በጀርመን በርሊን ዐውደ ርእይ እና ስብከተ ወንጌል መርሐግብር ተካሄደ

በጀርመን ንኡስ ማእከል

ጳጕሜ 3 ቀን 2008 ..

በጀርመን ርእሰ ከተማ በበርሊን ነሐሴ እና ፳፻፰.ም “ለሁለንተናዊ የቤተክርስቲያን እድገት የድርሻችንን እንወጣ” በሚል መሪ ቃል የዐውደ ርእይ እና የስብከተ ወንጌል መርሐግብር ተካሄደ። ይህንን በማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል ከበርሊን ደብረ ገነት ቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጋር በመተባበር ያዘጋጁትን መርሐግብር የከፈቱት የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ብርሃነ መስቀል ተድላ ሲሆኑ ዐውደ ርእዩን ብዙ ምእመናን ጎብኝተውታል። ዐውደ ርእዩ ፍኖተ ቤተከርስቲያን፣ ገዳማት እና የአብነት ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ማኅበረ ቅዱሳን የሚሉ ሦስት ትዕይንቶችን ያካተተ ነበር። በተለይም የኢትዮጵያ ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ለእምነትና ለታሪክ መጠበቅ እና ለዕውቀት፣ ትውፊትና ባሕል ከትውልድ ወደ ትውልድ መሸጋገር ያበረከቱትና እያበረከቱት ያለው አስተዋኦ እንዲሁም አሁን ያሉበት ወቅታዊ ችግሮቻቸው በሰፊው የተገለጸ ሲሆን ችግሮቹን ለመፍታት ማኅበረ ቅዱሳን እየወሰዳቸው ያሉ በርካታ ጊዜያዊ እና ዘላቂ መፍትሔዎች በቪዲዮ በታገዘ ማብራሪያ ለጎብኚዎች ቀርበዋል። ከዐውደ ርእዩ በተጨማሪም ከማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል የመጡት መምህር ፈቃዱ ሣህሌ ትምሀርት ሰጥተዋል።

ከሁለቱ ቀናት የዐውደ ርእይ ገለጻ በኋላ የውይይት መድረክ የተከፈተ ሲሆን ምእመናኑ በማስረጃ እና በፎቶ የተደገፈ የቤተክርስቲያናቸውን ታሪክ በማየታቸው እጅግ ከመደሰታቸው እና ከመማራቸው በተጨማሪ የገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶችን ተግዳሮቶች ለመፍታት በማኅበረቅዱሳን አስተባባሪነት እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችንም በማየታቸው እነሱም የዚህ ታሪክ አካል ለመሆን የድርሻቸውን ለመወጣት መወሰናቸውን ተናግረዋል። በዚህም መሠረት በአጥቢያቸው ስም በቋሚነት አንድ የአብነት ትምህርት ቤት ወይም የአንድ ገዳም ፕሮጀክት ለመርዳት ቃል የገቡ ሲሆን በእለቱ በነበረው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐግብር ላይም በንቃት ተሳትፈዋል።

20160813_164049 img_20160814_101310

በመርሐግብሩ ማጠቃለያ ላይ ንግግር ያደረጉት በማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ያብባል መሉዓለም መርሐግብሩ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ከፍተኛ ክትትል እና ድጋፍ ላደረጉት ለመልአከ ገነት ቆሞስ አባ ብርሃነ መስቀል ተድላ፣ ምዕመናንን በማስተባባር ለተሳታፊዎች መስተንግዶ በማቅረብ ገቢ እንዲሰበሰብ ላደረገው ለደብሩ ሰበካ ጉባኤ እንዲሁም እንግዶችን በማስተናገድ እና በዝግጅቶች ላይ በንቃት በመሳተፍ ከፍተኛ የቤተክርስቲያን ፍቅር ላሳዩት የአጥቢያው ምእመናን ምሥጋና አቅርበዋል። በመጨረሻም መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ብርሃነ መስቀል ተድላ ዐውደ ርእዩን ያዘጋጀውን የማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል እና ለዝግጅቱ የተራዱትን ምእመናን ሁሉ አመስግነው የገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ጉዳይ የቤተክርስቲያን ልጆች ሁሉ ጉዳይ ሰለሆነ የበርሊን ምእመናንም ዛሬ ያሳየነውን ተነሳሽነት አጠናክረን በገባነው ቃል መሠረት በቋሚነት አንድ ገዳም ወይም የአብነት ትምህርት ቤት ልንረዳ ይገባናል፤ የማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከልም የፕሮጀክት ዝርዝሮችን እና ወቅታዊ መረጃዎችን እና ሪፖርቶችን በማቅረብ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ትልቅ አደራ ተጥሎበታል በማለት መርሐ ግብሩን በጸሎት ዘግተዋል።

img_20160814_134856

በተያያዘ ዜና በማኅበረ ቅዱሳን የጀርመን ንዑስ ማእከል በያዝነው ፳፻፰.. የገዳማት እና አብነት ትምህርት ቤቶች ቀን” የተሰኙ መርሐግብራት በሙኒክ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል (ግንቦት እና ፳፩ ) እና በዳርምሽታት ሐመረኖኅ ኪዳነምህረት (ሰኔ ፲፰ እና ፲፱) አጥቢያዎች ከሰበካ ጉባዔያቱ ጋር በመተባበር አካሂዷል። በነዚህ መርሐግብራት ላይ ስለገዳማት እና የአብነት ትምህርት ቤቶች ታሪክ፣ አስተዋጽኦ፣ ወቅታዊ ችግር፣ እንዲሁም በማኅበረ ቅዱሳን በተለይም በአውሮፓ ማእከል አስተባባሪነት የተሰሩ ያሉ ሥራዎችን የዳሰሱ በቪዲዮ የተደገፉ ገለጻዎች የተሰጡ ሲሆን ገለጻዎቹን ተከትሎም ውይይቶች እና የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐግብራትም ተካሂደዋል።