በፊንላንድ ለመጀመሪያ ጊዜ ሐዊረ ሕይወት ተካሄደ።
በማኅበረ ቅዱሳን አውሮጳ ማዕከል በፊንላንድ ግንኙነት ጣቢያ አስተባባሪነት የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ለመጀመሪያ ጊዜ በፊንላንድ ሄልሲንኪ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የፊንላንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የባህል ማዕከል እሑድ ግንቦት ፭ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም ተካሄደ። በመርሐ ግብሩ ላይ የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን ካህናትን እና ተጋባዥ መምህራንን ጨምሮ የደብሩ ሰንበት ት/ቤት መዘምራን፣ ከሄልሲንኪ እና ከሌሎችም ከተሞች የመጡ ምእመናን ተሳትፈዋል።
መርሐግብሩን በጸሎት ከፍተው ያስጀመሩት የሄልስንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስትያን አስተዳዳሪ መጋቤ ብሉይ ቀሲስ ለማ በሱፈቃድ ሲሆኑ በመክፈቻ ንግግራቸውም የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት በማስተላለፍ ስለ ሐዊረ ሕይወት ዓላማ እና አስፈላጊነት አጭር ገለጻ አድርገዋል ።
ከአስተዳዳሪው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት በማስከተልም በዲ/ን ዶ/ር ሰሎሞን አበበ በማቴዎስ ወንጌል ፯፥፲፬ «ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፥ መንገዱም የቀጠነ ነውና፥ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው» የሚለውን ቃል መነሻ በማድረግ ሰፊ ትምህርት ተሰጥቷል። በመልእክቱም እኛ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እርሱ ያሳየንን ፍቅር ማድረግ እንደሚገባ እና በቃልም በሕይወትም ያሳየንን ሥራ ደግመን ማድረግ እንዳለብን ተነግሯል። በተለይም ደግሞ በክርስቶስ አንድ የሆንበትን ቁም ነገር በመርሳት ባልሆነ ነገር መለያየቱን መቆም እንዳለበት ትምህርት ተሰጥቷል።
ከመጀመሪው ቃለ ወንጌል በመቀጠል በሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስትያን አዳጊ ሕጻናት መዝሙርና እና ሥነ ጽሑፍ ቀርቧል። በስሥነ ጽሑፋቸውም የእመቤታችን ድንግል ማርያምን የልደት ታሪክ በሚጣፍጥ አንደበታቸው ያቀረቡ ሲሆን በተለይም አብዛኞቹ ሕጻናት ፊንላንድ ሀገር ተወልደው እንደማደጋቸው መጠን እንዲህ ባማረ መንገድ ማቅረባቸው ደብሩ ተተኪ አገልጋዮችን እዚሁ ሀገር ከተወለዱ ሕጻናት ለማፍራት ምን ያህል ጥረት እያደረገ እንደሆነ ያሳያል። በማስቀጠልም በሁለተኛው የትምህርት መርሐ ግብር «ኦርቶዶክሳዊ የመዳን ትምህርት» በሚል ርዕስ ከኢትዮጵያ በመጡት መምህር በዲ/ን ያረጋል አበጋዝ ሰፊ ትምህርት ተሰጥቷል። ትምህርቱም በመሠረታዊ የቤተክርስትያናችን የነገረ ድኅነት አስተምሮ ላይ ያተኮረ ነበር።
ከምሳ መልስ የከሰዓቱ መርሐግብር በሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስትያን ሰንበት ት/ቤት መዘምራን ባቀረቡት ዝማሬ የተጀመረ ሲሆን ክፍል ሁለት ኦርቶዶክሳዊ የመዳን ትምህርት በመምህር ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ ተሰጥቷል። ትምህርቱን በማስከተል የደብሩ ሕጻናት በግእዝ አማርኛና ፊንላንድኛ ቋንቋዎች መዝሙራትን አቅርበዋል። በማስከተልም ስለ ማኅበረ ቅዱሳን እና ስለሚያከናውናቸው እንቅስቃሴዎች በማስመልከት ገለጻ በግንኙነት ጣቢያው ጸሐፊ የቀረበ ሲሆን በገለጻውም ማኅበሩ በቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል ውስጥ ገዳማትን እና አብነት ት/ቤቶችን በመደገፍ ሂደት ውስጥ የተሰሩ ሥራዎችን እና የተገኙ ውጤቶች እና የነበሩ ችግሮች ቀርበዋል።
በመጨረሻ መጋቤ ብሉይ ቀሲስ ለማ በሱፈቃድ ባስተላለፉት መልእክት እና ምክር ለምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት መሻሻል እንደዚህ አይነት ጉባኤያት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበው ጉባኤው በጸሎት ተዘግቷል።