በሀገረ ጀርመን የካስል ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት ተከበረ

ኅዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም

በጀርመን ንዑስ ማዕከል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት የካስል ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ጥቅምት 24 እና 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በሀገረ ስብከቱ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ ቡራኬ ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ። ይህ የሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በካህናት እና ምዕመናን ብርቱ ጥረት የተገዛ መሆኑ ታውቋል። በበዓሉም ላይ ተጋባዥ እንግዶች፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ካህናትና ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንዲሁም በርካታ ምዕመናን ተገኝተዋል።

የመጀመሪያው ዕለት መርሐ ግብር ቅዳሜ ጥቅምት 24 ቀን ከቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ በበዓሉ ዋዜማ ስብሐተ እግዚአብሔር ከደረሰ በኋላ በብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ተባርኳል። በመቀጠልም ቅዳሜ ሌሊት የጽጌ ሥርዓተ ማኅሌት ደርሶ እሑድ ጥቅምት 25 ቀን ሥርዓተ ቅዳሴ ተከናውኖ ዑደተ ታቦቱ በድምቀት ተከብሯል።

በዕለቱ የሕንፃ አሠሪው ኮሚቴ ካዘጋጀው ሥዕላዊ ገለጻ ለመረዳት እንደተቻለው የካስል ደ/ቀ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ታቦተ ሕግ ተረቦክ አገልግሎት መሥጠት ከጀመረ ዐሥራ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል። ላለፉት ስድስት ዓመታት በቦታ ችግር ምክንያት አገልግሎቱን በተለያዩ ቦታዎች ላይ በወር አንድ ጊዜ ብቻ ለመስጠት ተገዶ ቆይቷል። ይህንኑ ችግር ለዘለቄታው በማስወገድ ደብሩ ቋሚ የአገልግሎት መስጫ ቦታ እንዲኖረው ለማድረግ የሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ግዢ ኮሚቴ አቋቁሞ ላለፉት ዐራት ዓመታት ገንዘብ የማሰባሰብና ቦታ የማፈላለግ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል። በመድኃኔዓለም ቅዱስ ፈቃድ የጀርመን ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን  ንብረት የነበረ አንድ ሕንፃ ቤተክርስቲያን በነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም. ከሁለት መቶ ሃያ ሺ ዩሮ በላይ በማውጣት በደብሩ ስም ተገዝቷል። ሕንፃው የኢ.ኦ.ተ. ቤተ ክርስቲያንን ቅርጽና መልክ እንዲይዝ በደብሩ ምዕመናን ከፍተኛ ርብርብ መጠነኛ እድሳትና የውስጥ ግንባታ ማሻሻያ እንደተደረገለትም የሕንጻ ግዢ ኮሚቴው በዘገባው ገልጿል።

የደብሩ አስተዳዳሪ መጋቤ ምሥጢር ኅሩይ ኤርምያስ ለሕንፃ ቤተክርስቲያኑ ግዢ መሳካት እስከ አሁን ድረስ በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በሙያና በዓይነት የረዱትን አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት፣  የጽዋ ማኅበራት፣ የደብሩን ሰበካ ጉባኤ እና የሕንፃ ሥራ ማኅበር አባላት እንዲሁም ምዕመናንን አመስግነዋል። በቀጣይም በብድር የተከፈለውን ገንዘብ ከፍሎ ደብሩን ከማንኛውም ዕዳ ነፃ ለማድረግ ምዕመናን ድጋፋቸው እንዲቀጥል ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስም በበኩላቸው የሕንፃ ቤተክርስቲያኑ ግዢ የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን በጀርመን ሀገር ለ3ኛ ጊዜ ባለይዞታ ያደረገ አኩሪና ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ደስታ የሆነ ሥራ መሆኑን በመግለጽ ከደብሩ አስተዳዳሪ ጀምሮ ለሕንፃ ቤተክርስቲያኑ መገዛት በተለያየ መንገድ እገዛና ትብብር ያደረጉትን በሙሉ በሀገረ ስብከቱና በራሳቸው ስም አመስግነዋል።  በተጨማሪም ለብዙ ዓመታት በደብሩ መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ አገልጋዮች ከደብሩ ሰበካ ጉባዔ የተዘጋጀውን ስጦታ ከብፁዕነታቸው እጅ ተቀብለዋል።

በደብሩ ጋባዥነት በበዓሉ ላይ የተገኙት በጀርመን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. አምባሳደር አቶ ኩማ ደመቅሳ እና በፍራንክፈርት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ቆንስላ ጀኔራል አቶ ምሕረተአብ ሙሉጌታም ምዕመናን በመተባበር የሠሩት ይህ ሥራ ሀገር የሚያኮራ፣ የአንድነትና የመተባበርን ጠቀሜታ አጉልቶ የሚያሳይ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል። ቤተ ክርስቲያኒቱ የበርካታ ዕሴቶች ባለቤት ለሀገርም ከፍተኛ ውለታ የዋለች እንደመሆኗ መጠን የልማት እንቅስቃሴው በዚህ ሳይገታ በሁሉም ዘርፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በመጨረሻም በበዓሉ ላይ የተገኙ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ካህናት እና ምዕመን በቤተ ክርስቲያኑ መገዛት የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ ገልጸው፤ በብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ ጸሎትና ቡራኬ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።

በተያየዘም ከዚህ ቀደም የበርሊን ደብረ ገነት ቅዱስ አማኑኤል አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የራሱ የሆነ ሕንጻ ገዝቶ በአገልሎት ላይ መሆኑ ይታወሳል። የኮሎኝ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንም የራሱ የሆነ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን አለው።እንዲሁም የፍራንክፈርት ምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም አጥቢያ ቤተክርስቲያን ደግሞ የራሱ የሆነ ሕንጻ ገዝቶ ሕንጻው የኢ.ኦ.ተ.ቤተ ክርስቲያን ትውፊትን እንዲይዝ ለማድረግ ውስጣዊ እድሳትን በማድረግ ላይ ሲሆን በቅርቡ ተባርኮ ለአገልግሎት ዝግጁ እንደሚሆን ያገኘው መረጃ ያሳያል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!