በፓርማ አውደ ርእይ ተካሄደ
በጣሊያን ንዑስ ማእከል
ሐምሌ 26 ቀን 2007 ዓ.ም.
የፓርማ ቤዛ ብዙኃን ቅድስት ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ከማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል ጋር በመተባበር ያዘጋጀው አውደ ርእይ በጣሊያን ፓርማ ከተማ ተካሄደ።
አውደ ርዕዩ በፓርማ ቤዛ ብዙኃን ቅድስት ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ኃይል ቆሞስ አባ ወልደ ሰንበት ተ/ማርያም የተከፈተ ሲሆን ከሐምሌ 11 – 12 ቀን 2007 ዓም ለምእመናን ክፍት ሆኖ ቆይቷል። በአውደ ርእዩ ቤተክርስቲያን ያደረገቺው የ2000 ዓመታት ሐዋርያዊ ጉዞ፣ የገዳማትና አብነት ት/ቤቶች ሚናና አሁንያሉበት ሁኔታ፣ ማኅበረ ቅዱሳን እያደረገ ያለው እንቅስቃሴና ለቤተክርስቲያን ሁለንተናዊ እድገት የምእመናን ድርሻ ምን ሊመስል እንደሚገባው በግልጽ ተተንትነው ቀርበዋል፡፡
በተጨማሪም በዝግጅቱ ሰፊ የስብከተ ወንጌል መርሐግብር ተካትቶ በሁለቱም ቀናት ለምእመናን ሰፋ ያለ ትምህርት በዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ ተሰጥቷል።
አውደርእዩን ከፓርማና አካባቢው የጣሊያን ከተሞች የመጡ ከመቶ በላይ ምእመናንና ምእመናት ተመልክተውታል።በተጨማሪም ወደ 10 የሚጠጉ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች አውደ ርዕዩን በእንግሊዝኛና በጣሊያንኛ ቋንቋ እየተገለጸላቸው ታድመዋል።
ከመንፈሳዊ ድርሻቸው ባለፈ ለሃገራችን የላቀ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሚና ያበረከቱ የቤተክርስቲያናችን ገዳማትና አብነት ት/ቤቶች አሁን ያሉበት ሁኔታ እንዳሳዘናቸው ለመረዳት ትእይንቶቹ በሚቀርቡበት ጊዜ እንባ የሚተናነቃቸውን ምእመናን መመልከት በቂ ነበር።
በዝግጅቱ ማጠቃለያ አስተያየታቸውን የሰጡ ታዳሚዎች ቤተክርስቲያን ያለችበትን ሁኔታ በስፋት የሚያሳይ ዝግጅት በዚህ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ በመዘጋጀቱ መደሰታቸውንና ጥሩ ግንዛቤ እንደጨበጡበት ተናግረዋል።ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው አንድ የውጭ ዜጋም በዝግጅቱ መደሰታቸውንና ስለቤተክርስቲያናቸው የበለጠ ለማወቅ ባላቸው ፍላጎት እንደመጡ፣ ማኅበረ ቅዱሳን የሚሠራቸውን ሥራዎችና የአንዳንድ ገዳማትን ነባራዊ ሁኔታ በአካል በመሄድ እንደተመለከቱ ገልጸው ከአውደ ርዕዩ ስለ ፍኖተ ቤተክርስቲያን የሚያውቁትን እንዳጠናከሩ፣ ካሁን በፊት ያላወቋቸውን አዳዲስ ነገሮች እንዳገኙ ገልጸዋል። ለወደፊት የአዋልድና ሌሎች ስለቤተክርስቲያኒቱ ጠለቅ ያለ ትንታኔ ያላቸው መጻሕፍት በልዩ ልዩ የአውሮፓ ቋንቋዎች ተርጉሞ ተደራሽ ለማድረግ ቢሞከር የሚል አስተያየትም ሰጥተዋል።
በዝግጅቱ ማብቂያ ለገዳማቱና አብነት ት/ቤቶቹ ማጠናከርያ አጭር የጨረታ ዝግጅት ተካሂዶ ምእመናኑ የአቅማቸውን የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል። መልአከ ኃይል አባ ወልደሰንበት ዝግጅቱን በጸሎት ከመዝጋታቸው በፊት በሰጡት አባታዊ ምክርና ማጠቃለያ ሰበካ ጉባኤው እንዲህ ያለውን የስብከተ ወንጌልና አውደ ርእይ ዝግጅት ረጅም ጊዜ አቅዶና ደክሞበት እንደተዘጋጀ ጠቁመው ይህንንም ለማሳካት የአጥቢያው ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በከፍተኛ ትጋት ማገልገላቸውን ገልጸው ምስጋና አቅርበዋል። ምእመናንም እንዲህ ያለውን ስለቤተክርስቲያናቸው በጥልቀት የሚያሳይ ዝግጅት እንደ ቀላል ነገር እንዳይመለከቱት፣ ያዩትንና የሰሙትን ከትበው እንዲይዙ መክረዋል። የማኅበረ ቅዱሳንን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከምስረታው ጀምሮ እንደሚያውቁ ገልጸው በቅንነት እነርሱን መስለን ቤተክርስቲያንን ካሉባት ወቅታዊ ተግዳሮቶች እንታደግ የሚል ጥሪ አቅርበዋል። ወደፊትም ተጨማሪና ሰፋ ያሉ ጉባኤያትን ማድረግ የሰበካ ጉባኤው ማቀዱን ገልጸዋል።