በማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማዕከል 17ኛውን ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ።
በአውሮፓ ማእከል ኅ/ኤ/ሚዲያ ክፍል
ሐምሌ 8 ቀን 2009 ዓ.ም.
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደረጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል አስራ ሰባተኛውን ጠቅላላ ጉባኤ “ታገኙ ዘንድ ሩጡ “፩ቆሮ ፱÷፳፬ በሚል መሪ ቃል በጀርመን ክሮፍልባህ የግብፅ ቅዱስ እንጦስ ገዳም የአካባቢው አቢያተ ክርስቲያናት አስተዳዲሪዎች ፣ የሀገረ ስብከቱ ተወካይ፣ የማኅበሩ አባላት እና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ከዓርብ ሰኔ ፴ እስከ እሁድ ሐምሌ ፪ ቀን አካሄደ።
በመክፈቻው ዕለት ዓርብ ጠቅላላ ጉባኤው በፀሎት ተጀምሮ የእንግዶች አቀባበልና የአባላት የእርስ በእርስ ትውውቅ ከተካሄደ በኃላ በአባቶች ቡራኬ ተሰጥቶ ተጠናቋል። ቅዳሜም ጸሎተ ቅዳሴ ተከናውኖ ጉባኤ የተጀመረ ሲሆን በጉባኤውም መምህር ዲያቆን ሄኖክ “እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው”ዘኊ ፲፪፥፯ በሚል ርዕስ መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ ያተኮረ ትምህርት ተሰጥቷል። በመቀጠልም የማእከሉ የ2009 ዓ.ም. የአገልግሎትና የሂሳብ ሪፖርት በማእከሉ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ያብባል የቀረበ ሲሆን እንዲሁም የኦዲትና ኢንስፔክሽን ሪፖርት እና የንዑስ ማእከላትና ግንኙነት ጣቢያዎች ሪፖርት ለጉባኤው ቀርቧል። በሪፖርቶች ላይ ለገዳማት እና አብነት ትምህርት ቤቶች እና ለስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን፣ በተለያዩ ቦታዎች የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብሮች መካሄዳቸውን እና አዳጊ ሕፃናት ላይ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ተገልጿል። የዋናው ማዕከል መልዕክትም በዋናው ማዕከል ተወካይ እና የማኅበር ቅዱሳን ዋና ፀሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ የቀረበ ሲሆን በተጨማሪም የደቡብ ምሥራቅና ምዕራብ አውሮፓን ሀገረ ስብከት ተወካይ መልአከ ኃይል ቆሞስ አባ ዘድንግል በጀርመን ዳርምሽታድ ከተማ የሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት አስተዳዳሪ የሀገረ ስብከቱን መልእክት አስተላልፈዋል። በማእከሉ የ6 ዓመት ስልታዊ አቅጣጫዎች ላይ የተደረገው ገለፃና ውይይት የቅዳሜ መርሐ ግብር አንዱ አካል ነበር።
እሑድ ከቅዳሴ በኋላ በቀጠለው ጉባኤ የ2010 ዓ.ም. የማእከሉ እቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። የአሜሪካን ማእከልን ወክለው ጉባኤው ላይ የተገኙት ዶ/ር አዲስ አስመላሽም የአሜሪካ ማእከልን መልዕክት እና የአገልግሎት ተሞክሮ አቅርበዋል። በመጨረሻም የጠቅላላ ጉባኤው አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ የመርሐ ግብሩን አጠቃላይ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን ጉባኤው ላይ እንግዳ በመቀበል እና በመስተንግዶ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉትን የጀርመን ንዑስ ማእከል አባላትና የአከባቢው ምእመናንን አመስግነዋል።
በዚህ ሶስት ቀን በቆየው ጉባኤ ላይ በማእከሉ መዘምራን የተለያዩ ጣዕመ ዝማሬዎችን እና ወረብ፣ ዝማሬ በህፃናት እንዲሁም ወረብ በመልአከ ስብሐት ተክሌ ሲራክ ቀርቧል።