከፍ ይበልና፣ ጌታችንንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛ ልጆቹ ፈቃዱን እያደረግን እንድንኖርና እርሱም ከመልካም ምግባራችንና ከበጎ ትሩፋታችን ብቻ የተነሳ ፍጹማን እንደማንሆን ያውቃልና፣ ከማያልቅ ልግስናው ከማይጓደል ምሕረቱ ዘመናትን እየመጸወተን ደስ የሚሰኝበትን ለእኛ እያደረገ በቸርነቱ ያኖረናል:: ከእርሱና ከዓላማው ጋር ጸንተን እንድንኖርም እንዲህ ሲል በቅዱስ ወንጌል አዝዞናል:: “ዘይፈቅድ ይትልወኒ ይጽላዕ ነፍሶ ያጥብዕ ወይንሳዕ መስቀለ ሞቱ ወይትልወኒ (እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ) ወምንተ ይበቁዖ ለሰብእ ለእመ ኩሎ ዓለመ ረብሐ ወነፍሶ ኃጉለ (ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል?)” (ማቴ. 16:24-26)።

Read more

ጰራቅሊጦስ

በቀሲስ ኃይለኢየሱስ ተመስገን

ግንቦት 26 ቀን 2009 ዓ.ም.

በቅዳሴ ጸሎት ካህናት ከሚጸልዩት ጸሎት ውስጥ “ወቡሩክ መንፈስ ቅዱስ ጰራቅሊጦስ መጽንዒ ወመንጽሔ ኩልነ” የሚል እናገኛለን ሁላችንን የሚያነጻ፣ የሚያጸና መንፈስ ቅዱስም ቡሩክ ነው ማለት ነው። በዚህ ጸሎት ላይ ጰራቅሊጦስ የሚለው ቃል ከሦስቱ አካላት አንዱ ለኾነው ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መጠሪያ እንደሆነና የሚያነጻ፣ የሚያጸና መሆኑን ይገልጣል። Read more

ቀርቦሙ እግዚእ ኢየሱስ ወሖረ ምስሌሆሙ (ጉዞ ከእግዚአብሔር ጋር) ሉቃስ 24÷13­-45

በቀሲስ ኃይለኢየሱስ ተመስገን

ሚያዚያ 21 ቀን 2009 ዓ.ም.

ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን ……………. በዓቢይ ኃይል ወሥልጣን

አሰሮ ለሰይጣን …………………………..አግአዞ ለአዳም

ሰላም ……………………………………… እም ይእዜሰ

ኮነ…………………………………………..ፍሥሐ ወሰላም

“ክርስቶስ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ ፤ ዲያብሎስን አሰረው አዳምን ነጻ አወጣው ፤ ሰላም ከዛሬ ጀምሮ ሰላም ሆነ”

13.ወይእተ ዕለእንዘ የሐውሩ ክልኤቱ እምውስቴቶሙ ሀገረ እንተ ርኅቅት እምኢየሩሳሌም መጠነ ስሳ ምዕራፍ እንተ ስማ ኤማኁስ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በኵር ሆኖ ከሙታን መካከል በተነሣበት ዕለት በሰንበተ ክርስቲያን ከመቶ ሃያዎቹ የክርስቶስ ቤተሰቦች ውስጥ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከኢየሩሳሌም 60 ምዕራፍ ያህል ወደምትርቀው ኤማኁስ ወደምትባለው መንደር ሲሄዱ ስላጋጠማቸው ወንጌል የሚነግረንን አባቶቻችን ያስተማሩንን እንመለከታለን።

ቅዱስ ሉቃስ በጻፈው ወንጌል የተጠቀሰው የቀልዮጳ ስም ብቻ በመሆኑ(ሉቃስ 24÷18) ሁለቱ የኤማኁስ መንገደኞች ራሱ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ እና ቀልዮጳ እንደሆኑ ይነገራል። አባቶቻችንም ሉቃስን ዘውእቱ ቀልዮጳ/ሉቃስ ማለት የቀልዮጳ ሌላ ስም ነው/ በማለት ሁለቱ የኤማኁስ መንገደኞች ሉቃስና ኒቆዲሞስ ናቸው ብለው በወንጌል ትርጓሜ ላይ አስቀምጠዋል።  Read more

ሆሣዕና

በኤርምያስ ልዑለቃል

መጋቢት 30 ቀን 2009 ዓ.ም.

ሆሣዕና ቃሉ የዕብራይስጥ ሲሆን ትርጉሙም አሁን አድን ማለት ነው። በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት የታላቁ ዓቢይ ጾም ስምንተኛ እሑድ የሆሣዕና በዓል በድምቀት የሚከበርበት ዕለት ነው። በዚህ ዕለት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ትህትና በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ያደረገውን ጉዞ የሚዘክር ቃለ እግዚአብሔር በስፋት ይደርሳል። በአራቱም ወንጌላውያን በቅዱስ ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ ና ዮሐንስ ይህንኑ የፍጹም ትህትና እና የፍቅር ጉዞ አስመልክቶ የተጻፉ የወንጌል ክፍሎች  (ማቴ 21፥1-17 ፣ ማር 11፥1-10 ፣  ሉቃ 19፥28-44 ፣ ዮሐ 12፥9-19) በቅድስተ ቤተ ክርስቲያን ዑደት እየተደረገ በአራቱም አቅጣጫዎች ይነበባሉ። Read more