በዴንማርክ ዐውደ ርእይ ተካሄደ
በዴንማርክ ግኑኝነት ጣቢያ
ሐምሌ 10 ቀን 2007 ዓ.ም.
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሰ/ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማዕከል የዴንማርክ ግንኙነት ጣቢያ ከዴንማርክ የደብረ ምሕረት ቅዱስ አማኑኤል ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጋር በመተባበር በኮፐንሃገን ከተማ ዐውደ ርእይ አካሄደ። ዐውደ ርእዩ በመልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ዘሚካኤል ጸሎት እና የመግቢያ ንግግር እንዲሁም ለአውሮፓ ማዕከል ፲፭ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ከዋናው ማዕከል ተወክለው በመጡት በአቶ ፋንታሁን ዋቄ ለሕዝቡ ክፍት ሆኗል። ዐውደ ርእዩ የተካሄደው ሐምሌ ፫ እና ፬ ፳፻፯ ዓ.ም. ሲሆን በሁለቱ ቀን መርሐ ግብር ከመቶ ሰው በላይ ተገኝቷል።
ዐውደ ርእዩ የዴንማርክ ግንኙነት ጣቢያ የ ፳፻፯ ዓ.ም. እቅድ መነሻ ሆኖት በዴንማርክ የደብረ ምሕረት ቅዱስ አማኑኤል ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ አስተዳደር ትብብር እና በአውሮፓ ማእከል ሥራ አስፈጻሚ ልዩ ድጋፍ የተደረገ ነው።
ዐውደ ርእዩ «ፍኖተ ቤተክርስቲያን» የሚል አጠቃላይ ርዕስ ሲኖረው፣ በውስጡ ”ቤተክርስቲያን በሦስቱ ሕግጋት” ፣ ” ዝክረ ገዳማት ” እና ”ማኅበረ ቅዱሳን ማን ነው?” የሚሉ ክፍሎች ነበሩት።
”ቤተክርስቲያን በሦስቱ ሕግጋት” የሚለውን የመጀመሪያውን የዐውደ ርእይ ክፍል ያቀረቡት ዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ ሲሆኑ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በሕገ ልቡና፣ በሕገ ኦሪት እና በሕገ ወንጌል የነበራትን ታሪካዊ ጉዞ ለታዳሚው አብራርተዋል። እንዲሁም ከዚሁ ክፍል ጋር አባሪ ሆኖ የቀረበውን የዴንማርክ ደብረ ምሕረት ቅዱስ አማኑአል ቤተክርስቲያንን አመሠራረት እና እድገት ዝርዝር የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ሥራ አስፈጻሚ አባል ዶ/ር ዳንኤል ጸጋይ አቅርበዋል።
”ዝክረ ገዳማት” የሚለው ሁለተኛው የዐውደ ርእይ ክፍል በዲ/ን መሐሪ ቀርቧል ። ይህም ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ለኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ያላቸውን መሠረታዊ ጠቀሜታ መነሻ አድርጎ በአሁኑ ሰዓት ያሉባቸውን ችግሮች በማስረዳት ምእመናን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የሚያነሳሳ ነበር። በተጨማሪም እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የሚደረገውን የምእመናን ተሳትፎ ከሌሎች ቦታዎች ተሞክሮ ለማሳያ ቀርቧል።
” ማኅበረ ቅዱሳን ማን ነው? ” የሚለውን ሦስተኛ ክፍል ያቀረቡት አቶ ፋንታሁን ዋቄ ናቸው ። በዚህም የማኅበረ ቅዱሳንን ማንነት፣ ለቤተክርስቲያን እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ ምን እንደሆነ እና ያሉበት ተግዳሮቶች በሚገባ ተብራርተው ቀርበዋል።
በሁለቱም እለታት ዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ “የእነርሱ ትርፍ የእናንተን ጉድለት እንዲሞላ በአሁኑ ጊዜ የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጉድለት ይሙላ” በሚል ርእስ እና የቅዱስ ጳውሎስን ታሪክ መነሻ በማድረግ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል።
ከዐውደ ርእዩ በኋላ ለአንዳንድ ምእመናን ባደረግነው ቃለ መጠይቅ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በሕገ ልቦና፣ በሕገ ኦሪትና በሕገ ወንጌል የሄደችበትን መንገድ በዝርዝር ለመረዳት እንደቻሉ የገለጡ ሲሆን የአብነት ትምህርት ቤቶችን አስተዋጽኦ እና ችግሮቻቸውንም የተረዱ መሆናቸውን እና ወደፊትም የበኩላቸውን ለማድረግ የውዴታ ግዴታ ያለባቸው መሆኑን ተናግረዋል። በተጨማሪም ስለ ማኅበሩ ያላቸው ግንዛቤ እንደጨመረና በሥራውም ያቅማቸውን ለማገዝ ፈቃደኝነታቸውን ገልጸዋል።
ከዴንማርካውያን መካከል የኮፐንሀገን ደብረ ምሕረት ቅዱስ አማኑኤል ቤተክርስቲያን አገልጋይ የሆኑትን ዲ/ን ማርቆስ ሚናን አጠቃላይ ስለ ዐውደ ርእዩ ጠይቀናቸው ሲመልሱ «እኔ ኢትዮጵያ ሳልሄድ ኢትዮጵያ ያለሁ ያህል ተሰምቶኛል፤ ቤተክርስቲያኗን ስለምወድ የእርስዋ የሆነውን እወዳለሁ። ነገር ግን በሁለቱም ቀን በአስተርጓሚ ነው የሰማሁት። እንዲህ ከሚሆን ለእኔም ሆነ እንደ እኔ የቋንቋ ችግር ላለባቸው ሁሉ አንብበን እንድንረዳ ዐውደ ርእዩ በዴኒሽ ወይም በእንግሊዘኛ ጽሑፍ ቢኖርው ጥሩ ይመስለኛል።» በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በመጨረሻም ለዚህ ላበቃን ለእግዚአብሔር አምላካችን ምስጋና እያቀረብን ለዐውደ ርእዩ መሳካት አስተዋጽኦ ያደረጉትን፣ በዋናነት የዋና ማእከሉንና የአውሮፓ ማእከል አባላትን፣ የደብሩን የሰባካ ጉባኤ ሥራ አስፈጻሚ አባላትን እና ሌሎች በሥራ የተባበሩ ምእመናንን ሁሉ እድሜ እና ጤና ይስጥልን እንላለን። እኛንም ለበለጠ አገልግሎት ያተጋን ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃዱ ይሁንልን፤ አሜን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር ፤ አሜን።