የጣሊያን ንዑስ ማእከል አውደ ርእይ አካሄደ
በጣሊያን ንዑስ ማእከል
ሰኔ 25 ቀን 2009 ዓ.ም.
ማኅበረ ቅዱሳን የጣሊያን ንዑስ ማእከል ግንቦት ፲፱ እና ፳ ፳፻፱ ዓ/ም ከሮም ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም እና ቅዱስ ኡራኤል ቤተክርስቲያን ጋር በመተባበር “ አብረን እንስራ ለውጥም እናመጣለን!” በሚል መሪ ቃል ዐውደ ርእይ አካሄደ። ዐውደ ርእዩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሕገ ልቡና በሕገ ኦሪትና በሕገ ወንጌል ያደረገችው ጉዞ፣ የገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶችን ታሪክ እና አሁን ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ፣ ዝክረ ቅዱስ ያሬድ እና ማኅበረ ቅዱሳን በሚሉ አራት ዓቢይ ክፍሎች የተከፈለ ነበረ።
ዓውደ ርዕዩ ከመካሄዱ በፊት ለምእመናን ስለገዳማት አጭር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስብከተ ወንጌል ተሰጥቷል። ዐውደ ርእዩን የከፈቱት በሮም ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም እና ቅዱስ ዑራኤል ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ቆሞስ መልአከ ፀሐይ አባ ሰላማ ወልደ ሳሙኤል ሲሆኑ ምእመናንም ዐውደ ርእዩን ከተከታተሉ በኋላ ሰለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሐዋሪያዊ ጉዞ የበለጠ ግንዛቤ እንዳስጨበጣቸው ይልቁንም የእምነታችን መሰረት የሆኑትን ገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች ላይ ማኅበረ ቅዱሳን እየሰራ ያለውን ሥራ የሚያሳይ መረጃ በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው ወደ ፊት ከማኅበሩ ጋር በመተባበር በጋራ ገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶችን ለመርዳት ቃል ገብተዋል። በአውደ ርዕዩ ላይ በውጪ ሃገር ተወልደው ላደጉ ህጻናት እና ታዳጊዎችን ታሳቢ በማድረግ ተጨማሪ ትዕይንቶችን በጣሊያንኛ ማዘጋጀቱ አበረታች ጅምር መሆኑን ገልፀው ንዑስ ማእከሉ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
ዐውደ ርእዩ ለሁለት ቀናት ክፍት ሆኖ በምእመናን የተጎበኘ ሲሆን ከ 100 በላይ የሚሆኑ የአጥቢያው ምእመናን ጎብኝተውታል። የጣሊያን ንዑስ ማዕከል በነበረበት አንዳንድ ክፍተቶች ምክንያት ጠንካራ እንቅስቃሴ ሳያደርግ የቆየ ቢሆንም ከዚህ በኋላ ግን በአዲስ መልክ ከደብሩ አስተዳዳሪ፣ ከሰበካ ጉባኤው እንዲሁም ከምእመናን ጋር ለመሥራት ይህ አውደ ርዕይ ተስፋ ሰጪ ጅምር ነው።