በጀርመን ሙኒክ ዐውደ ርእይ ተካሔደ
በጀርመን ቀጣና ማእክል
ግንቦት 20 ቀን 2007 ዓ.ም.
በማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል ግንቦት ፲፭ እና ፲፮ ፳፻፯ ዓ.ም. በጀርመን ሙኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ”ለሁለንተናዊ የቤተክርስቲያን እድገት የድርሻችንን እንወጣ” በሚል ርዕስ የዐውደ ርእይ እና የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር አካሄደ::
በሙኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ሊቀብርሃናት ቆሞስ አባ ገብረሕይወት ፍስሐ የተከፈተው ዐውደ ርእይ በሦስት ትዕይንቶች የተከፋፈለ ነበር:: የቤተክርስቲያንን ታሪካዊ ጉዞ የሚያስቃኘው የመጀመሪያው ትዕይንት ከሕገ ልቡና የተጀመረው የኢትዮጵያውያን እግዚአብሔርን የማምለክ ጉዞ እና ሐዋርያዊ አገልግሎት በርካታ ወርቃማ እና የፈተና ዘመናትን እያሳለፈ ለዛሬ መድረሱን የሚያስረዳ ሲሆን የቤተክርስቲያን አገልግሎት በአውሮፓ በተለይም በጀርመን ያለበትን ሁኔታ እና የአመሠራረት ታሪክም ያካተተ ነበር:: በሁለተኛው ትዕይንት ደግሞ የኢትዮጵያ ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ታሪክ ፣ አስተዋጽኦ እና ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት በማኅበረ ቅዱሳን አስተባባሪነት እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች የተዳሰሱብት ነው:: ሦስተኛው ትዕይንት ስለማኅበረ ቅዱሳን እና አገልግሎቱ ነበር:: ከዐውደ ርእዩ በተጨማሪ ከማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል በመጡት በመምህር ዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ ትምህርት ተሰጥቷል::
ዐውደ ርእዩን የተመለከቱት የሙኒክ እና አካባቢው ምእመናን በሰጡት አስተያየት ስለ ቤተክርስቲያን ታሪክ ብዙ ጠቃሚ መረጃዎችን ማግኘታቸውን፣ ስለ ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ችግርም በሚገባ መገንዘባቸውን እና ችግሮቻቸውን ለመቅረፍ በማኅበረ ቅዱሳን በኩል የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለመደገፍ ዝግጁነታችውን ተናግረዋል። ሊቀብርሃናት ቆሞስ አባ ገብረሕይወት ፍስሐ በበኩላቸው የአብነት ተማሪዎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እርሳቸውም በውስጡ በማለፍ የቀመሷቸው መሆናቸውን እና የአብነት መምህራን ወደ ከተማ ፍልሰትም በአገልግሎት በቆዩባቸው ጊዜያት የተመለከቱት አሳዛኝ እውነታ መሆኑን በማስረዳት በማኅበረ ቅዱሳን እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ እየተሰሩ ያሉ ጅምሮችን ምእመናን ሊደግፉ እንደሚገባ አሳስበዋል ::
ዐውደ ርእዩ እሑድ ከሰዓት ከመጠናቀቁ በፊት ንግግር ያደረጉት በማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማዕከል ሰብሳቢ ዲያቆን ሰሎሞን አስረስ ለዝግጅቱ መሳካት ከጅማሬ እስከ ፍፃሜ ከፍተኛ ትብብር ያደረጉትን የደብሩን አስተዳዳሪ፣ ዐውደ ርእዩ እንዲካሄድ በሙሉ ፈቃደኝነት የሚያስፈልገውን ሁሉ ያደረጉትን የሰበካ ጉባዔ አባላትን እንዲሁም ዐውደ ርእዩን በመጎብኘት እና በገንዘባቸው ድጋፍ በማድረግ የተባበሩትን ምእመናን በሙሉ አመስግነው ይህ ቀና ትብብር ለወደፊትም እንደማይለያቸው ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል::በመጨረሻም ሊቀብርሃናት ቆሞስ አባ ገብረሕይወት ማእከሉ ዐውደ ርእዩ በደብሩ ስላካሔደ በሰበካ ጉባኤው ሥም ምሥጋና አቅርበው የአጥቢያው ምእመናንን በማስተባበር ገዳማቱን በቋሚነት የሚደግፉ መሆኑን በመግለጽ መርሐ ግብሩን በጸሎት ዘግተዋል::
ተመሳሳይ የዐውደ ርእይ ዝግጅቶችና ለገዳማትና አብነት ት/ቤቶች ማጠናከሪያና ማቋቋሚያ ድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሮች በጀርመን ሃምቡርግ ኪዳነምሕረት እንዲሁም በስዊዘርላንድ፣ ግሪክ፣ ስዊድን፣ ዴንማርክ፣ ጣሊያን፣ ፊንላንድ፣ ቤልጄም እና እንግሊዝ እንደሚካሔዱ ከማእከሉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡