ግብረ-እስጢፋኖስ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማዕከል ግብረ-እስጢፋኖስ የተሰኘ ልዩ የዲያቆናት መርሐ ግብር በመጋቢት 23 እና 24፣ 2012 ዓ.ም አዘጋጀ፡፡
በማዕከሉ ትምህርት ክፍል አስተባባሪነት የተካሄደው ይህ መርሐ ግብር በአውሮፓ የሚኖሩ ዲያቆናትን በአንድ ላይ በማሰባሰብ ዲያቆናት ከቤተ መቅደስ አገልግሎት ጀምሮ ምዕመናንን በስብከተ ወንጌል በማስተማር ወንጌልን ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት የላቀ ሚና እንዲኖራቸው ለማደረግ ያለመ ነበር፡፡ በመርሐ ግብሩም የኢጣልያንና አካባቢው ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሕርያቆስ ለዲያቆናት ትምህርት፣ ተግሳጽ፣ ቡራኬ፣ እና ቃለ ምዕዳን የሰጡ ሲሆን ካህናት አባቶች መነኮሳት እና በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት የሚገኙ ከ 40 በላይ የሚሆኑ ወንድሞች ዲያቆናት ተሳትፈዋል፡፡ ለሁለት ቀን የተካሄደው ይህ ልዩ የዲያቆናት መርሐ ግብር የሰማዕቱ ቅዱስ እስጢፋኖስን ታሪክ፣ አገልግሎት በመዘከር እና ከሰማዕቱ እኛ ምን እንማራለን? የሚለውን ነጥብ ለተሳታፊዎች በማስገንዘብ ተጀምሯል፡፡ የክህነትን ሥርዓት እና ክብር በተመለከተ ትምህርት፣ ምክር በብጹዕ አቡ ሕርያቆስ የተሰጠ ሲሆን በቀሲስ ሰሙ ምትኩ (ዶ/ር) አማካኝነት ደግሞ ሰፊ የክህነት ምንነት የግንዛቤ ማብራሪያ በማድረግ የመጀመሪያ ቀን መርሐ ግበር ተጠናቋል፡፡
በሁለተኛው ቀን በነበረው ቆይታም የስብከተ ወንጌልን ትርጉም እና አስፈላጊነት፣ ስብከተ ወንጌል እንዴት መቼ እና የት? መካሄድ አለበት የሚለውን በተመለከተ በመልአከ ሳህል ቀሲስ ያብባል ሙሉዓለም (ዶ/ር) አማካኝነት ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ዲያቆናት በስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንዳይሳተፉ የሚያደርጉ ችግሮችን ለመለየት በተሳታፊዎች መካካል ውይይት የተደረገ ሲሆን፦ በቂ የሆነ የመንፈሳዊ ዕውቀት አለመኖር፣ እራስን መደበቅ፣ ያልተገባ ፍርሃት፣ ስብከተ ወንጌልን መሠረት ያደረጉ የስልጠና ማዕከላትም ሆነ የመንፈሳዊ ኮሌጆች አለመኖር፣ እንዲሁም በአብነት ትምህርት ቤቶች ስብከተ ወንጌልን መሠረት ያደረገ የትምህርት እና የስልጠና ሥርዓት አለመኖሩ ከአብነት ትመህርቱ ጎን ለጎን የስብከተ ወንጌል ዲያቆናት ክህሎታቸውን እንዳያዳብሩ ያደረጓቸው ዐበይት ችግሮች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
በመጨረሻም ወንድሞች ዲያቆናት እነዚህን ችግሮች ተቋቁመው በክህነት አገልግሎት ኃለፊነታቸውን እንዲወጡ ታታሪዎች፣ አንባቢዎች እና ሁሌም በጸሎት የሚተጉ መሆን እንደሚገባቸው መልአከ ምሕረት አባ ዘሚካኤል ደሬሳ ምክራቸውን እና ተሞክሯቸውን በማካፈል እንዲህ አይነቱ መርሐ ግብር ወደፊት በሰፊ ሁኔታ መተግበር እንዳለበት በማሳሰብ ስልጠናው በጸሎት ተፈጽሟል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር።
አሜን፡፡
ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል