በእንግሊዝ የ2ኛው ዙር ሐዊረ ህይወት ተካሄደ
በዩኬ ንዑስ ማዕከል
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤ/ማ/ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን አዉሮፓ ማዕከል የዩናይትድ ኪንግደም ንዑስ ማዕከል ያዘጋጀው የ2ኛው ዙር ሐዊረ ሕይወት መርሐግብር ሰኔ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. በታላቋ ብሪታንያ በነቲንግሃም ከተማ በቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተክርስቲያን ተካሄደ።
በጉባዔው ላይ ከተለያዩ የእንግሊዝ ከተሞች የተሰባሰቡ 50 ያህል ህፃናት እና ከ230 በላይ የሚሆኑ ካህናትና ምዕመናን ተሳትፈዋል። መርሐ ግብሩም በካህናት አባቶች ጸሎትና ቡራኬ ተከፍቶ የአዉሮፓ ማዕከል ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር በላቸው ጨከነ ለሐዊረ ህይወቱ ተሳታፊዎች ሁሉ የእንኳን ደህና መጣችሁ! መልዕክት አስተላልፈዋል። አያይዘውም ስለማኅበሩ አመሠራረት ፤ ስያሜ፤ እንዲሁም ማኅበሩ ስለሚያደርገው አስተዋፅዖ በአጭሩ አብራርተዋል።
በመቀጠል የዩኬ ን/ማዕከል አባላት መዝሙር ከቀረበ በኋላ በመጋቤ ብሉይ ቀሲስ ለማ በሱፍቃድ የሄልሲንኪ ደ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ በቤተክርስቲያን ሥርዓትና አገልግሎት ዙሪያ ጥልቅ ትምህርት ተሰጥቷል። የትምህርት አቀራረብ መሠረታዊ የሆነና የምእመናንን ግንዛቤ ግምት ውስጥ ያስገባ እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ ትምህርት ነበር። በትምህርቱ ስለኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ፤ የአገልግሎት ሥርዓት፤ የአገልጋይና የተገልጋይ ደንብና ጥንታዊ የሆነ አደረጃጀት እንዳላትና፤ በትውፊትዋ ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ እና ቅዱሳት መፃህፍት ያልተደገፈ ወይም ያልተመሳከረ ሥርዓትም ሆነ ልማዳዊ የሆነ አገልግሎት እንደሌላት ግልፅና ጥልቅ የሆነ ማስገንዘቢያ ተሰጥቷል።
ከዚህ በማስቀጠልም ይህንን ሐዊረ ሕይወት ልዩ ካደረጉት መርሐ ግብሮች መካከል በህፃናት ክፍል ተዘጋጅቶ ሕፃናቱ በጋራ መዝሙር ለጉባኤው ማቅረብና የሕጻናት የጥያቄና መልስ ዉድድር ነው። በዉድድሩ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ለወጡ ሶስት ኅፃናት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ተሳትፎ ላደረጉ ህፃናት በሙሉ በዩኬ ን/ማዕከል የተዘጋጀ የተሳትፎ ሰርተፍኬት በየአጥቢያ ቤተክርስቲያናቸው በኩል እንዲደርሳቸው ተደርጓል።
ይህ የህፃናት መርሐ ግብር ከወላጆች መርሐ ግብር በተጓዳኝ መካሄዱ ህፃናት ለቤተክርስቲያን አስተምህሮና አገልግሎት ፍላጎት እንዲኖራቸው ለማበረታታት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ታምኖበታል።
ማኅበረ ቅዱሳን በአገር ቤት የተለያዩ አካላትን በማስተባበር ስለሠራቸው ሥራዎች በተለይም ስብከተወንጌል ባልተስፋፋባቸው የጠረፍ አህጉረ ስብከቶች አካባቢ ስለሚካሄደው የስብከተ ወንጌል ማስፋፍያ መርሐግብር እንዲሁም አብነት ት/ቤቶች እና ገዳማት በመግለጽ በቀጣይም ያሉባቸዉን ችግሮች ቀርፈው ራሳቸዉን እንዲችሉ ለማድረግ የተሠሩትን እና እየተሠሩ ያሉትን ሥራዎች በጽሑፍ፣ በድምጽ እና በምስል በማስደገፍ በንዑስ ማዕከሉ ቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል አቅርቧል። የዕለቱ ሁለተኛ ትምህርት የሆነዉን “ነገረ ድኅነት” በመጋቤ ሥርዓት ቀሲስ ሚካኤል ተሰጥቷል። በትምህርቱም ለመዳን መደርግ የሚገባውን ተግባርና የአተገባበር ሥርዓት በጥልቀት ተዳሷል።
በማስከተልም የሰሜን ምዕራብ አዉሮፓ ሀገረ ስብከት ተወካይ ሊቀ ኅሩያን ፍሥሐ ተፈሪ በግል የተሰማቸውን ደስታና የሀገረ ስብከቱን መልዕክት አስተላልፈዋል። ተወካዩ ሀገረስብከቱ ከማህበሩ ጋር እስካሁን ያለውን ቀና ትብብር አስገንዝበው ወደፊትም በመተባበር ሊሠሩ እንደሚገባ ገልፀዋል።
እንዲሁም በማህበረ ቅዱሳን የታላቋ ብሪታንያ ንዑስ ማዕከል ምክትል ሰብሳቢ ለጉባዔዉ ዝግጅት አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሰሜን ምዕራብ አዉሮፓ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት፣ ጉባኤው ላይ ትምህርት ላስተላለፉት አባቶች እንዲሁም በለንደን እና ከለንደን ዉጭ ለሚገኙ በገንዘብ እና በተለያየ መልክ ለረዱ ድርጅቶችና፣ ምዕመናን እና ምዕመናት ምስጋና አቅርበዋል። የጉባኤው ተሳታፊዎች በተሰጡት ትምህርቶች ብዙ እውቀት እንዳገኙበት እና በአጠቃላይ መርሐ ግብሩ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። በመጨረሻም መርሐግብሩ በኣባቶች ጸሎትና ምስጋና ተፈጽሟል።