በጀርመን ኑረንበርግ ዐውደ ርእይ እና የስብከተ ወንጌል መርሐግብር ተካሄደ

በጀርመን ማእከል

ጥቅምት 20 ቀን 2010 ዓ.ም.

በደቡባዊቷ የጀርመን ከተማ ኑረንበርግ ጥቅምት 11 እና 12 2010 ዓ.ም “አብረን እንሥራ ለውጥ እናመጣለን” በሚል መሪ ቃል የዐውደ ርእይ እና የስብከተ ወንጌል መርሐግብር ተካሄደ። ይህንን በማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል  የጀርመን ንዑስ ማእከል ከኑረንበርግ ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን ፍኖተ ቤተከርስቲያን ገዳማት እና የአብነት ትምህርት ቤቶች እና  ማኅበረ ቅዱሳን የሚሉ ሦስት ትዕይንቶች የተከፋፈለውን ዐውደ ርእይ  ከ150 በላይ ምእመናን ጎብኝተውታል። በተለይም የዐውደ ርእዩ ዋና ጉዳይ በሆነው የኢትዮጵያ ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ለእምነትና ለታሪክ መጠበቅ እና  ለዕውቀት፣ ትውፊትና ባሕል ከትውልድ ወደ ትውልድ መሸጋገር ያበረከቱትና እያበረከቱት ያለው አስተዋኦ  እንዲሁም አሁን ያሉበት ወቅታዊ ችግሮቻቸው ላይ ሰፊ ገለጻ ተደርጓል። በተጨማሪም ችግሮቹን ለመፍታት በመላው ዓለም በተለይም በአውሮፓ ያሉ ምእመናን በማኅበረ ቅዱሳን አስተባባሪነት አስተዋፅዖ እያደረጉባቸው ያሉትን  በርካታ ጊዜያዊ እና ዘላቂ መፍትሔዎች በቪዲዮ በታገዘ ማብራሪያ ለተመልካች ቀርበዋል። በሁለቱ ቀናት በነበረው የስብከተ ወንጌል መርሐግብርም በመርጌታ ይቻለዋል ጎሽሜ እና በቀሲስ ዶ/ር ያብባል ሙሉዓለም አገልግሎትን የተመለከቱ ትምህርቶች ሰጥተዋል።

sdr

ከሁለቱ ቀናት የዐውደ ርእይ ገለጻ በኋላ የውይይት መድረክ የተከፈተ ሲሆን ምእመናኑ በማስረጃ እና በፎቶ የተደገፈ የቤተክርስቲያናቸውን ታሪክ እና ቅርስ በማየታቸው እጅግ ከመደሰታቸው እና  ከመማራቸው በተጨማሪ የገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶችን ተግዳሮቶች ለመፍታት በማኅበረ ቅዱሳን አስተባባሪነት እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችንም በማየታቸው መደሰታቸውን እና እነሱም  የዚህ ታሪክ አካል  ለመሆን የድርሻቸውን ለመወጣት መወሰናቸውን ተናግረዋል።  በእለቱ በነበረውም የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐግብር ላይም ምእመና  በንቃት ተሳትፈዋል።

 

 

በመርሐግብሩ ማጠቃለያ ላይ ንግግር ያደረጉት በማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ያብባል መሉዓለም በመርሐግብሩ መሳካት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ለዝግጅቱ መሳካት ከፍተኛውን ሚና ለተጫወቱት አካላት በሙሉ  በተለይም  መርሐግብሩ እንዲካሄድ ክትትል እና ድጋፍ ላደረጉት ለደብሩ አስተዳዳሪ ለመርጌታ ዳዊት ከፍያለው፣ የምመናኑን ስሜት በሚገዛ ያሬዳዊ መዝሙራቸው መርሐግብሩን ከማድመቃቸው በተጨማሪ ለተሳታፊዎች ምግብ አቅርበው በመሸጥ ከፍተኛ ገቢ ላስገኙት ለደብሩ መዘምራን እንዲሁም በዝግጅቶች ላይ በንቃት በመሳተፍ ለቤተክርስቲያናቸውያላቸውን ልዩ ፍቅር ላሳዩት  ለአጥቢያው ምእመናን ላቅ ያለ ምሥጋና አቅርበዋል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።