የጥምቀት በዓል በለንደን እና በሊቨርፑል ከተሞች በአንድነት ይከበራል
በዩኬ ቀጠና ማዕከል
ጥር 5 ቀን 2007 ዓ.ም.
የ፪፻፯ ዓ.ም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል በታላቋ ብሪታኒያ በለንደን እና በሊቨርፑል ከተሞች በህብረት ይከበራል። በዓሉ በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት አዘጋጅነት ጥር ፲ እና ፲፩ ቀን ፪፻፯ ዓ.ም በለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ጥር ፲፭ እና ፲፮ ቀን ፪፻፯ ዓ.ም በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት የለንደን ውጭ ወረዳ ቤተ ክህነት አዘጋጅነት በታላቁ የሊቨርፑል ካቴድራል በደማቅ ሥነ ሥርዓት ይከበራል።
በለንደን የሚከበረው በዓል ላይ አራቱ በለንደን ከተማ ውስጥ የሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት ማለትም ርዕሰ አድባራት ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም፣ ጽርሐ ጽዮን ቅድስት ማርያም፣ ደብረ ገነት ቅድስት ሥላሴ እና ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ይሳተፋሉ። በሊቨርፑል ከተማ በሚዘጋጀው በዓለ ጥምቀት ላይ በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት የለንደን ውጭ ወረዳ ቤተ ክህነት ውስጥ ካሉት አብያተ ክርስቲያናት አሥሩ ማለትም የበርሚንግሃም ደብረ መድኃኒት ቅዱስ አማኑኤል፣ የማንችስተር ደብረ ሰላም ቅድስት ሥላሴ፣ የኒውካስል ደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል፣ የስቶክ ኦን ትሬንት ቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል፣ የሀደርስ ፊልድ ደብረ ጸሐይ ቅድሰት ኪዳነ ምህረት፣ የሸፊልድ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል፣ የሊድስ ደብረ ስብሐት መድኃኔ ዓለም፣ የብሪስተል ስደተኛው መድኃኔዓለም፣ የሊቨርፑል መካነ ቅዱሳን አቡነ ተክለ ሃይማኖት እና የካርዲፍ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አብያተ ክርስቲያናት ይሳተፋሉ። በዚሁ በዓል ላይ ከአብያተ ክርስቲያናቱ ጋር በወረዳ ቤተ ክህነቱ ሥር የሚገኙ የኮቨንተሪ ሰማዕቱ ቅዱስ ቂርቂስ፣ የደርቢ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ የኖቲነግሃም ልደታ ለማርያም፣ የሌስተር አቡነ አረጋዊ፣ የግሎስተር ሰማዕቱ ቅዱስ እስጢፋኖስ ማህበር፣ የሚድልስቦሮው ቅዱስ ጊዮርጊስ መንፈሳዊ ማህበራት ተሳታፊ ናቸው።
በተለይ በሊቨርፑል የሚከበረው በዓል ለመጀመሪያ ጊዜ በመሆኑ ከይዘቱና ከበዓሉ ስፋት አንጻር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ዝግጅቱ ቀደም ብሎ ሲከናወን የሰነበተ በመሆኑ በዓሉን የተለየ ያደርገዋል። ይህ በዓል በሀገሪቷ ውስጥ አሉ ከሚባሉት ታላለቅ አብያተ ክርስቲያናት አንዱ በሆነው የሊቨርፑል ካቴድራል ከመካሔዱ ጋር በበዓሉ ላይ ከኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች፣ የመንግስት ባለሥልጣናት እንዲሁም በሊቨርፑል እና በሌሎች የዩኬ ከተሞች የሚገኙ ብዛት ያላቸው እንግሊዛውያን ነዋሪዎች ይገኙበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በዓሉ ከዋዜማው ጀምሮ ታቦታቱ በቦታው አርፈው የዋዜማና ከተራ የሥርዓተ ማኅሌት፣ የስብከት እና የመዝሙር መርሐ ግብራት የሚከናወኑ ሲሆን በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ታሪኳን፣ መንፈሳዊ ሀብቷን እና እንዲሁም በሀገር ደረጃ ያበረከተቻቸውን አስተዋጽኦ የሚያስቃኝ በአማርኛና በእንግሊዝኛ በአውሮፓ ማእከል የዩኬ ቀጠና ማእከል የተዘጋጀ ዐውደ ርእይ በብፁዕ አቡነ እንጦንስ የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሊቀ ጳጳስ ተባርኮ ለምዕመናን በይፋ ይከፈታል። በዓሉ ጥር ፲፮ ቀን የቅዳሴ እና የጥምቀት መርሐ ግብራት ከተከናወኑ በኋላ ታቦታቱ ወደ መንበረ ክብራቸው በታላቅ ሥነ ሥርዓት ተሸኝተው የበዓሉ ፍጻሜ ይሆናል።