ማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቪዠን መርሐ ግብር ሊጀምር ነው
በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ
መስከረም 12 ቀን 2005 ዓ.ም.
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ማኅበረ ቅዱሳን ከጥቅምት 4 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ዘወትር በየሳምንቱ እሑድ ጧት ከ3፡30 እስከ 4፡00 ሰዓት የሚቆይ መርሐ ግብር በኢትዮጵያ ብሮድ ካስቲንግ ሰርቪስ ቴሌቪዠን (EBS TV) ለመጀመር ሙሉ ዝግጅት ማጠናቀቁ ተገለጠ፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን ኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ፥ የሬድዮና ቴሌቪዠን ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት ዲያቆን ሄኖክ ኀይሌ ለመካነ ድራችን በሰጡት መግለጫ፡- ማኅበሩ ከተመሠረተበት ጊዜ አንሥቶ ላለፉት ሃያ ዓመታት በልዩ ልዩ የኅትመት ውጤቶች እንዲሁም በመካነ ድር (website) እና በሬድዮ አማካኝነት በሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ትምህርት ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው፤ አሁን ደግሞ በልዑል እግዚአብሔር ፈቃድ በሳምንት አንድ ጊዜ የ30 ደቂቃ መርሐ ግብር ለመጀመር ትናንት መስከረም 11 ቀን 2005 ዓ.ም ከኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን የሥራ ሓላፊዎች ጋር ለአንድ ዓመት የሚቆይ ስምምነት ማኅበሩ መፈራረሙን ገልጸዋል፡፡
ዲያቆን ሄኖክ በዚሁ ገለጻቸው፥ በአውሮፓና አሜሪካ እንዲሁም በሀገር ውስጥ በ17515 ኪሎ ኸርዝ፣ በ16 ሜትር ባንድ አጭር ሞገድ ዘወትር አርብ ከምሽቱ 3፡30 እስከ 4፡30 ድረስ የሚተላለፈውን የሬድዮ ዝግጅት በመከታተልና ገንቢ አሰተያየት በመስጠት ምእመናን ላደረጉት ተሳትፎ በማመስገን በአዲሱ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር ላይም ተመሳሳይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
ማኅበሩ ከጥቅምት 2003 ዓ.ም አንሥቶ በአጭር ሞገድ የሬድዮ መርሐ ግብር መጀመሩ ይታወሳል፡፡