የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብራት በአገረ ኖርዌይ እና በአገረ ጣልያን

በኖርዌይ እና በጣልያን ን/ማዕከላት

ግንቦት 6 ቀን 2010 ዓ.ም.

፪ኛው ዙር የሐዊረ ሕይወት (የሕይወት ጉዞ) መርሐ ግብር በአገረ ኖርዌይ በክርስቲያንሳንድ ከተማ ከሚያዝያ ፲፫ – ፲፬  ፳፻፲ ዓ.ም. (April 21-22, 2018) ተካሄደ፡፡

በደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን እና በአውሮፓ ማዕከል የኖርዌይ ንዑስ ማዕከል በጋራ በተዘጋጀው በዚሁ መንፈሳዊ መርሐ ግብር ላይ በአገረ ኖርዌየ ከሚገኙ የቤተከርስቲያን ልጆችና መምህራን በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ተጋባዥ መምህራን ተገኝተዋል። በመርሐ ግብሩ ላይ ከኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጨምሮ ከተለያዩ የኖርዌይ ከተሞች የመጡ ምዕመናን ወምዕምናት ተሳትፈዋል፡፡

በዕለተ ቅዳሜ ጠዋት ላይ ጸሎተ ኪዳን የተካሄደ ሲሆን በማስከተልም መላከ ሰላም ቀሲስ ንግዳወርቅ በቀለ “ለወይኔ ያላደረግሁለት ምን አለ? “(ኢሳ. 5፣ 1) በሚል ርዕስ የትምህርተ ወንጌል አገልግሎት የሰጡ ሲሆን በመቀጠልም የኖርዌይ ን/ማዕከል ሰብሳቢ “ማኅበረ ቅዱሳን ማነው?” በሚል ማብራራያ ከሰጡ በኃላ “በአውሮፓ ተተኪውን ትውልድ ለቤተ ክርስቲያን በተቀናጀ መልኩ ለማስተማር ምን እናድርግ?” በሚል ርዕስ ላይ ለማህበረ ምዕመናኑ ሰፋ ያለ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡ እንዲሁም የንዑስ ማዕከሉ ትምህርት ክፍል በኢ/ኦ/ተ/ቤ ማኅበረ ቅዱሳን የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮጀክት ዙሪያ የአዳዲስ አማንያን ጥምቀትን ጉዳይ፣ፈተናዎችና ቀጣይ ሥራዎችን እና የምዕመናንን ድጋፍ የሚፈልጉ ሥራዎች በተመለከተ ሪፖርት አቅርቧል፡፡

 

ከምሳ በኃላ እና በማግሥቱ ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ  “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መግቢያ“ በሚል ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ በሁለቱም ቀናት በሁለት ተከታታይ ክፍሎች ሰፋ ያለ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡

የደብሩ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች እንዲሁም ማዕከላውያን በመርሐ ግብሩ ወቅት ወረብና የተለያዩ ያሬዳዊ መዝሙራትን አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም ከምዕመናን ለቀረቡ መንፈሳዊ ጥያቄዎች  በመላከ ሰላም ቀሲስ ንግዳወርቅ በቀለ  እና ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ ምላሽ ተሰጥቶ የዕለ እሁድ  መርሐ ግብር ተጠናቋል። ባለፈው አመትም በክርስቲያንሳንድ ከተማ የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር መካሄዱ ይታወሳል፡፡

በተያያዘ ዜናም በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ሰ/ማ/መ/ማኅበረ ቅዱሳን  የአውሮፓ ማዕከል የጣልያን ንዑስ ማዕከል ሚያዚያ ፳፯ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም.  በጣሊያን ሮም ከተማ የመጀመሪያውን ሐዊረ ህይወት አካሂዷል። መርሐ ግብሩ ላይም በሁለት አበይት ክፍላት ተከፍሎ ከኢትዮጵያ በመጡ ተጋባዥ መምህራን ለምዕመናን ሰፊ ትምህርት ተሰጥቶበታል። የመጀመሪያው ክፍል የንስሐ  ሕይወትን የተመለከተ ሲሆን በሁለተኛው ክፍል ደግም ነገረ-ቤተክርስቲያን በሚል ርዕስ ቤተ ክርስቲያን ማን ናት ቤተ ክርስቲያን እና ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ቤተ ክርስቲያን በየዘመናቱ የገጠሟት ፈተናዎች የሚሉ ጉዳዮች ያካተተ ሰፊ ትምህርት ተሰጥቷል።

በትምህርቶቹ ማጠቃለያ ላይ ምዕመናን ያሏቸው ጥያቄዎች አቅርበው በመምህራን ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!