፲፭ ኛው የአውሮፓ ማዕከል ጠቅላላ ጉባዔ ሊካሄድ ነው
ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም.
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ሰ/ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማዕከል ፲፭ኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በጀርመን ሀገር ፍራንክፈርት ከተማ ሊያካሂድ ነው። ከሰኔ ፳፮ እስከ ፳፰ ቀን ፳፻፯ዓ.ም. በሚቆየው በዚህ ጉባዔ፦
- የደቡብ ፣ የደቡብ ምሥራቅ እና የደቡብ ምዕራብ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሙሴ እና የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ
- የሰሜን ምዕራብ ሀገረ ስብከት ተወካይ
- በጀርመን የሚገኙ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እና አባቶች
- በተለያዩ የአውሮፓ ሃገራት የሚኖሩ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት እንዲሁም ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች እንደሚሳተፉበት ይጠበቃል።
ጉባዔው የተሳካ ይሆን ዘንድ ጊዜአዊ የመረጃ መረቦች በተለያዩ የማኅበራዊ ድረ ገጾች የተዘረጉ ሲሆን ማዕከሉ ባለፈው ዓመት ፲፬ኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በጣሊያን ሮም ከተማ ማካሔዱም ይታወሳል።
ማኅበረ ቅዱሳን ከሀገር ውጪ ካሉት አራት ማዕከላት አንዱ የሆነው የአውሮፓ ማዕከል የተመሠረተው በ፲፱፻፺፫ ዓ.ም. ለትምህርት ወደ አውሮፓ በመጡ እና በአውሮፓ ኗሪ በሆኑ የማኅበሩ አባላት እንደሆነ ይታወቃል። ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት በአምስት ቀጣና ማዕከላት እና በሰባት ግንኙነት ጣቢያዎች በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት አገልግሎቱን እየፈጸመ ይገኛል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!