በጀርመን ድሶልዶርፍ የጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ።

በጀርመን ን/ማእከል ኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ክፍል

ግንቦት 24 ቀን 2008 ..

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በደቡብ ምሥራቅ እና ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት በጀርመን ድሶልዶርፍ የጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ሙሴ ሚያዚያ 16 ቀን 2008 .. በእለተ ሆሳዕና ተባርኮ ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ።

gemanabuye

በዓሉን አስመልክቶ ትምህርት እና ቡራኬ የሰጡት የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሙሴ በቤተ ክርስቲያኑ መከፈት ምእመናኑን እንኳን ደስ ያላችሁ በማለት ለቤተክርስቲያኑ መመስረት አስተዋጽኦ ያደረጉትን ሁሉ አመስግነዋል፡፡ በዱሰልዶርፍ እና አካባቢው የሚኖሩ ምእመናን ብዙ በመሆናቸው እና ባደረጉት ቅን ትብብር ለቤተ ክርስቲያኗ የሚያስፈልገውን ንዋያተ ቅድሳት በማሟላት ቤተ ክርስቲያኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ መከፈት መቻሉን ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም ወደፊትም ምእመናን የጎደለውን በማሟላት እና የቤተ ክርስቲያኗ አገልግሎት በተጠናከረ ሁኔታ እንዲቀጥል በማድረግ በኩል የሚጠበቅባቸው ኃላፊነት ትልቅ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከኢትዮጵያ የመጡ መምህራን እንዲሁም ከመላው ጀርመን የመጡ በርካታ ምእመናን ተሳታፊዎች ነበሩ።

በዓሉ ዋዜማ ቅዳሜ ሚያዚያ 15 ቀን 2008 .ም በዲ.ን ዶክተር ቴዎድሮስ በለጠ ‘‘እስራት እንዳይበዛባችሁ አታፊዙ’’ ኢሳ. ፳፰፥፳፪ በሚል ርዕስ ለተሳታፊ ምእመናን ሰፊ ትምህርት ተሰጥቷል። እንዲሁም እሁድ ሚያዚያ 16 ቀን 2008 .“ ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን” ፪ኛ ቆረ. ፱፥፲፭ በሚል ርዕስ ትምህርት ወንጌል በዲ.ን ሄኖክ ኃይሌ ተሰጥቷል።

እሁድ ሥርዓተ ቅዳሴው እንደተጠናቀቀ ቤተክርስቲያኑን እንዲያስተዳድሩ ቄስ ቤዛ መንግስቱ በብፁዕ አቡነ ሙሴ የተሾሙ ሲሆን እርሳቸውም የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንደሚወጡ በዮሐንስ ፥፩ ፲፮ ያለውን የወንጌል ክፍል በማንበብ ቃል ገብትዋል። ምእመናኑም ሹመታቸውን ሦስት ጊዜ ይደልዎ በማለት በቤተክርስቲኗ የቆየ ትውፊት መሠረት መቀበሉን ገልጿል።

gemanabuye2

ይህ በዱሰልዶርፍ ከተማ የተተከለው የጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን በቄስ ቤዛ መንግስቱ አነሳሽነት እና በድሶልዶርፍ አካባቢ ተሰባስበው በነበሩ ምዕመናን ጥረት የተጀመረ ሲሆን በጀርመን አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ በኢ//// አብያተ ክርስቲያናትን ቁጥር አሥራ አራት አድርሶታል።