በጀርመን የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ተመሰረተ።

በጀርመን ን/ማእከል 

ጥር  13 ቀን 2010 ዓ.ም.

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በም/ም/ደ/አውሮፓ ሀገረ ስብከት የሰ/ት/ቤ/ማ/መምሪያ አስተባባሪነት በጀርመን የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ተመሰረተ።

በሀገረ ስብከቱ የሰ/ት/ቤ/ማ/መምሪያ ኃላፊ መልአከ ኃይል አባ ዘድንግል አስተባባሪነት ከሰ/ት/ቤቶች አመራሮች ጋር በተካሄደው የመነሻ ስብሰባ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ለመመስረት የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎችን የሚያከናውን አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴ የተመረጠ ሲሆን የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት መተዳደሪያ ደንቡን ከዚህ በፊት በሰሜን አሜሪካ የተሠራውን መሠረት በማድረግና ህገ ቤተክርስቲያንን በጠበቀ መልኩ አርቅቆ የማቅረብና የማጸደቅ፥ የሰንበት ትምህርት ቤቶችን ተወካዮች ሰብስቦ የማወያየት እና የሰንበት ትምህርት ቤቶችን አባላትን ስለ አንድነቱ ዓላማ እንዲረዱ የማድረግ ተግባራትን በኃላፊነት እንዲመራ ለኮሚቴውም ተስጥቶት ነበር።

ኮሚቴውም የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባዔ በጀርመን ሀገር ለመመሥረት የሚያስችል ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብ አዘጋጅቶ በመቅረብ የመጀመሪያው ስብሰባ ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በፍራንክፈርት አካባቢ በሮሰልስሃይም በሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት አዳራሽ ተካሂዷል። በዚህ ስብሰባ ላይ የሀገረ ስብከቱ የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ፣ የኮሚቴው አባላት፣ የሰንበት ት/ቤቶች አመራሮች እና በሰ/ት/ማ/ም ማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል ተወካይ ተገኝተዋል።

ስብሰባውን በፀሎት ያስጀመሩት መልአከ ኃይል አባ ዘድንግል “ናሁ ሠናይ ወናሁ አዳም፤ ሶበ ይሄልዉ አኀው ኅቡረ። ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው” በመዝሙረ ዳዊት 132 ፥ 1 በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ላይ መሠረት በማድረግ አስተምረዋል። ባስተላለፉት መልክትም ብዙ ተደክሞበት የነበረው የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ምስረታ እግዚአብሔር ፈቅዶ እውን መሆኑን እና ቤተክርስቲያንን ለመጠበቅ ብሎም የቤተክርስቲያን ጠላቶች ለመቋቋም በአንድነት መሆን እንደሚያስፈልግ ቅዱሳን ሐዋርያት በአንድነት ተሰባስበው ይፀልዩ፥ ይማማሩና ይመገቡ እንደነበር በማንሳት አሳስበዋል።

በመቀጠልም በተዘጋጀው ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ የተለያዩ አስተያየቶችና እርማቶች ተሰጥተዋል። በቦታው የተገኙ የሰንበት ት/ቤቶች ተወካዮች እርማት የተሰጠበት መተዳደሪያ ደንብ አፅድቀዋል። በማስከተልም የአንድነት ጉባኤውን ለ3 ዓመታት የሚያገለግሉ 12 የሥራ አመራር ጉባኤ አባላትና ሁለት ኦዲተሮች ከየሰንበት ትምህርት ቤቱ ተመርጠዋል።

በመጨረሻም በስብሰባው ላይ የተገኙት በሰ/ት/ማ/ም ማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል ማእከል ተወካይ ማኅበሩ የመዋቅርን ዝግጅት ፣ ሥልጠና መስጠት ፣ ጥናት ማካሄድ ፣ መካነ ድር ማዘጋጀት እና በመሳሰሉት ሥራዎች ላይ እገዛ እንደሚያደርግ ተናገረዋል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!