የ6ኛው ፓትርያርክ ሥርዓተ ሢመት ተፈጸመ
የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 6ኛ ፓትርያርክ ሆነው የተመረጡት የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሥርዓተ ሢመት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም. ተፈጸመ፡፡
ከዋዜማው ጀምሮ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የማኅሌት ጸሎት በማድረስ የተጀመረው ሥርዓተ ጸሎት ከሌሊቱ 10፡00 ሰዓት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከአቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፤ እንዲሁም ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን በመንበረ ጸባዖት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል በመገኘት ሥርዓተ ጸሎቱ ቀጥሏል፡፡
ከኪዳን ጸሎት በኋላ ሥርዓተ ቅዳሴው ቀጥሎ ፤ ከሥርዓተ ቅዳሴው ጋር በማያያዝ የቅዱስ ፓትርያርኩ ሥርዓተ ሢመት በአቃቤ መንበሩ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል እየተመራ በማከናወን ቅዱስ ፓትርያርኩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማገልገል ቃለ መሐላ ፈጽመዋል፡፡ ከሥርዓተ ሢመቱ በኋላ ከአኀት ቤተ ክርስቲያናት መካከል የሕንድ፤ የግብጽ እንዲሁም የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት በየተራ ጸሎት አድርሰዋል፡፡
ሥርዓተ ቅዳሴው እንደተጠናቀቀ በአውደ ምሕረት ላይ የተለያዩ መንፈሳዊ መርሐ ግብሮች ተከናውነዋል፡፡ የአኀት ቤተ ክርስቲያናት እንዲሁም ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፤ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 6ኛው ፓትርያርክ ሆነው በመሾማቸው መልካም ምኞታቸውን በመግለጽ ለቤተ ክርስቲያኒቱና ለአገር እድገት በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡