‹‹ዮም መስቀል ተሰብሐ፤ ዓለም ተጸውአ፤ ወሰብእ ግዕዘ፡፡›› ቅዱስ ያሬድ

‹‹ዮም መስቀል ተሰብሐ፤ ዓለም ተጸውአ፤ ወሰብእ ግዕዘ፡፡ ዛሬ መስ ከበረ፤ ዓለም ለድኅነት ተጠራ፤ ሰውም ነጻ ወጣ፡፡›› ቅዱስ ያሬድ

‹‹መስቀል›› የሚለውን ቃል አለቃ ኪዳነ ወልድ በመዝገበ ቃላታቸው በቁሙ፤ መስቀያ፤ መሰቀያ፤ ለሞት የሚያበቃ መከራ በማለት ተርጉመውታል፡፡ (ገጽ.፰፻፹፫)

መንፈሳዊና ምሥጢራዊ የመስቀልን ትርጉም በሰፊው ያብራሩት ደግሞ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ናቸው፡፡

በውዳሴ መስቀል ድርሰታቸው ከሰጡት ማብራሪያ ጥቂቱን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

መስቀል፡   – ዕፀ ሕይወት ነው

  • ዕፀ መድኃኒት ነው፡፡
  • ዕፀ ትንቢት ነው፡፡
  • ዕፀ ዕረፍት ነው፡፡
  • ሰይጣንን የሚያጠፋ ምሳር ነው፡፡
  • የአጋንንትን ራሶች የሚቆርጥ ሰይፍ ነው፡፡
  • የቅድስናና የንጽሕና ማኅተም ነው፡፡
  • ለሚጋደሉ የድል አክሊል፣ ወደ በጉ ሰርግ ለተጠሩትም የሰርግ ልብሳቸው ነው፡፡……

አጠቃቀም

      ኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያለ መስቀል የምትሠራው ምንም ዓይነት ሥራ የለም፡፡ ከቅዱስ ፓትርያርኳ ጀምሮ እስከ ምእመናን ድረስ ያሉት ሁሉ ለአምልኮተ እግዚአብሔር ሲፋጠኑ መስቀልን በዋነኛነት ይጠቀማሉ፡፡ ጸሎታቸውን ሲጀምሩ ካህናት በመስቀል ምእመናን በጣታቸው አመሳቅለው በማማተብ ስመ ሥላሴን ይጠራሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን ስትፈጽም መስቀል ዋነኛ መንፈሳዊ መሣሪያዋ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የመስቀልን ሁለገብ አገልግሎት እንደሚከተለው ገልጸውታል፡፡

‹‹በተግባራችን ሁሉ፣ በምንገባበትና በምንወጣበት ጊዜ፣ ልብሶቻችንን ከመልበሳችን በፊት፣ ከመታጠባችን በፊት፣ በቀንና በማታ ወደ ምግብ ገበታ በምንቀርብበት ጊዜ፣ ማታ መብራታችንን በምናበራበት ጊዜ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ በምንጀምርበትና በምንፈጽምበት ጊዜ፣ በዕለታዊ ሕይወታችን መደበኛ ሥራችንን በምንጀምርበት ጊዜ በትምእርተ መስቀል ግንባራችንን እናማትባለን፡፡››

በግልጽ እንደሚታየው ድኅነተ ዓለም የተፈጸመበትን ቅዱስ መስቀል ቤተ ክርስቲያናችን በጉልላቷ ላይ በማድረግ ተሸክማው ትኖራለች፡፡ ካህናትና ምእመናንም ከቅፅረ ቤተ ክርስቲያን ሲደርሱ በዐይነ ሥጋ መስቀሉን በዐይነ ነፍስ ደግሞ የተሰቀለውን (ክርስቶስን) እያዩ ለተሰቀለው አምላክ የባሕርይ፣ ለተሰቀለበት መስቀል ደግሞ የአክብሮት ስግደት ይሰግዳሉ፡፡ ‹‹እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን፡፡›› (መዝ.፻፴፩፥፯) እንደተባለ፤ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መላ አካሉ ላረፈበት፣ እጆቹና እግሮቹ ለተቸነከሩበትና በቅዱስ ደሙ መፍሰስ ለተቀደሰ መስቀሉ እንሰግዳለን፡፡

ታሪካዊ የአጠቃቀም ጉዞውም የሚከተለውን ይመስላል፡፡

  • በሁለተኛው ምእት ዓመት የሶረያ ቤተ ክርስቲያን በምሥራቅ አቅጣጫ በግድግዳው ላይ መስቀልን ማኖር (ማንጠልጠል) ጀምራለች፡፡

በአራተኛው ምእት ዓመት ክርስትናው በተሰበከበት ዓለም ሁሉ በአብያተ ክርስቲያናት ሕንፃዎች በውስጥና በውጭ መስቀልን ማኖር፣ ማንጠልጠልና መቅረጽ በስፋት መተግበር ጀመረ፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ታላቁ ቈስጠንጢኖስ ከመክስምያኖስ ጋር በተዋጋ ጊዜ ‹‹በዝ ትእምርተ መስቀል ትመውዕ ፀረከ፡፡ ጠላትህን በዚህ  የመስቀል ምልክት ታሸንፋለህ፡፡›› ከሚል ጽሑፍ ጋር በጸፍጸፈ ሰማይ የመስቀል ምልክት መታየት ነው፡፡ ቈስጠንጢኖስ እንዳየው አድርጎ በፈረሱና በበቅሎው ኮርቻ፣ ልጓም፣ ግላስና በዕቃዎቻቸው ሁሉ፤ በጦር መሣሪያዎቻቸውና በጦር ልብሶቻቸው እንዲሁም በሰንደቅ ዓላማት ላይ የመስቀልን ምልክት በማስቀረጹ ድል አድራጊ መሆን ችሏል፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በአብያተ ክርስቲያናት በስፋት መጠቀም ተጀመረ፡፡ ከዚህም አልፎ እስካሁንም ድረስ እንደሚታየው ፊንላንድ፣ ጆረጂያ፣ አይስላንድ፣ ኖርዌይ፣ ስዊዘርላንድ፣ ስዊድን፣ ግሪክና የመሳሰሉት አገራት በባንዲራቸው ላይ የመስቀል ምልክት መጠቀምን ከቈስጠንጢኖስ ወርሰዋል፡፡

      ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- ‹‹እርሱም (ክርስቶስ) የአካሉ ማለት የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፡፡›› (ቈላስይስ ፩፥፲፰) በማለት እንዳስተማረው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንኑ በተግባር በሚያሳይ መልኩ ከላይ እንደገለጽነው በራስዋ (በጉልላቱ) ላይ መስቀሉን ተሸክማ የክርስቶስ አካልነቷን ታረጋግጣለች፡፡ ልጆቿም በአንገታቸው በማንጠልጠል፣ የክርስቶስ አካል (የቤተ ክርስቲያን) ሕዋሳት መሆናቸውን ያሳያሉ፡፡ በዚህም መስቀሉን ባዩ ቁጥር በላዩ የተሰቀለውን፣ የድኅነታቸው ራስና ፈጻሚ የሆነውን መድኃኔ ዓለምን እያሰቡ በዐይነ ኅሊና ቀራንዮ ይጓዛሉ፡፡

የመስቀሉ አከባበር ታሪካዊ ዳራ

      መስቀል የከበረው፣ ዓለም ለድኅነት የተጠራውና የሰው ልጅ ነጻ የወጣው በክርስቶስ ሲሆን በተለይም በቀራንዮ አደባባይ በተሰቀለ ጊዜ ይህ ሁሉ ተፈጽሟል፡፡ ‹‹ወይቤ ተፈጸመ ኵሉ፡፡ ሁሉ ተፈጸመ አለ፡፡›› (ዮሐ.፲፱፥፴) እንዲል፡፡ በመስቀል ላይ በሆነው ሞቱ ነቢያት የተነበዩት ትንቢት፣ የመሰሉት ምሳሌ፣ የቆጠሩትም ሱባኤ ተፈጽሟልና፡፡ በሌላ አገላጽ ሁሉም ስለሰው ልጅ ድኅነት ነበርና የሰው ልጅ ድኅነት በመስቀል ላይ ተፈጸመ፤ ታወጀ፤ ተረጋገጠ፡፡ በደሙ ቀድሶ ያከበረውን ቅዱስ መስቀል በዚህ መልክ የማክበራችን ምክንያትስ ምንድነው? ቀጥለን እናየዋለን፡፡

      መድኃኒታቸውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ክደው የሰቀሉ አይሁድ በደሙ የከበረ መስቀልም ሕይወት፣ መድኃኒት መሆኑን ባዩ ጊዜ በሰይጣናዊ ቅንዓት ነደዱ፡፡ ‹‹እሱን (ክርስቶስን) ተገላገልን ስንል መስቀሉ ደግሞ ተአምራት ያደርግ ጀመር!›› ብለው በመቆጣት በቆሻሻ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ ጣሉት፡፡ እስከ ፸ ዓመተ ምሕረት ድረስ የጣሉት ቆሻሻ በመስቀሉ ላይ እንደኮረብታ ተከመረ፡፡ በ፸ ዓ.ም ኢየሩሳሌም በጠፋች ጊዜ የተረፉት አይሁድ በመሰደዳቸው ተረስቶና ተቀብሮ ከ፫፻ ዓመታት በላይ ያለበት ሳይታወቅ ቀረ፡፡

      መስቀሉ የእግዚአብሔር ኃይል መሆኑን የተረዳች (፩ቆሮ.፩፥፲፰)ንግሥት እሌኒ በ፫፻፳፮ ዓ.ም መስቀሉን ፍለጋ ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ገሰገሰች፡፡ በዚያም ከአይሁድ መምህራን መካከል የተቆጠረ ኪርያኮስ የተባለ ሽማገሌ አገኘች፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ መስቀሉ የተቀበረበትን አካባቢ አሳይቷታል፡፡ ክፉዎች ወገኖቹ ከጉድጓድ ቀብረው የቆሻሻ መጣያ እንዳዳረጉት ነገራት፡፡ ንግሥት እሌኒም መስከረም ፲፮ ቀን እንጨት አስደምራ ከለኮሰችው (ካቀጣጠለችው) በኋላ ከፍህሙ ላይ በርካታ ዕጣን አደረገችበት፡፡ የዕጣኑም ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ከመንበረ ጸባኦት ደርሶ ተመልሶ በፈቃደ እግዚአብሐር መስቀሉ ከተቀበረበት መካከለኛው ኮረብታ ዐረፈ (ሰገደ)፡፡ በዚህ ድንቅ ተአምር መካነ መስሉን ተረድታ መስከረም ፲፯ ቀን ሠሪዊቷንና ሕዝቡን ይዛ ማስቆፈር ጀመረች፡፡

      ለረጅም ዓመታት በመስቀሉ ላይ የተጣለው ቆሻሻ ታላቅ ተራራ ሁኖ ስለነበር ያንን የቆሻሻ ክምር በጥንቃቄ ካስወገዱ በኋላ ሦስት መስቀሎችን አገኙ፡፡ እነዚህም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የሆነው ቅዱስ መስቀልና የሁለቱ ወንበዴዎች የተሰቀሉባቸው መስቀሎች ናቸው፡፡ መስቀሉ የተገኘው ከብዙ ድካምና ጥረት በኋላ መጋቢት ፲ ቀን ሲሆን ዕውራንን አብርቷል ሐንካሣንን አርትቷል ሙታንን አንሥቷል የጌታችን መስቀልም ባደረገው ድንቅ ተአምራት በተለይም ሙት በማስነሳቱ ተለይቶ ሊታወቅ ችሏል፡፡

      የተባረከችው ንግሥት እሌኒ ባየቻቸው አምላካዊ ተአምራት እጅግ በመደሰቷ መስቀሉን አቅፋ እግዚአብሔርን አመሰገነችው፡፡ ሕዝቡም ሁሉ በቅዱስ መስቀሉ መገኘት ከፍተኛ ሐሴትና ደስታ አደረጉ፡፡ እየዳሰሱትም ኪሪያላይሶን እያሉ ዘመሩ፡፡ በመሸም ጊዜ ቅድስት እሌኒ ከኢየሩሳሌሙ ኤጲስ ቆጶስ ከአባ መቃርዮስ፣ ከሠራዊቶቿና ከሕዝቡ ጋር የችቦ መብራት ይዘው በሰልፍ ሆነው እየዘመሩ ቅዱስ መስቀሉን በክብር አኖሩት፡፡

      ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከመጀመሪያ ጀምሮ መስቀሉን የተሸከመችውና የምታከብረው ቢሆንም በተለይም ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በልዩ ሁኔታ ማክበርን ጀመረች፡፡ ለመስቀል መስገድ፣ መስቀልን መሳም፣ በመስቀል ሕዝብን መባረክ፣ መስቀል መያዝ፣ በልብስና በአካል ላይ የመስቀል ምልክት መቅረጽ እየተስፋፋ መጣ፡፡ በማያምኑ ዘንድ እንደ ሞኝነት የሚቆጠረው (፩ቆሮ.፩፥፲፰) የመስቀሉ ነገር ኃይለ እግዚአብሔር መሆኑ ይበልጥ ጎልቶ የተሰበከውና ክብሩ የገነነው ከዚህ ወዲህ ነው፡፡

      በዓለ መስቀል መስከረም ፲፯ ቀን የመከበሩ ምክንያት ከላይ እንደገለጽነው በዚህ ቀን ንግሥት እሌኒ ግብር እግብታ ቁፋሮ ያስጀመረችበት ቀን ሲሆን በዋናነት ግን በዚሁ ቀን በዓመቱ ንግሥት እሌኒ በ፫፻፳፯ ዓ.ም በጎልጎታ ቤተ ክርስቲያን አሠርታ መስቀሉን ያስገባችበትና ቅዳሴ ቤቱን ያከበረችበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡ በዚሁም ላይ መጋቢት ፲ ቀንም በዓሉን ማስብ (ማክበር) አልተወችም፡፡

      ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታላቁን የመስቀል በዓል በየዓመቱ በአደባባይ (በመስቀል አደበባባይ) በድምቀት ታከብራለች፡፡ በዕለቱ ማለትም በበዓለ መስቀል ዋዜማ የቅድስት እሌኒን የመስቀል ፍለጋ ጉዞ ለማስታወስ ደመራ ደምራ ለበዓሉ የተዘጋጀውን ስብሐተ እግዚአብሔር ታደርሳለች፡፡ በጸሎቱም ፍጻሜ በ፬ቱም መዓዝን አባቶች ዞረው ከባረኩት በኋላ ይለኰሳል፤ (ይቀጣጠላል)፡፡ ሕዝቡም ችቦውን እያቀጣጠለ ታሪኩንና በዋናነት በመስቀሉ ኃይል የተገለጠው ብርሃን ያበሥራል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ለቅዱስ መስቀሉ የሰጠችውን ልዩ ትኩረት ለመግለጽ ከመስከረም ፲፯ እስከ መስከረም ፳፬ ድረስ ያሉትን ቀናት ዘመነ መስቀል ብላ ሰይማዋለች፡፡ በነዚህም ቀናት ነገረ መስቀሉ ይሰበካል፤ ስብሐተ መስቀልም ይደርሳል፡፡

መስቀልና ነገረ ድኅነት

      በነገረ ድኅነት አስተምህሮ መስቀል ዋናው ማጠንጠኛ ነው፡፡ የተነገረው ትንቢት፣ የተቆጠረው ሱባኤና የተመሰለው ምሳሌ የተፈጸመው በመስቀል ላይ ነው፡፡ (ዮሐ.፲፱፥፴) ኢየሱስ ክርስቶስን እወዳለሁ የሚል ሁሉ እውነተኛዋን የአደራ እናቱን ያገኘውም በመስቀል ላይ ነው፡፡ (ዮሐ.፲፱፥፳፭‐፳፯) በሰው ልጆች ላይ ለ፶፻፭፻ ዓመታት ሠልጥኖ የኖረው ሞት የተወገደው በመስቀል ላይ በሆነው በክርስቶስ ሞት ነው፡፡ ጠላት ዲያብሎስ በአዳምና በሔዋን ላይ ያኖረውን (የሰወረውን) የዕዳ ደብዳቤ የደመሰሰው በመስቀሉ ነው፡፡ ‹‹በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፤ እርሱንም በመስቀል አርቆ ከመንገድ አስወግዶታል፡፡›› (ቈላ.፪፥፲፬‐፲፮) እንዲል፡፡

      ስለ ነገረ ድኅነት ስንነጋገር ስለመስቀሉ መናገር የግድ ነው፡፡ የመዳናችን ጉዳይ (ምስጢር) ያለ መስቀሉ አልተፈጸመምና፡፡ ሊቃውንቱ ይህን በዝማሬያቸው ‹‹ለአዳም ዘአግብኦ ውስተ ገነት፣ ወለፈያታዊ ኅረዮ በቅጽበት፣ ዝንቱ ውእቱ መስቀል፡፡ አዳምን ወደ ነገት ያስገባው፤ ወንበዴውንም በፍጥነት የጠራው ይህ መስቀል ነው፡፡›› በማለት በመስቀል የተፈጸመውን ድኅነት አመስጥረውታል፡፡ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በመስቀል ላይ የሆነውን የሰው ልጅ ድኅነት እንዲህ በማለት ነው የገለጸው፡፡ ‹‹ከኀጢአታችን ያወጣን ዘንድ በጽድቁም ያድነን ዘንድ እርሱ ስለኀጢአታችን በሥጋው በእንጨት ላይ ተሰቀለ፤ በግርፋቱም ቊስል ቊስላችሁን ተፈወሳችሁ፡፡›› (፩ጴጥ. ፪፥፳፬) ይህንኑ አስመለክቶ ቅዱስ ጳውሎስም፡- ‹‹ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደተሰቀለ እናውቃለን፤ የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቋልና፡፡›› በማለት በሞት ጥላ ይኖር የነበረ የሰው ልጅ በመስቀሉ ነጻ መውጣቱን ገልጾልናል፡፡

መስቀል የሰላም ዋስተና

      በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት ክርስቶስ በመስቀሉ ፯ቱን መስተጻርራን (ተቀዋዋሚዎች) አስታርቋል፡፡ እነዚህም ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና ቅዱሳን መላእክት፣ ሕዝብና አሕዛብ፣ እንዲሁም ነፍስና ሥጋ ናቸው፡፡ በነዚህ በጥንድ በጥንዶቹ መካከል የጥል ግድግዳ ቆሞ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ (5500) ዘመናት ሰላም ጠፍቶ በጠላትነት ነበር የኖሩት፡፡ እነዚህን በማስታረቅ እውነተኛውን ሰላም የሰጣቸውና አንድ ያደረጋቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን የጥሉን ግድግዳ ያፈረሰውም በመስቀሉ ነው፡፡ ‹‹እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ፣ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፣ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሐር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው፡፡ መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፣ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ፡፡›› (ቈላስ.፩፥፳) በማለት የገለጸልን ይህንን ሲያረጋግጥልን ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ሕዝብ እና አሕዛብ (የተገዘሩና ያልተገዘሩ) በመባባል አንዱ አንዱን እየነቀፈ የሚያሳድድበት ዘመን ያበቃው በመስቀሉ ነው፡፡ ይህ በመስቀሉ የተገኘው ሰላምና አንድነት ነው፡፡ የመጀመሪያው የሁለትነታቸው ስም ሕዝብ (የተገዘሩ)፣ አሕዛብ (ያልተገዘሩ) የሚለው ስም ጠፍቶ በክርስቶስ ያገኘነው አንድ ስም ክርስቲያን መጠሪያችን ሆነ፡፡ ይህ ስም ሰላማችን የተረጋገጠበትና አንድንታችን የታወጀበት፣ ምድራውያኑንና ሰማያውያኑን እንኳን ሳይቀር በአንድ ምስጋና (ቅዳሴ) ያስተባበረ ሆነ፡፡

ማጠቃለያ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀሉ ሁሉን ወደ እሱ ያቀረበበትና አንድ ያደረገበት መሆኑን በገለጸበት አንቀጽ እንዲህ ብሏል፡፡ ‹‹እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ካልሁ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ፡፡›› (ዮሐ.፲፪፥፴፪) ምንም ዓይነት ምድራዊና ሥጋዊ መስፈርቶች ሳያግዱት ሁሉም ሰው በመስቀሉ ተስቦ ቀርቧል፡፡ ከምድር ብቅ፥ ከሰማይ ዝቅ ብሎ መሰቀሉ ሰማያውያንና ምድራውያኑን አንድ ማድረጉን ማሳያ ነው፡፡ የመስቀሉን አራት ጐኖች፥ የክርስቶስም አራቱን አቅጣጫዎች ያጣቀሰ ስቅለቱ የሰው ልጆችን ሁሉ (በአራቱ ማዕዘናት ያሉትን) አንድ ማድረጉን የሚገልጽ ናቸው፡፡ ሁሉን ትተን እንድንከተለው ያዘዘን መስቀሉን ተሸክመን ነው፡፡ (ማር.፰፥፴፬)

ማኅበረ ቅዱሳን ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ

ኢ-ሜይል አድራሻ፡-