በኦስሎ ከተማ የአውደ ርዕይና የአውደ ጥናት መርሐ ግብር ተካሄደ
በኖርዌይ ግንኙነት ጣቢያ
ሰኔ 25 ቀን 2006 ዓ.ም.
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማእከል የኖርዌይ ግንኙነት ጣቢያ «ለሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን እድገት የድርሻችንን እንወጣ» በሚል መሪ ቃል የአውደ ርዕይና የአውደ ጥናት መርሐ ግብር ከሰኔ 6-8 ቀን 2006 ዓ.ም በኦስሎ ከተማ በደማቅ ሁኔታ አካሄደ።
በዚህ ብዙ ምእመናን በተሳተፉበት መርሐ ግብር በዋናነት ሦስት/3/ ትዕይንቶች፣ አውደ ጥናትና ስብከተ ወንጌል ተካተዋል። መርሐ ግብሩ ዓርብ ሰኔ 6 ከሰዓት በኋላ በጸሎት ተከፍቶ ትምህርተ ወንጌል የተሰጠ ሲሆን፤ ቅዳሜ ሰኔ 7 ጠዋት የአውደ ርዕይ መርሐ ግብሩ ተጀምሯል። ከሰዓት በኋላ በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል የቀረበ አውደ ጥናት «የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በአድዋ ድል ላይ ያላት ድርሻ» በሚል ርዕስ በዶ/ር ተክሉ አባተ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጓበታል። አውደ ጥናቱን ተከትሎ ትምህርተ ወንጌል ከተሰጠ በኋላ የአውደ ርዕዩ ገለጻ እስከ ማታ ድረስ ቀጥሏል። እንዲሁም እሑድ ከቅዳሴ በኋላ ገለጻው ቀጥሎ ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት ላይ ተጠናቋል።
በሦስቱ ትዕይንቶች ማለትም ሐዋርያዊ ተልዕኮና ስብከተ ወንጌል(ትዕይንት አንድ)፣ የኢትዮጵያ ጥንታውያን ገዳማት ትናንትና ዛሬ(ትዕይንት ሁለት) እና ማኅበረ ቅዱሳን(ትዕይንት ሦስት) ዙርያ በስፋትና በዝርዝር ገለጻ ተደርጓል።
በትዕይንት አንድ ገለጻ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልዕኮዋን ለመወጣት ያደረገችው ውጣ ውረድና በገጠሟት ተግዳሮቶች ምክንያት እየቀነሰ የመጣውን የምእመናን ቁጥር በማሳየት ማኅበረ ቅዱሳን ለዚህ ችግር ጊዜያዊ መፍትሄ ይሆናል ብሎ እያከናወነ ስላለው በተመረጡ ገጠራማና አጽራረ ቤተ ክርስቲያን በበዙበት አካባቢ የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮግራምን በተመለከተ ሰፊ ገለጻ በመደረጉ ለተሳታፊዎች በቂ ግንዛቤ ፈጥሯል።
በትዕይንት ሁለትም – የኢትዮጵያ ጥንታውያን ገዳማትና የአብነት ት/ቤቶች ትናንትና ዛሬ – የገዳማትና የአብነት ት/ቤቶች አስፈላጊነትና ለአገራችን ያደረጉት ከፍተኛ አስትዋጽኦና ድርሻ እንዲሁም ዛሬ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ በበቂ ሁኔታ ገለጻ ስለተደረገ የተሳተፊ ምእመናንን ስሜት ቀስቅሷል። ብዙዎች ከእንባ እና ከስሜትም አልፈው ለገዳማትና አብነት ት/ቤቶች ድጋፍ ለማድረግ በተለይ በማኅበሩ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማገዝ እና በተለያዩ ፕሮጀክቶች ላልታቀፉ ገዳማትና አብነት ት/ቤቶችም ልዩ ትኩረት ለመስጠት ቃል ገብተዋል።
በመጨረሻው ትዕይንት ስለማኅበረ ቅዱሳን አመሰራረት፣ ዓላማና ራዕይ፣ አደረጃጀትና ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እንዲሁም ተግዳሮቶችን በማንሳት ሰፊ ገለጻ ተደርጓል። በገለጻው ላይም ስለማኅበሩ የተሳሳተ አመለካከት ያላቸው ምእመናን እንዳሉ ከታዳሚዎች በጥያቄና በአስተያየት ቀርቧል። በተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ በአውሮፓ ማዕከል ሰብሳቢ ዲ/ን ሰሎሞን አስረስ ሰፊ ገለጻ በመደረጉ ለቤተክርስቲያን ብቻ የተቋቋመ ማኅበር መሆኑን ተሳታፊዎች መገንዘባቸውን በቃልና በጽሑፍ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!