በማኅበረ ቅዱሳን አዉሮፓ ማዕከል የዩኬ(እንግሊዝ) ንዑስ ማዕከል አስተባባሪነት የተዘጋጀዉ ጉባዔ ተጠናቀቀ
በእንግሊዝ ንዑስ ማዕከል
ሐምሌ 29 ቀን 2008 ዓ.ም.
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ ቤቶች ማ/ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን አዉሮፓ ማዕከል የዩኬ (እንግሊዝ) ንዑስ ማዕከል ከሁለት አጥቢያ አቢያተ ክርስቲያናት ጋር በመተባበር አዘጋጅቶት የነበረዉ የስብከተ ወንጌል ጉባዔ በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል። ጉባዔው ሰኔ ፳፭ እና ፳፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በበርሚንግሃም ደ/መድኃኒት ቅዱስ አማኑኤል እንዲሁም ሐምሌ ፪ እና ፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በሊድስ ደ/ ስብሐት መድኃኔ ዓለም አቢያተ ክርስቲያናት የተካሄደ ሲሆን በበርሚንግሃም፣ በሊድስ እና በአቅራቢያ ከተሞች የሚኖሩ በራካታ ምዕመናን ተካፍለዋል።
ለዚህ ጉባዔ ከኢትዮጵያ የተጋበዙት መምህር ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ በተለያዩ ርዕሶች ላይ ሰፊ መንፈሳዊ ትምህርቶችን ከመስጠታቸውም ባሻገር በጥያቄና መልስ መርሐግብር ከምዕመናን ለተሰበሰቡ በርካታ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል:: ከዚህም በተጨማሪ በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ በተለይም በተሃድሶ ማንነት እና እንቅስቃሴ ዙሪያ በቪድዮ የተደገፈ ሰፊ ገለጻ ሰጥተዋል::ከነዚህ ጉባዔያት ጎን ለጎን ከሰ/ት/ ቤት አባላት እንዲሁም በተለያዩ የቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ዘርፎች እያገለገሉ ከሚገኙ (ለምሳሌ በተተኪ መምህርነት እና መርሐ ግብር መሪነት) ወንድሞች ጋር የተለየ ሰዓት በመመደብ የመንፈሳዊ አገልግሎት ማጠናከሪያ መርሐግብሮች ተካሂደዋል።
በዩኬ ንዑስ ማዕከል አስተባባሪነት የአጥቢያዉ ሰ/ት/ቤት አባላት ከአቅራቢያዉ ካሉ ሌሎች የሰ/ት/ ቤቶች እና ማኅበራት አባላት ጋር ለጉባዔዉ የተመረጡ ያሬዳዊ መዝሙራትን በጉባዔዉ ላይ በጋራ አቅርበዋል። ከዚህም በተጨማሪ የመዝሙር ተሰጥኦ ያላቸዉ ሁለት እህቶች ከለንደን እና ከደርቢ ከተማ የተጋበዙ ሲሆን ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን ሰውተው በሁለቱም ከተሞች በተደረጉ ጉባኤያት ላይ በመገኘትና ከምዕመናን ጋር እግዚአብሔርን በማመስገን አርአያ ሆነዋል።
ለዚህ ጉባዔ መሳካት ከዩኬ ንዑስ ማዕከል ጋር በመሆን የበርሚንግሃም ደ/መድኃኒት ቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም ቀሲስ አዲስ አበበ እና የሊድስ ደ/ ስብሐት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ቀሲስ ከፍያለዉ አስቻለዉ እንዲሁም የአብያተ ክርስቲያናቱ መንፈሳዊ የሰበካ ጉባዔ አባላትና ምዕመናን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። እነዚህ የቤተ ክርስቲያን አባቶች በለንደን ደ/ገነት ቅድሥት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ካለባቸዉ መንፈሳዊ ኃላፊነት እንዲሁም የግል እና የማህበራዊ ኑሮ ጫና ሳይበግራቸዉ ጉባዔዉ ከታሰበበት እስከ ተጠናቀቀበት ቀን ድረስ በመከታተል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ በተለይ የየሰበካ ጉባኤያቱ አንዳንድ አባላት እና ምዕመናን በጉባዔዉ ዝርዝር ዝግጅት (በደብዳቤ መጻጻፍ፣ በማስታወቂያ ሥራ፣ በጉባዔ ቦታ ፍለጋ፤ በመስተንግዶ ወዘተ) ዉስጥ በመሳተፍ ከፍተኛ ሚና ተጫዉተዋል። በየጉባዔያቱ የተሳተፉት ምዕመናን በዝግጅቱ እንደተደሰቱና የዚህ ዓይነት መርሐግብር በየዓመቱ እንዲዘጋጅ የጠየቁ ሲሆን በተለይ የሊድስ ደ/ስብሐት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ጉባዔ መጨረሻ ላይ በሚቀጥለዉ ዓመት ለሚዘጋጀዉ ተመሳሳይ ጉባዔ የመምህርና የዘማሪ ሙሉ ወጭ መሸፈኛ ከወዲሁ ከምዕመናን ቃል ተገብቷል።
ይህ ጉባዔ የዩኬ ን/ማዕከል በ2008 ዓ.ም ለማከናወን በእቅድ ከያዛቸዉ ሥራዎች አንዱ ሲሆን ን/ማዕከሉ ጉባዔዉን ከማስተባበር በተጨማሪ የመምህሩን የቪዛ እና ትራንስፖርት ሙሉ ወጪ ሸፍኗል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!