አምስተኛው ሐዊረ ሕይወት በአገረ ጀርመን ተካሄደ

በጀርመን ንዑስ ማዕከል

መጋቢት 25 ቀን 2010 ዓ.ም.

የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ለ፭ተኛ ጊዜ በጀርመን አገር ፍራንክፈርት ከተማ አቅራቢያ በክሮፍልባህ የግብፅ ቅዱስ እንጦስ ገዳም “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።” (ማቴዎስ፭÷፲፮) በሚል መሪ ቃል ተካሄደ። በዚህውም ጉባኤ ብፁዕ አቡነ ሚሻኤል የቅዱስ እንጦንስ ገዳም የበላይ ጠባቂ፣ በጀርመን የኢ/ኦ/ቤ/ክ አስተዳዳሪዎች እና የሀገረ ስብከቱ ካህናትና ዲያቆናት፣ ከኢትዮጵያ እና ከሌሎች አውሮፓ ሀገራት ተጋባዥ መምህራን እንዲሁም ዘማሪያን ተገኝተዋል። በተጨማሪም 400 የሚሆኑ ምዕመናን በጉዞው ላይ ተሳትፈዋል።

የጉዞው መነሻ ዓርብ ዕለት መጋቢት 14/2010 11:00 ሰዓት ላይ ከፍራንክፈርት ባቡር ጣቢያ ሲሆን ምዕመናን እርስ በእርስ እየተወያዩ ከአንድ ሰዓት በኋላ  የጉዞው መዳረሻ ወደሆነው የርዕሰ መነኮሳት ቅዱስ እንጦንስ ገዳም ደርሰዋል። በአስተባባሪዎች አማካኝት የማረፊያ ቦታ ከተሰጠ በኋላ የመጀመሪያው ቀን የምሽት መርሐ ግብር በአባቶች ቡራኬ ተጀምሮ የ‘እንኳን ደኅና መጣችሁ’ ንግግር በቀሲስ ዶ/ር ያብባል ሙሉዓለም (የአውሮፓ ማዕከል ሰብሳቢ) እና ስብከተ ወጌል በዲያቆን ያረጋል አበጋዝ  ተሰጥቷል።

በዕለተ ቅዳሜ ጠዋት ላይ ጸሎተ ቅዳሴ የተካሄደ ሲሆን በማስከተልም እስከ ምሳ ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ “ነገረ ቤተክርስቲያን (አቅሌስያ)”ን አስመልክቶ ሰፊ ትምህርት በዲያቆን ያረጋል ተሰጥቷል።  ከሰዓት በኋላ በነበረው መርሐ ግብርም ቀሲስ ዶ/ር ያብባል “ማኅበረ ቅዱሳን ማነው?” በሚል ርዕስ ስለ አውሮፓ ማዕከል አመሠራረት እና አሁን የአውሮፓ ማዕከል ምን እየሠራ እንዳለ ለተሳታፊው ገለፃ አቅርበዋል። በመቀጠልም የ‘ስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮጀክት’ ዙሪያ በምስል ወድምፅ የታገዘ ገለፃ በዲ/ን ገብረ ሕይወት (የጀርመን ን/ማዕከል ሰብሳቢ) ቀርቧል። በገለፃውም ላይ ስለ አዳዲስ ተጠማቂያን፣ በቀጣይ ሊሠሩ ስለ ታቀዱ ሥራዎች እና የምዕመናንን ድጋፍ የሚፈልጉ ሥራዎች ተዳስሰዋል።

 

“በጎ ሥራ በነገረ ድኅነት” በሚል ርዕስ በዲያቆን መስፍን ኃይሌ በሁለት ክፍል ትምህር የተሰጠ ሲሆን በመቀጠልም የዕለቱን ትምህርት አስመልክቶ ያሬዳዊ ዝማሬ በመልአከ ስብሐት ተክሌ ሲራክ (በጀርመን ፍራንክፈርት ደ/ኃይል ቅዱስ ዑራኤል ወቅዱስ ያሬድ አስተዳዳሪ) እና በዘማሪት ሶስና የበገና ዝማሬ ቀርቧል። መልአከ ኃይል አባ ዘድንግል የዳርምሽታድ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት አስተዳዳሪ እና የሀገረ ስብከቱ ተወካይም አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በመጨረሻም ከምዕመናን ለቀረቡ መንፈሳዊ ጥያቄዎች በተባጋዥ መምህራን እና በአባቶች ተሰጥቶ የዕለት ቅዳሜ  መርሐ ግብር ተጠናቋል።

በማግሥቱ በዕለተ ሰንበት የዐቢይ ጾም ፯ተኛ ሳምንት (ኒቆዲሞስ) በአቡነ ሚሻኤል መሪነት በተከናወነው ፀሎተ ቅዳሴ ተሳትፎ በኋላ የምሳ ሥርዓት ተደርጎ የጉዞ ዝግጅቱ ተጠናቋል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር !