በኮፐንሀገን የደብረ ምሕረት ቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ዐቢይ የአዲስ ዓመት መንፈሳዊ ጉባኤ አካሄደ።

በዴንማርክ ግንኙነት ጣቢያ

መስከረም 10 ቀን 2010 ዓ.ም.

ባሳለፍነው ቅዳሜ መስከረም 6 እና እሑድ መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም. (September 16 and 17 /2017) በዴንማርክ ኮፐንሀገን የደብረ ምሕረት ቅዱስ አማኑኤል ደብር የአዲሱን ዓመት ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ ዐቢይ የርእሰ አውደ ዓመት ጉባኤ አድርጓል። የጉባኤውም መሠረታዊ ዓላማ በሥራ፣ በትምህርት እና በተለያዩ የኑሮ ሁኔታዎች ከአገር ርቀው ያሉ “ዝርዋን ምዕመናንን” ሀገራቸውን ባህላቸውን ይልቁንም ሃይማኖታቸውን በቤተክርስቲያናቸው በኩል እንዲያውቁ ለማስቻል እና በቋሚነት ሊገለገሉ የሚችሉበትን አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መፍትሄም ለመፈለግ ጭምር መሆኑ ተገልጿል።

ቅዳሜ በነበረው መርሐ ግብር የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥሪ ሰምተው ከተገኙት ምዕመናን በተጨማሪ ከተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ሕጻናትን በማደጎነት ለማሳደግ የወሰዱ የዴንማርክ ዜግነት ያላቸው “ወላጆች” ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ልጆቻቸው ጋር በመርሐ  ግብሩ ላይ የተገኙ ሲሆን በዕለቱም ለዘመነ ቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት የመክፈቻ ጸሎቱን ተከትሎ በደብሩ አስተዳዳሪ ክቡር መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ዘሚካኤል ደሬሳ ተላልፏል። በተጨማሪ ከኢትዮጵያ በመጡ ተጋባዥ መምህር ዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ ትምህርተ ወንጌል እና የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ተከናውኗል። የበዓሉን ልዩ ገጸ በረከት “አበባይሆሽ” መዝሙር እንዲሁም ሥነ ጽሐፍና ልዩ ልዩ ያሬዳዊ ጣዕመ ዝማሬዎችን ቀርበዋል። በመርሐ ግብሩ ፍጻሜ “ቤተ ክርስቲያኒቱ በኪራይ የቅዳሴና የጉባኤ መርሐ ግብራትን ማካሔድ የለባትም” በሚል ክቡር አስተዳዳሪው ባቀረቡት ማሳሰቢያ ለቤተክርስቲያናቸው ገንዘባቸውን ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን እስከመስጠት ዋጋ ለመክፈል ምዕመናን ቁርጠኝነት በማሳየታቸው በልማት ኮሚቴነት አምስት የሥራ አስፈጻሚ አባላት ያሉት የሕንጻ አፈላላጊ አባላት ተመርጠው በጸሎተ ማርያም ኃላፊነት ተቀብለው የዕለቱ መርሐ ግብር በጸሎት ተቋጭቷል።

በዕለተ ሰንበት እሑድ ማለዳው ላይ በቀጠለውም መርሐ ግብር በክቡር አስተዳዳሪው መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ዘሚካኤል ደሬሳ መሪነት ጸሎተ ኪዳን እና የጉባኤ መክፈቻ ጸሎት ተደርጎ የዚህ ዐቢይ የአዲስ ዓመት መንፈሳዊ ጉባኤ አካል የሆነው የ “ጸረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ” ግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብር በ ዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ ቀርቧል። መነሻውን አውሮፓ አድርጎ ምዕመናንን ፕሮቴስታንትና አልፎም እምነት አልባ አለማዊ እስከማድረግ አላማ ያለውን ባለ 500 ዓመት ታሪክ የዘመናዊ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ድብቅ አጀንዳ እና በዓለማችን ይልቁንም በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ከነ መፍትሔ አቅጣጫው የቀረበ ሲሆን በግንዛቤ ማስጨበጫ ላይ ማጠቃለያቸውን ያስቀመጡት የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ዘሚካኤል ደሬሳ ቀጣዩን ትውልድ በማነጽ ረገድ ወላጆች ሊኖራቸው የሚገባውን ድርሻ ተገንዝበው ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

በመጨረሻም ዲ/ን ቡሩክ አሸናፊ በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ከሰባት ዓመታት በላይ በትምህርት እና በሥራ ቆይታቸው ቤተ ክርስቲያንን በትጋት በማገልገላቸውና ይልቁንም ያለፉትን ሦስት ዓመታት ወደ ዴንማርክ ከመጡበት ጊዜ አንስቶ ያለመታከት ላከናወናወኗቸው የስብከተ ወንጌል፣ የቅዳሴ፣ የዝማሬና ልዩ ልዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች የምሥጋናና የሽኝት መርሐግብር በማካሔድ የአውደ ዓመቱ ልዩ መርሐ ግብር ፍጻሜ ሆኗል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።