የቴክኖሎጂ ውጤቶች ና የሉላዊነት ጫና በልጆች አስተዳደግ

በላቸው ጨከነ ተስፋ (ዶ/ር)

መግቢያ

“ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው። ” (መዝ፻፳፮፥፫)  ከእግዚአብሔር የተሰጡንን በረከት በሚገባው ተንከባክቦ፣ አስተምሮ  እና ጠብቆ ማሳደግ የወላጆች ትልቅ ሥራ ነው። ቅዱስ መጽሐፍ “እንግዲህ እነዚህን ቃሎች በልባችሁና በነፍሳችሁ አኑሩ። ልጆቻችሁንም አስተምሯቸው። በቤትህም ስትቀመጥ በመንገድም ስትሄድ ስትተኛም ስትነሳም አጫውቷቸው። እርሷንም እንዲሰጣቸው እግዚአብሔር ለአባቶቻችሁ በማለላቸው ምድር እንደ ሰማይ ዘመን በምድር ላይ ዘመናችሁ የልጆቻችሁም ዘመን ይረዝም ዘንድ በቤትህ መቃኖችና በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው።” (ዘዳ 11፥18) እንዳለ ልጆችን ጠብቆ እና ተንከባክቦ ማሳደግ የወላጆች ትልቁ ድርሻ ነው።

ዛሬ በተለይ  ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖሩ ወላጆች ለሚኖሩበት ሀገር ባህል እና ሕግ እንግዳ መሆን፣ ከልጆች ጋር የመግባቢያ ቋንቋ ችግር፣ ከቤተ ዘመድ መራቅ፣ የሥራ ጫና እና የጊዜ እጥረት፣ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጫና እና ዕለት ዕለት ቅድስት ቤተክርስቲያን በቅርባቸው እንደልብ ስለማያገኙ  የልጆችን አስተዳደግ የበለጠ ውስብስብ አድርጎታል። በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ዘመኑን ዋጅቶ ልጆችን በሃይማኖትና በግብረ ገብ ትምህርት ለማሳደግ ከወላጆች ብዙ ይጠበቃል። በዚህ አጭር ጽሑፍ  የቴክኖሎጂ ውጤቶች በልጆች አስተዳደግ ላይ የፈጠሩትን  ችግሮች እና የመፍቴሔ ሐሳቦች ለውላጆች ግንዛቤ ከመፍጠረ አንጻር ቀረበዋል።

የዘመኑን የልጆች አስተዳደግ ውስብስብና አስቸጋሪ ካደረጉት ነገሮች አንዱ የመረጃ ቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ በቴሌቪዥን እና በኢንተርኔት የሚተላለፉ መልክቶች ናቸው። ቴክኖሎጂ የራቀውን በማቅረብ የተወሳሰበውን በማቅለል ሕይወትን የተሻለች ማድረጉ አሌ የማይባል ቢሆንም የጎንዮሽ ውጤቱም ደግሞ በተለይ ለልጆች የዚያኑ ያህል የከፋ ነው። በአግባቡ እስካልተጠቀምንበት ድረስ። ክፉና ደጉን በአግባቡ ባለየው በልጆች አዕምሮ ላይ የሚያሳርፈው ተጽዕኖ ደግሞ የከፋ ነው። በአዳጊነት የዕድሜ ክልል የሚገኙ ተማሪዎችን ነፍስ ካወቁ በኋላ ከትምህርታቸው የሚያዘናጋቸው፣ ከእንቅልፍ፣ ከማኅበራዊ መስተጋብር ያራራቀቸው፣ ቁምነገር እንዳይሠሩ የሚያዘናጋቸው አየሆነ ነው። የተክኖሎጂ ውጤቶች ብለን የምንመድባቸው የቪዲዮ ጌም መጫወት፣  ፊልሞች ማየት፣ የቴሌቪዥን መረሐ ግብሮች፣ ኢንተርኔት በተለይም የፌስ ቡክ ቻት፣ ዘፈን ማድመጥ፣ የተለያዩ ጨዋታዎች መመልከት የመሳሰሉት ናቸው።

የአንተርኔት እና የቴሌቪዥን ለልጆች ያለው ጉዳት  

ልጆች ከሕፃንነት ጀምሮ አስቸጋሪ ሱስ የሚሆንባቸው የቴሌቪዥን ሥርጭት በተለይም ፊልም መመልከት ነው። ዕድሜ ሳይለዩ የሚለቀቁ የቴሌቪዥን ሥርጭቶችን ያለ ከልካይ የሚመለከቱ ሕፃናት ከፍተኛ ተፅዕኖ ይፈጠርባቸዋል። የተፅዕኖው ውጤትም አፍራሽ ወይም ገንቢ ሊሆን ይችላል። በየትኛውም የዕድሜ ክልል ያሉ ልጆች የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ያለ ገደብ እንዲመለከቱ መፍቀድ ወይም ፍጹም ቴሌቪዥን እንዳይመለከቱ መከልከል ተገቢ አይደለም። ሁለቱም ጽንፎች የየራሳቸው የጎንዮሽ/ጎጂ/ ውጤት አላቸው።

ልጆች በኮምፒውተሮቻቸው እና በስልካቸው ለእነርሱ የማያስፈልጉ ነገሮች ይደርሳቸዋል ከማያውቁት ጓደኛ ወይም ከማያውቁት ሰው ሊደርሳቸው ይችላል። ሌላው የኢንተርኔት ችግር ልጆች በሳይበር አባላጊዎች (አማጋጮች) የተጋለጡ ይሆናሉ። ድምጻቸውን በመቅረጽ ለሌሎች አዳኞች ያስተላልፋሉ፤ ይሸጣሉ። ልጆችን የእነርሱ ባሪዎች በመሆን የተጠየቁትን በሙሉ እንዲፈጽሙ አለበለዘያ የያዙትን ምስል እና ድምፅ ለወላጅ፣ ለጓደኛ አና ለትምህርት ቤት አንደሚሰጡ በመግለጽ ያስፈራራሉ። ልጆችም በዚህ ምክንያት ራሳቸውን እስከ ማጥፋት፣ ለጭንቀት እና ለአደንዛዥ እፅች መጋለጥ ይደርሳሉ። ልጆች በሳይበር ዝሙት እስከ መፈጸም ይደርሳሉ። የተለያዩ ማስተዋቂያዎችን ያያሉ፤ ያለ አቅማቸው የተለያዩ ነገሮችን ይገዛሉ። አላስፈላጊ የሆኑ ፋይሎች፣ ቫይረሶች ወደ ኮምፒውተር ሊወርዱ ይችላሉ።

በዘረፉ ጥናት ያደረጉ ምሁራን አብዛኛ ጊዚያቸውን በእንተርኔት እና በቴሌቪዥን የሚያሳልፉ ልጆች የሚከተሉት ችግሮች ያጋጥሟቸዋል ይሉናል፦

 • የጥናት ጊዜያቸውን በመሻማት ትምህርታቸው ላይ ጫና ይፈጥራል። ከአሰቡበት ሳይደረሱ ሊቀሩ ይችላሉ።
 • በሚዲያ የሚያዩትን እና በንግድ የሚተዋወቁ ነገሮችን በማየት አቅማቸው ከሚፈቅደው በላይ ለማግኘት ይመኛሉ፤ በብልጭልጭ ነገር እንዲታለሉ ይሆናሉ።
 • በፊልም የሚያቸውን ወንጀሎች እየተለማመዱ ወደ ማከናውን ይመጣሉ (ለምሳሌ ስርቆት፣ ሃሺሽ መጠቀም፣ መደባደብ) በሚዲያ የሚተዋወቁ የመንገድ ላይ ምግቦች (fast foods) በማየት ለምግቦች ልዩ ፍቅር ይኖርቸዋል። ይህም ሰውነታቸው ከመጠን በላይ እንዲሆን ስለሚያደርግ የጤና መታወክ ያስከትልባቸዋል።
 • አብዛኛውን ጊዜያቸውን ብቻቸውን ከሚዲያ ጋር ስለሚያሳልፉ ከቤተሰብ እና ከማኅበርሰቡ ጋር እንዳይገናኙ በማድርግ ምናባዊ (virtual) ዓለምን እንዲኖሩ የብችኝነትን/ግለኝነት/ ሕይወት ያለማምዳል።
 • የንባብ ክህሎታቸው ዝቅተኛ ይሆናል፤ ከንባብ ከሚገኘው በረከትም ተቋዳሽ አይሆኑም።
 • አካላዊ እንቅስቃሴ ሳያደርጉ ቁጭ ብለው ስለሚውሉ ጥንካሬ አይኖራቸውም።
 • የትኩረት አቅማቸው ዝቅተኛ ይሆናል፣ ለፈጠራና ለምርምር ጊዜ አይኖራቸውም።
 • በዕድሜያቸው መጫወት ያለባቸውን ያህል አይጫወቱም። ከእህት እና ወንድማቸው ከጓደኞቻቸው ጋር የሚጫወቱበት ጊዜ አያገኙም።
 • ሕይወትን በቴሌቪዥን መስኮት ሽው እልም ስትል እያዩ ቀላል አድርገው ያስቧትና ሲጋፈጧት ከባድ ትሆንባቸዋለች።
 • ልጆች ብዙ ክሂሎችን የሚያዳብሩት በማየት ሳይሆን በመሥራት ነውና የሥራ ጊዜያቸውን ይሻማሉ።
 • ከአካባቢያቸው ጋር የሚኖራቸው መስተጋብር የተወሰነና ዝቅተኛ ይሆናል። አካባቢያቸውንም በደንብ እንዳያውቁት እንቅፋት ይሆንባቸዋል።
 • እየበሉ ሳይንቀሳቀሱ ስለሚቆዩ በዘመኑ አሳሳቢ ለሆነው ውፍረት (obesity) ይጋለጣሉ፤ በዚህ ሳቢያ ለሚከሰቱ የጤና ችግሮች ሊጋለጡ ይችላሉ።
 • ለወደፊት ለጾታ ግንኑኝነት ያለቸው አመለካከት የተዛባ ይሆናሉ፤ ተጨባጩን ዓለም ሳይሆን ሰው ሠራሹን ዓለም ናፋቂ ይሆናሉ፤ ሁል ጊዜ አዲስ ነገር ናፋቂዎች ይሆናሉ።
 • የሥነ ልቦና ጫና ያደርግባቸዋል፤ በትምህርት ቤት አና በቤተሰብ ያለው ግንኙነት የሻከረ ነው፤ ብቸኝነት ያጠቃቸዋል። ራሳቸውን እሰከ ማጥፋት ይደርሳሉ። ሱስ ስለሚሆንባቸው ሁልጊዜ ያያሉ። ሌሎችንም ወደ እዚህ ይመራሉ።
 • እራሳቸውን በደንብ ስለማይጠብቁ በመልካቸው፣ በአለባበሳቸው እና በቤተሰባቸው ማንጓጠጥ (bullying) ይደርስባቸዋል።

የመርጃ ቴክኖሎጂውን ለልጆቻን አንዴት አንጠቀም?

በአደጉ ሀገሮች ይህን ችግር ለመቆጣጠር በመንግሥት፣ የኢንተርኔት መስመር አከራዮች እና በትምህርት ቤት የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ። ወላጆችም በቤት የወላጅ መቆጣጠሪያ (Parental control) ይጠቀማሉ። ለቤተሰቡ ሁሉ የየራሱ መግቢያ እና ማለፊያ ይኖረዋል፤ ወላጅ ብቻ የሚጠቀምባቸውን ፋይሎች እና ሌሎች መረጃዎችን ልጆች እንዳያይዋቸው ይረዳል። ወላጅ የሚፈልጉትን ድረ ገጾች ብቻ መምረጥ እና ሌሎችን በኮምፒውተሩ እንዳይከፍቱ ማድረግ ይችላል። ወይም ወላጅ መክፈት የሌለባቸውን ድረ ገጾች ወሳኝ ቃላቶችን በመጠቀም መከላከል ይቻላል። የተወሰኑት ሶፍቴዎሮች ልጆች የድምፅ እና የምስል መልእክት ኮምፒዊተሮችን ተጠቅመው እንዳያሰተላልፉ ይረዳል። የልጆችን አጠቃላይ በኢንተርኔት ላይ ያላቸውን እንቅስቃሴ ሪፖርት ያደርጋል። ምን ድረ ገጽ እንደጎበኙ፣ ለምን ያህል ሰዓት፣ ከማን ጋር አንደተገናኙ ያሳያል። ወላጆች ለልጆቻቸው ለምን ያህል ጊዜ ኮምፒውተር ላይ መቀመጥ እንዳለባቸው ገደብ ለማድረግ ይረዳል፤ ልጆች ከተፈቀደላቸው በላይ ሲጠቀሙ ለወላጆች መልእክት ይሰጣል። እነዚህ ሁሉ መፍትሔዎች ችግሩን ቢያቀሉትም ፈጽሞ እንዳይከሰት ማድረግ አልቻሉም።

ከእነዚህ መፍትሔዎች ጋር የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ወላጆች ከልጆች ጋር የቀረበ ግንኙነት እንዲኖራቸው ማድረግ፤ ምንም ከወላጅ የተደበቀ ነገር እንዳይኖር ማድረግ ያስፈልጋል። ልጆችን ከወላጅ በላይ ማንም ሊረዳቸው እና ሊግባባቸው አይችልም። የተከሰቱትን ችግሮች ሁሉ ለመፍታት የተከሰተውን ነገር ልጆች በግልጽነት እንዲያወያዩን ማድረግ ከዚህ ከኢንተርኔት አጠቃቀም ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት መፍትሔ ይሆናል። ልጆች ስለሚነግሩን ነገር ለመረዳት ስለ ኢንፎርሜሺን ቴክኖሎጂ መሠረታዊ እውቀት ሊኖረን ይገባል። ልጆች 13 (አሥራ ሦስት) ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ሶሻል ሚድያ (ፌስ ቡክ፣ ትዊተር) መጠቀም እንደማይችሉ ማስረዳት። ልጆች ከእኛ በላይ እንዲሚያውቁ ሆነው ሊሰማቸው አይገባም። ወላጆች ልጆች ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ላይ ሳይሆን ቴክኖሎጀውን በመሥራት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ልጆችን በተላያየ ቦታ የሚዘጋጁ ሳይንስ ነክ የሆኑ ዓውደ ርዕይዎችን እንዲዩ  ማደረግ ይገባል።

በአግባቡ እየመረጡ የልጆች ተሌቪዥን ሥርጭት እና የተመረጡ ፊልሞች እንዲመለከቱ ቢደረግ በርካታ ቁምነገሮች ሊቀስሙ፣ መልካም የሚባል ማኅበራዊ፣ ሞራላዊ እሴቶችን ሊያዳብሩ ይችላሉ። ውጤታማ የቴሌቪዥን አጠቃቀም የሚከተሉትን ተግባራት ይጠይቃል:-

 • ልጆች ምን ማየት እንዳለባቸው መለየት (አመፅ፣ ድብደባ፣ የአዋቂዎችን ጉዳይ እንዳይመለከቱ መጠንቀቅ)።
 • ቤተሰባዊ ጉዳዮች ላይ እና በሕፃናት ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ እና የሚያተኩሩ ዝግጅቶችን እንዲመለከቱ ማበረታት።
 • ተፈጥሮን ማወቅ፣ ማድነቅ የሚችሉባቸውን፣ ተፈጥሮን የሚያስቃኙ ዝግጅቶችን እንዲመለከቱ ማገዝ።
 • በቀን ውስጥ ቴሌቪዥን የሚመለከቱበትን የሰዓት ገደብ መወሰን፣ ጥሩ ነገር ሲሠሩ እንደ ሽልማት እንዲሆናቸው ማድረግ።
 • አብሮ እየተመለከቱ ስለሚተላለፈው ነገር አንዳንድ ጥያቄዎችን በማቅረብ የሚያዩትን ነገር መረዳታቸውን መገምገም።
 • በሚያዩት ነገር እና በእውኑ ዓለም መካከል ያለውን ልዩነት ማስረዳት።
 • ልጆች የግል መረጃዎችን (ኢሜይል፣ ስልክ፣ የቤት አዳራሻ) ለማያውቁት ሰው መቼም መስጠት የለባቸውም።
 • መቼም ልጆች የግል ማለፊያዎችን (Password) ለማንም መስጠት የለባቸውም። ማለፊያዎችን (Password) በየጊዜው መቀየር መቻል አለባቸው።
 • በሶሻል ሚድያ የሚለቋቸው ጽሑፎች፣ ፎቶግራፎች ሰውን የሚያናዳዱ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ፤ የሌሎችንም ፎቶግራፍ ባሌቤቱን ሳይስፈቅዱ አለማስቀመጥ።
 • ከማን እንደተላከ የማይታወቅ የኢሜይል መልእክት ልጆች መክፈት የለባቸውም።
 • የገንዘብ ነክ መረጃዎችን ልጆች ከወላጆች ጋር ብቻ እንዲጠቀሙ ማድረግ ለባንኮች ክፍያ ለመጠቀም ልጆች የማያውቁት ተጨማሪ ማለፊያ መጠቀም።
 • በኢንተርኔት ጓደኝነት የሚጠይቁ ሰዎችን የሚያውቋቸውን ብቻ ማድረግ።
 • ልጆች በኢንተርኔት ብቻ ጊዜያቸውን እንዳያጠፉ ሌሎች በኮምፒውተር የሚሠሩ ነግሮችን ማዘጋጀት።
 • ሰለ ቤተሰብእ የእረፍት ጉዞ፣ በቤት ስለሚዘጋጅ ዝግጅት፣ አብረው ሰለሚኖሩ ስዎች መረጃ በሶሻል ሚዲያ ማውጣት የለባቸውም።

ማጠቃለያ

ለልጆች የሰውነት ቅመምን፣ የሕይወትን ጣዕምና ትርጉምን እንዲሁም የስኬትን መንገድ የማመላከት ሚና በቀዳሚነት የወላጅ ድርሻ መሆኑን ወላጆችም፣ ልጆችም፣ ባለሙያችም የሚያሰምሩበት ጉዳይ ነው።

በአጠቃላይ ልጆች በተጠመዱባችው ሱሶች አማካይነት ጸያፍ ንግግሮችን፣ ደባል ሱሶችን፣ አመፅን፣ ልቅ ወሲባዊ  ድርጊቶችን፣ ኢ-ሥነ ምግባራዊ ተግባሮችን ይማራሉ፤ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ልማዶች ወረዋቸው በዕድሜያቸው ሊሠሯቸው የሚገቧቸውን ሥራዎች እንዳይሠሩ ይከለክሏቸዋል። ከመደበኛው ትምህርታችው ያዘናጋቸዋል። እነዚህን የቴክኖሎጂ አፍራሽ ተፅዕኖዎች ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ባይቻልም መቀነስ ግን ይቻላል። ወላጆች ልጆቻቸውን ከነዚህ ነገሮች ለመታደግ ጠንካራ ሥራ ይጠበቅባቸዋል፤ በጊዜያቸው በሕይወታቸው በማንነታቸው እና በውጤታቸው ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ውጤት ከግምት በማስገባት የኤሌክትሮኒክስ አጠቃቀማቸው ላይ ገደብ ማበጀት፣ ልምድ ማካፈል፣ ዕድሜያቸውን ያላገናዘቡ መልእክቶችን እንዳይታደሙ መጠንቀቅ፣ ከሚመለከቷቸው ነገሮች ጠቃሚ ቁም ነገሮችን ብቻ እየመረጡ እንዲጠቀሙ ግንዛቤያቸውን ማዳበር፣ የራሳቸውን ማንነትና የማኅበረሰባቸውን ማኅበራዊ እሴቶች እንዲያውቁ ማድረግ፣ ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ መከታተል፣ ትምህርታቸውን በአግባቡ መከታተላቸውን መገምገም ወዘተ የወላጆች ሓላፊነት ሊሆን ይገባዋል።

* ፈሰሴ ገብረሐና ፣ በላቸው ጨከነ – የልጆች አስተዳደግ በዚህ ዘመን ተግዳሮቶች እና መፍትሔዎች። ሎንዶን ፳፻፮ ዓ.ም. ከታተመው መጽሐፍ ለዚህ መጽሔት የተዘጋጀ
** ይህ ጽሑፍ በኢ/ኦ/ተ/ቤት ክርስቲያን በሰ/ምዕራብ አውሮፓ ሀገር ስብከት በፊንላንድ የሄልሲንኪ ደበረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በ፳፻፲ ዓ.ም. ባሳተመው መጽሔት ላይ የወጣ ነው።