የአውሮፓ ማዕከል ፲፭ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በፍራንክፈርት ፥ ጀርመን አካሄደ
በብዙኀን መገናኛ እና ቴክኖሎጂ አገልግሎት ክፍል
ሐምሌ 02 ቀን 2007 ዓ.ም.
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደረጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማዕከል አስራ አምስተኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በጀርመን ሀገር በፍራንክፈርት ከተማ በምትገኘው በደብረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከሰኔ ፳፮ እስከ ፳፰ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. አካሄደ።
በጉባኤው ላይ ብፁዕ አቡነ ሙሴ የደቡብ፣ ምሥራቅና ምዕራብ አውሮፓ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ መጋቤ ምሥጢር ኅሩይ ኤርምያስ የደቡብ ምሥራቅና ምዕራብ አኅጉረ ስብከት ዋና ጸሐፊ፣ የዋናው ማዕከል እና የአሜሪካ ማዕከል ተወካዮች እንዲሁም በጀርመን የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት የደብር አስተዳዳሪዎች እና ከመላው አውሮፓ የተሰባሰቡ ከ፺ በላይ የሚሆኑ የማኅበሩ አባላት ተገኝተዋል።
ሰኔ ፳፮ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ቀትር ጀምሮ እንግዶች ወደ ጉባኤው ቦታ ፍራንክፈርት ደብረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የደረሱ ሲሆን ጉባኤው ሠርክ ላይ በአባቶች መሪነት በጸሎተ ኪዳን ተጀምሮ በዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል። በመቀጠልም የእራት መስተንግዶ በጀርመን ቀጣና ማዕከል ከተደረገ በኋላ በጠቅላላ ጉባኤው አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ደረጀ ወርቁ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ተላልፎ በመጨረሻም የአባላት የእርስ በርስ የትውውቅ መርሐ ግብር ከተከናወነ በኋላ የእለቱ መርሐ ግብር ፍጻሜ ሆኗል።
ሰኔ ፳፯ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ጠዋት ጸሎተ ወንጌል (ማቴ.፯ ፥ ፳፬) በብጹዕ አቡነ ሙሴ መሪነት ደርሶ ቀሲስ ለማ በሱፍቃድ «እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ልጅ የቱ ነው?» (ሉቃ.፲፭ ፥ ፲፩ – ፴፪) በሚል ርዕስ ትምህርት ሰጥተዋል። ቀጥሎም የማዕከሉ ሰብሳቢ ዲ/ን ሰሎሞን አስረስ ለተጋባዥ እንግዶች እና ለማዕከሉ አባላት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት አስተላልፈዋል። የ፳፻፯ ዓ.ም. የማዕከሉ የአገልግሎት ክፍሎች እና የማዕከላት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በማዕከሉ ሰብሳቢ የቀረበ ሲሆን ጉባኤው የሂሳብ፣ የኦዲትና ኢንስፔክሽንን ዕቅድ ክንውን ሪፖርት ካዳመጠ በኋላ በሪፖርቱ ላይ ሰፊ ውይይት አድርጓል። ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችም የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ አባላት ማብራሪያ እና ምላሽ ከሰጡ በኋላ አጠቃላይ ኃሳቦች በብጹዕ አቡነ ሙሴ እና በተጋበዙ እንግዶች ተሰጥተው ሪፖርቱን ጉባኤው አጽድቆታል።
የደቡብ፣ ምሥራቅና ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከትን መልእክት ያስተላለፉት ዋና ጸሐፊው መጋቤ ኅሩይ ኤርምያስ ማዕከሉ ለሀገረ ስብከቱ እያደረገ ላለው ድጋፍ አመስግነው ወደፊትም ከማዕከሉ ጋር አብሮ ለመሥራት ሀገረ ስብከቱ ዝግጁ እንደሆነ ተናግረዋል። «በማዕከሉ የተሠሩ ሥራዎችንÂ በማየቴ ተደስቻለሁ፤ እኛ ያላየናቸውን የአገልግሎት ክፍተቶች በማየታችሁ ፣ በመሥራታችሁ እግዚአብሔር ይስጣችሁ » በማለት ዋና ጸሐፊው መልእክታቸውን ቋጭተዋል። ሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ገብረ ሕይወት ፍሥሐ በበኩላቸው «ከዋክብት ሰማይን ፣ አበቦች ምድርን እንደሚያስጌጡ ሁሉ ፣ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን ጌጦች ናቸው፤ እናንተም ለቤተ ክርስቲያን ጌጦች ናችሁ» በማለት ማኅበሩ በአገልግሎት እንዲተጋ አበረታትተዋል።
በመጨረሻም ብጹዕ አቡነ ሙሴ ባስተላለፉት መልእክት ማኅበሩ በተለይም ግቢ ጉባኤያትን በማስተማር እና የተዘጉ ገዳማት እና የአብነት ትምህርት ቤቶችን በማስከፈት በቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉትን ብዙ ክፍተቶች ሸፍኗል። አሁንም ማኅበሩ ይህንን መልካም ሥራውን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል ሲሉ ብፁዕነታችው መልእክታቸውን ለጉባኤው አስተላልፈዋል። ወደፊትም ማዕከሉ ከሀገረ ስብከቱ እና ከአባቶች ጋር ከዚህ የበለጠ ተቀራርቦ እንዲሠራ በማለት መመሪያ ካስተላለፉ በኋላ የጠዋቱን መርሐ ግብር በጸሎት ዘግተዋል።
በእለቱ ከምሣ መስተንግዶ መልስ በመልአከ ስብሐት ተክሌ ሲራክ በጀርመን የካርልስሩኸ ምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ወረብና መዝሙር፣ በማዕከሉ አባላት ወረብ እንዲሁም በጀርመን የሙኒክ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ በሆኑት በሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ገብረ ሕይወት ፍሥሐ መዝሙር ቀርቧል። በዚሁ እለት ከሰዓት በኋላ ጉባኤው ሰፊ ጊዜ ሰጥቶ የተወያየበት አንዱ ርዕሰ ጉዳይ «በውጭው ዓለም የሚገኙ ሕፃናትን በቤተ ክርስቲያን በተቀናጀ መልኩ እንዴት እናተምር?» የሚል ነው። በዚህም ርዕሰ ጉዳይ ላይ ችግሮችን ፣ መፍትሔዎችን እና ተሞክሮዎችን የዳሰሰ ጥናት ለጉባኤው ቀርቧል። በቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ዙርያ በተደረገው ውይይት ማኅበሩ ከዚህ በፊት የቀረፀው ሥርዓተ ትምህርት መኖሩ ተወስቶ ወደፊት ግን በአዲሱ የውጭ ማዕከላት መዋቅር መሰረት ሕፃናት እና አዳጊ ወጣቶችን የማስተማር ሥራ እራሱን በቻለ «የተተኪ ትውልድ ሥልጠና» በሚባል ክፍል ተመስርቶ በርካታ ውጤታማ ሥራዎችን መሥራት እንዳለበት አፅንኦት ተሰጥቶበታል።
ከዚህ በመቀጠልም «ሚዲያ ለቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ እድገት» በሚል ርዕስ ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን በርካታ ገንቢ ኃሳቦች ተሰጥተዋል።
በዚሁ እለት ምሽት ከእራት በኋላ ከዋናው ማዕከል ተወክለው በመጡት አቶ ፋንታሁን ዋቄ « የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እና ተግዳሮቶች » በሚል ርዕስ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችም ማብራሪያ በጽሑፉ አቅራቢ ተሰጥቶባቸዋል። የዕለቱ መርሐ ግብርም መንፈቀ ሌሊት ሲሆን ተፈጽሟል።
ጉባኤው እሑድ ሰኔ ፳፰ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ከቅዳሴ በኋላ እኩለ ቀን ላይ ቀጥሎ የተሻሻለውን የውጭ ማዕከላት መመሪያና መዋቅር አተገባበርን በተመለከተ ውይይት ተደርጓል። የማዕከሉ የአገልግሎት ክፍሎች እና የኦዲት እና ኢንስፔክሽን የመጪው ዘመን የ፳፻፰ ዓ.ም. ዕቅድ ቀርቧል። በእቅዱ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ አባላቱ ማብራሪያ እና ምላሽ ከሰጡ በኋላ እቅዱ በጠቅላላ ጉባኤው ጸድቋል።
በመቀጠልም ሕጻናት መዝሙር አቅርበው ፣ የሰሜን አሜሪካ ማዕከል ተወካይ ዲ/ን ብዙአየሁ ልመንህ የማዕከሉን መልእክት ካስተላለፉ በኋላ የማዕከላቸውን ልምድ ለጉባኤው አካፍለዋል። እንዲሁም ሁለቱ ማዕከላት በጋራ ሊያገለግሉባቸው የሚችሉባቸውን የአገልግሎት ዘርፎች ለጉባኤው አቅርበዋል። የዋናው ማዕከል መልእክትም በተወካዩ በአቶ ፋንታሁን ዋቄ ለጉባኤው ቀርቧል።
በመጨረሻም የማዕከሉ ሰብሳቢ ዲ/ን ሰሎሞን አስረስ ለዚህ ጉባኤ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉት መልአከ ፀሐይ ቆሞስ አባ ሲራክ ተድላ የፍራንክፈርት ደብረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ፣ ለቤተ ክርስቲያኗ ሰብካ ጉባኤ፣ አባታዊ ምክርና ገንቢ አስተያየቶችን በመስጠት ለጉባኤው ሞገስ ለሆኑት አባቶች ፣ ተወካይ በመላክ ልምዳቸውን እንድናገኝ ላደረገው የሰሜን አሜሪካ ማዕከል እንዲሁም ፲፭ኛውን ጠቅላላ ጉባኤ ላዘጋጁት የጀርመን ቀጣና ማዕከል አባላት ከፍተኛ ምስጋና አቅርበው፣ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ የተነሱና ውሳኔ ያገኙ ጉዳዮችን ለመተግበር ሁሉም አባላት እንዲተባበሩ ጥሪ በማስተላለፍ ፲፭ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ተጠናቋል። ቀጣዩን የማዕከሉን ፲፮ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ለማዘጋጀት የዩኬና የኔዘርላንድ ማዕከላት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን የማዕከሉ ሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ ነባራዊ ሁኔታዎችን በማገናዘብ ወስኖ ለአባላት እንደሚገልጽ አሳውቋል።
በጉባኤው ማግስት ሰኞ ሰኔ ፳፱ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. የተወሰኑት አባላት ከፍራንክፈርት የአንድ ሰዓት ገደማ ርቀት ላይ ወደሚገኘው የግብፅ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ እንጦስ ገዳም በመሄድ ጉብኝት አድርገዋል።