በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤ/ማ/መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን

አውሮፓ ማእከል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኮሮና ቫይረስ (COVID 19) ሳቢያ በአውሮፓ የምትገኘውን ቤተ ክርስቲያን (ምእመናን) ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶች እና መፍትሔዎችን በተመለከተ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በሰ/ት/ማ/መ ማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማዕከል  በአውሮፓ ለሚገኙት ለ፬ቱ አህጉረ ስብከት ካቀረበው ምክረ ሐሳብ የተወሰደ፡፡

ጽሑፉን በፒዲኤፍ (PDF) ለማግኘት ይህን ይጫኑ።


ይዘት

1.   መንፈሳዊ ሕይወትን በተመለከተ

1.1 – ክርስቲያናዊ ሕይወታችንን እንዴት እንከባከብ?

2.  ለካህናት (ለማስታወስ ያህል)

3.  ልጆችን በተመለከተ.

4.  ወረርሽኙን ተከትለው የሚመጡ አካላዊና ስነ ልቡናዊ ጉዳቶች እና መፍትሔዎቻቸው፡፡

4.1 – መንፈሳዊ መፍትሔዎች

4.2 – ሌሎች መፍትሔዎች

5.   የኮሮና ወረርሽኝ በአውሮፓ በሚገኙ አጥቢያዎች እና በምእመናን ላይ የደቀነው ኢኮኖሚያዊ ፈተና

5.1 –  በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ በአውሮፓ የሚገኙ አጥቢያዎች የሚገጥማቸው የገቢ ማሽቆልቆል

5.2 – የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን የአጥቢያው ምእመናን ወቅታዊ ችግር በተመለከተ

5.3 –  የአብነት ትምህርት ቤቶችን እና ገዳማትን መከላከል ድጋፍ በተመለከተ

6.  የቀጥታ ስርጭት እና ስብሰባዎችን ለማካሄድ የሚረዱ ቴክኖሎጂዎች ጥቆማ

6.1 –  በሁለት ወገን መነጋገር የሚያስችሉ

6.2 – ከአንድ ወገን ብቻ ለሚተላለፉ ቀጥታ ስርጭቶች

7. ማጠቃለያ ፦

መግቢያ

በዚህ ወቅት በዓለም ላይ የተከሰተው ወረርሽኝ (COVID 19) በአንድም በሌላም መንገድ በምእመናን እና በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደሩ አሌ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ “ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል።” ተብሎ እንደተጻፈው (1ቆሮ. 10፡13) ይህንን ከፊታችን የተደቀነውን ፈተና ማለፍ ይቻለን ዘንድ ወጥነት ባለው መልኩ እንዲህ ብናድርግ መልካም ይሆናል የሚል ሐሳባችንን እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን ሐሳባችንን እንደሚከተለው እንጠቁማለን፡፡

ስለዚህም በዚህ ሰነድ ውስጥ የተገለጹትን ጥቆማዎች እንደ መነሻ ሐሳብ በመጠቀም የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን አገልግሎት ባለንበት ይበልጥ ብናጠናክር መልካም እንደሚሆን ጽኑዕ እምነት አለን፡፡

1.          መንፈሳዊ ሕይወትን በተመለከተ

ከደዌያት ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ዓለም በተለያዩ አዝማናት በርካታ አሳዛኝ ታሪኮችን አስመዝግባለች፡፡ ይህንንም ከቅዱሳት መጻሕፍት ጀምሮ በዓለም ታሪክ መዛግብት ውስጥ ሰፍሮ እናገኛልን፡፡

በእነዚያ የወረርሽኝ ወቅት ውስጥ ደግሞ ክርስቲያኖች እንዴት እንዳለፉ ማወቅ ታሪካዊ ዕውቀታችንን ከመጨመር በዘለለ ዛሬ ያለነው ክርስቲያኖችም ለራሳችን ብሎም ለዓለማችን አንዳች የሚረባ ነገር ለማድርግ እገዛ ስለሚያደርግ ከብዙው ጥቂቱን ካስታወስን በኋላ አሁን የቀረበልንን የቤት ሥራ እንዴት መሥራት እንደሚገባን እንዲሁ ጥቂት እናነሳለን፡፡

በ3ኛው መክዘ የተነሳው የቆጵርያኖስ ወረርሽኝ (The Plague of Cyprian) በመባል የሚጠራውና በገዳይነቱ የሚታወቀው፤ በሮማ ከተማ ብቻ በቀን እስከ 5ሺ ሰዎችን ሕይወት ይቀጥፍ ነበር፡፡ ከዚህም የተነሳ ሰዎች የዓለም ፍጻሜ እንደ ተቃረበ እንዲያስቡ ያደረገ ከባድ ወረርሽኝ ነበር፡፡ በዚያ በአስቸጋሪ ወቅት ክርስቲያኖች – ምሳሌ የሌለውን የክርስቶስን ፍቅር በተግባር በመግለጥ የፍቅር እና የርኅራኄ ተግባራትን ይሠሩ ነበር፡፡ ታላቁ ዲዮናስዮስ ሊቀ ጳጳስ ዘእስክንድርያ እንዲሁም የካርቴጁ ጳጳስ ቅዱስ ቆጵራንዮስም (Cyprian of Carthage) በትምህርቶቻቸው ውስጥ ክርስቲያኖች ያደረጉትን ሥራ ከማበርታት በተጨማሪ በአንክሮና ውብ በሆነ አገላለጽ ገልጸውት እናገኛለን (Eusebius, Ecclesisitical. Hist.7.22.7-10) ፡፡

በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው ዑልያኖስ መምለኬ ጣዖት (Julian the Apostate 361 -363) የሮማ ግዛት ንጉሥ በነበረበት ዘመን እንዲሁ በአፍሪካ እና በምዕራባዊው የሮማን ግዛት ውስጥ ወረርሽኝ ተነስቶ ከባድ አደጋን ጥሎ ነበር፡፡ በለይቶ መቆያ  ውስጥ ከሰው ተለይተው የነበሩ ሰዎችም የመዳን ዕድል ሳይገጥማቸው እየቀሩ በዚያው በተለዩበት ሥፍራ እየሞቱ መቅበር እንኳ አዳጋች ነበር፡፡

በዚያን ዘመን ዑልያኖስ የሚያምነው እምነት (አምልኮ ጣዖት) በሚፈልገው መጠን እና ፍጥነት አልሄደለትም ነበር፡፡ ዑልያኖስ በ362 ወደ ገላትያ እየሄደ ሳለ ካህነ ጣዖት ለነበረው ለአርሳስየስ (Arsacius) በጻፈው መልእክቱ ላይ የእርሱ እምነት (አምልኮ ጣዖት) ሳይስፋፋ በተቃራኒው ክርስትናው እየሰፋ የመጣበትን ምክንያት እንዲህ ሲል አስፍሮ ነበር፡፡

“እነዚህ ገሊላውያን [ክርስቲያኖች] መጻተኞችን ለመቀበል የሚያሳዩት ርኅራኄ፣ ፍቅር፣ የሞቱትን ሰዎች ለመቅበር የሚያደርጉት ጥንቃቄ (ትጋት)፣ የሕይወታቸውን ቅድስና ተመልከት! . . . የእነርሱን ድሆች ብቻ አይደለም የሚረዱት የእኛንም [ጣዖት አምላኪ] ድሆችን ጭምር ነው የሚረዱት፡፡ ስለዚህ ይህንን ሥራ ሁላችንም ማከናወን ይኖርብናል፡፡ ይህ ከአንተ ብቻ የሚጠበቅ አይደለም ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በገላቲያ የሚኖሩ ካህናት [ካህናተ ጣዖት] ጭምር እንዲሁ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ ካህናቱ፣ ሚስቶቻቸው፣ ልጆቻቸው እንዲሁ እንዲያደርጉ አድርጋቸው፤ ካልታዘዙ ግን ከሥራቸው አሰናብታቸው፡፡” [Julian the Apostate, Letters Works vol. 3, Letter 22]

በዚያን ዘመን የነበሩትም ክርስቲያኖች ራሳቸውን መስዋዕት በማድረግ ለሌሎች ለመኖር እጅግ በመትጋት አቅመ ደካማዎችን እና ድሆችን በመርዳት ተጠምደው መልካም ሥራቸው በሰዎች ፊት ብርሃን ሆኗል፡፡ እንዲህ ዐይነት ቀውስ የተከሰተባቸውን ዘመናት ተከትሎ የክርስቲያኖች ቁጥር ከፍ ይል ነበር፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ክርስቲያኖች በዚያን ወቅት በሚያሳዩት አስደናቂ ፍቅር እና ርኅራኄ ሌሎችን መማረክ በመቻላቸው፤ አምላካቸውን በተግባር መስበክ በመቻላቸው ነበር፡፡ እኛስ ዛሬ እንዴት ነው ክርስቲያናዊ ግዴታችንን ለመወጣት መዘጋጀት ሚገባን? ከፊታችን ያለው ትልቁ የቤት ሥራ!

1.1 ክርስቲያናዊ ሕይወታችንን እንዴት እንከባከብ?

በዚህ ወቅት በየዕለቱ ከምንሰማቸው ነገሮች የተነሳ ሙሉ ትኩረታችን ከበሽታው የተነሳ “እሞት ይሆን? እንዴትስ ነው መትረፍ የምችለው” በሚለውን ሐሳብ መያዛችን የማይታበል ሀቅ ነው፡፡ እንዲህ ማሰባችን ሰው ከመሆናችን የመነጨ በመሆኑ በራሱ ላይነቀፍ ይችላል፡፡ ነገር ግን ክርስቲያን እንደመሆናችን ከዚህ በላይ ሊያስጨንቀን የሚገባው የነፍስ ከሥጋ መለየት ሳይሆን ከዘለዓለማዊው ሕይወት የምንለይበትን እውነተኛውን ሞት እንዳንሞት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ይኸውም ከእግዚብሔር መለየት ነው፤ ከእርሱ ጋር ያለን አንድነት እንዳይቋረጥ ስለ እርሱ መጨነቅ አለብን፡፡ እንዴት?

1.1.         ቤታችን ሆነን በጸሎት በመትጋት

በቅዱስ መጽሐፍ ምድር ሁሉ ለእግዚአብሔር ናት ተብሎ እንደተጻፈው ቤተ ክርስቲያን መሄድ የማንችልባቸው ሁኔታዎች ሲኖሩ ቤታችን ውስጥ ጸሎታችንን በማድረስ፤

 • በቤት ውስጥ ሆኖ ስለ መጸለይ በሐዋርያት ዘመን የነበሩ እውነታዎችን መገንዘብ (መጽሐፋዊ ነው)፤
 • ቤት ውስጥ ጸሎት ስናድርግ ልናደርጋቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች (ጥቂት ለማስታወስ)፤
  • የጸሎት ቦታን እንደ ቤታችን ሁኔታ ወስኖ ማዘጋጀት፤
  • ቅዱሳት ስዕላት ፊት መቆም፣ ለክርስቲያን እንደሚገባ መልበስ፣ እግዚአብሔር ጸሎቴን ይሰማኛል በሚል እምነት መጸለይ፣ የእግዚአብሔርን ምሕረት እየጠየቁ አብዝቶ መስገድ፤
  • ቤት ውስጥ የሚደረገው ጸሎት (ከተቻለ የግል እና የቤተሰብ በማለት መለየት ቢቻል) ሁሉም የቤተሰብ አባላት የሚኖራቸው የጸሎት ልምድ ሊለያይ ስለሚችል ሁሉም እንደ አቅሙ እንዲጸልይ ማበረታታት፤
 • ስለ ምን እንጸልይ? (በጸሎት መጻሕፍቶቻችን ከምንጸልየው በተጨማሪ መጨረሻ ላይ)
  • ከአሁን በፊት አምላካችን እግዚአብሔርን ስለ በደልናቸው በደሎች እያስታወስን ስለ በደላችን መጸጸት፣ ማልቀስ፣ እግዚአብሔር እንደ ቸርነቱ መጠን በመላው ዓለም በተለይም በዚህ ወቅት በሕመሙ ተይዘው ለሚሰቃዩት ምሕረትን እንዲልክላቸው፣ የሞቱትንም የቀደመውን ሥራቸውን ይቅር ብሎ ዕረፍተ ነፍስን አንዲሰጣቸው፣ ከዚህ የተነሳ ጽኑ ኀዘን ውስጥ ለወደቁት ቤተሰቦቻቸው መጽናናትን አንዲያድላቸው፣ በሙያቸው ሰዎችን ለማዳን የተቻላቸውን በማድረግ ደፋ ቀና እያሉ ላሉት ባለሙያዎች ብርታቱን እንዲያድላቸው፤ ጥበቡን እንዲሰጣቸው፣ ይህን ወረርሽኝ ምክንያት በማድረግም የሰው ልጅ ሁሉ ወደ ልቡ ተመልሶ እግዚአብሔርን ማሰብ እንዲችል፤ ለተግሳጽ ወይም ለትምህርት የመጣ ደዌ እንዲያደርግ ስለ ሰው ልጆች ሁሉ ብንለምን፣ አላዊቂዎችም “እግዚአብሔር እያለ እኛ ለምን እንዲህ እንሰቃያለን?!” ብለው ይባስ ከእርሱ ለመራቅ ሰይጣን እንደ ምክንያት አድርጎ በሕሊናቸው ውስጥ ክፉ ሐሳብን አሹልኮ እንዳያስገባ ስለ ሰው ሁሉ መጸለይ፡፡

1.2.        ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ

 • በተቻለን መጠን የየዕለቱን ስንክሳር ማንበብ፤ በዕለቱ ወደ ሚታሰቡት ቅዱሳንም ይህንን ደዌ በቃል ኪዳናቸው ከዓለማችን እግዚአብሔር እንዲያርቅልን እንዲያሳስቡልን መማጸን፤
 • መንፈሳዊ ዕውቀት የሚጨምሩልን እና መልካም ዕውቀት የሚገኝባቸውን መጻሕፍትን ማንበብ

1.3.        ለሰዎች በጎ ነገርን በማሰብና በማድረግ

 • ሰዎችን መርዳት የምንችልበት አግባብ ካለ በጥንቃቄ እና በፍቅር በመሆን መርዳት (ኢሳ. 58፡10)፡፡ ብርሃናችን ክርስቶስ በሕይወታችን ተገልጦ ማዕበሉን ፀጥ ያደርግልን ዘንድ ስለ ወገኖቻችን የጌታችንን ደጅ እናንኳኳ፡፡ የቱንም ያህል ደካሞች ብንሆን ስለ ሌሎች ሰዎች ስንጸልይ ስለ ፍቅራችን ሲል ይሰማናልና ስለ ሌሎች ወገኖቻችን መጸለይን ቸል አለማለት (እኔ ማን ሆኜ ነው ስለ ሌሎች የምጸልየው አንበል፤ ነገር ግን እንደቸርነትህ እያልን እናሳስብ እንጂ)፡፡
 • ከቤት ቤት ሄደን መርዳት ባይቻለን ቢያንስ በየጊዜው በመደወል እንጠይቅ፣ በሥራ አጋጣሚ ይሁን በሌላ ምክንያት የተዋወቅናቸው (በተለይም የውጪ ዜጎች፣ በሃይማኖት የማይመስሉን) በዚህ ጊዜ ክርስቲያናዊ ፍቅር በማሳየት ሐዋርያው እንደ ተናገረው የክርስቶስ መዓዛ እንሁን፡፡ [2ቆሮ. 2፡15-16]

1.4.        የንስሐ ሕይወትን በመለማመድ

 • ክርስቲያን እንደመሆናችን የንስሐ አባት ይኖረናል፤ ከአሁን በፊት ንስሐ አባት ካልያዝን አሁን የንስሐ አባት በመያዝ፡፡ የንስሐ አባታችን በሚሰጡን ምክር መሠረት ሕይወታችንን መምራት፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ “ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች።” (ዮሐ 9:4) የተባለው እንዲህ ላለውም ይተረጎማል፡፡

1.5.        ከመረጃ ጎርፍ ራስን በመጠበቅ

 • አእምሮአችን የሰጠነውን ነው የሚሆነው፡፡ ስልኮቻችን እና መሰል መረጃ ማግኛ ቁሳቁሶቻችን ላይም እገዳ መጣል (Quarantine) ያስፈልጋል፡፡ የተመጠነ መረጃ ከማግኘት በዘለለ ሙሉ ቀን የሞቱ ሰዎችን ቁጥር እየቆጠሩ መዋል፣ የመላው ሀገራትን መረጃ በመተንተን ወይም ሲተነተን በማድመጥ ራስን ባተሌ(busy) ከማድረግ መጠንቀቅ፡፡ ይህ ወቅት “ለነጋዴዎች” ጥሩ የመነገጃ ጊዜ ስለሆነ ያልሆነውን እያወሩ ከሚያሸብሩን መርዶ ነጋሪዎች መጠንቀቅ፡፡ ተስፋ የሚያሰንቁን፣ በእምነትና በጥንቃቄ ማለፍ እንደሚቻል ወደ ሚያስተምሩን ሚዲያዎች  ፊታችንን እናዙር፣ ቀልብን በሚገዙ ይልቁንም ደግሞ የንስሐ መዝሙራትን ማድመጥ ይገባናል፡፡

1.6.        ስለ ሚበልጠው ነገር በማሰብ

 • ምናልባት አሁን ሥራ በማቆማችን ወይም ገቢያችን ስለ ቀነሰ ከሚገባው በላይ ማሰብ አይገባም፡፡ በዚህ ወረርሽኝ ሕይወታቸውን ያጡትን፣ ቤተሰባቸውን የተነጠቁትን፣ ይህንንም ተከትሎ የጤና ቀውስ የደረሰባቸውን፣ ትላንት የሞቀው ቤተሰብ ዛሬ ተቀዛቅዞ የኃዘን ድባብ ሰፍኖ ነገሮች ሁሉ በፍጥነት ራሳቸውን የቀያየሩባቸው ሰዎችን ማሰብና የምናውቃቸውም ካሉ መርዳት ተገቢ ነው፡፡ ሰውን በክብር መቅበር መጽሐፋዊ እንዲሁም ባሕላዊም ሆኖ ሳለ ያንን ማድረግ እንኳ ያልቻሉትን እናስብ! በአጠቃላ በእነዚህ ፈተናዎች ውስጥ ስላለፉት እየጸለይን እኛን ደግሞ ከዚያ ስለሠወረን በማመስገን የሚበልጠውን ነገር ማሰብ ራሳችንን ለመጠበቅ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

2.    ለካህናት (ለማስታወስ ያህል)

 • ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ልጆቻችንን በተደጋጋሚ ልናገኛቸው (በስልክ) የሚገባ ጊዜ ነው፡፡ ከአባቶች ለልጆች የምትደርስ አንዲቷ የስልክ ጥሪ ልጆች ላይ የምታሳድረው በጎ ተጽዕኖ እንደ ቀላል ማየት አይገባም፤
 • የሚጠይቅ፣ የሚያበረታ፣ በጸሎትም ከጎናቸው የሚሆን አባት እንዳላቸው በተግባር ሊገለጽላቸው ይገባል፤
 • በአንድም በሌላ ምክንያት ከአሁን በፊት ቤተ ክርስቲያን መሄድ ያልቻሉ ሰዎች በዚህ ወቅት በአንጻራዊነት ቤታቸው ስለሚሆኑ እነርሱም የእግዚአብሔርን ፍቅር እንዲያውቁ ለማድረግ መልካም ዕድል እንደሆነ በማሰብ እነርሱንም ታሳቢ ያደረገ አገልግሎት ማበርከት፤
 • እግዚአብሔር ደዌያትን ከሰው ልጆች ያርቅ ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር በካህናት አንደበት እንደምትጸልይ ምእመናን እንዲያውቁ ማድረግና (በእንተ ዱያን) በዚህም እንዲጽናኑ ማበርታት፤ ምእመናንም እንደ አቅማቸው በጸሎት እንዲተጉ ማበርታት፤
 • ባለ ትዳሮች ቤት ውስጥ ሲያሳልፉ (ረጅም ሰዓት አብሮ ማሳለፍ) በአንዳንድ ቤተሰብ ውስጥ ይህንን ተከትሎ የሚመጣ አለመግባባት እንዳይኖር መንፈሳውያን ልጆቻቸውን በተቻላቸው መጠን በተወሰነ ጊዜያት ማግኘት ቢቻል ጥንዶቹን ከዚህ አንጻር በጋራ ማነጋገር፣ አብረው እንዲጸልዩ፣ ቃለ እግዚአብሔርን እንዲማማሩ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን በጋራ እንዲያነብቡ ማበረታት እንዲሁም መከታተል፤
 • ባለ ትዳሮች ቤት ውስጥ በሚኖሩት ሥራዎች እንዲተጋገዙ መምከር (በመደበኛው ጊዜ የሚከናወን ተግባር ቢሆንም) ሁለቱም ቤት በመዋላቸው ጫናው ወደ አንዱ ብቻ እንዳያመዝን ይልቁንም አንዱ ለአንዱ በማሰብ በመተጋገዝ እርስ በርስ ያላቸውን ፍቅር ይበልጥ ለመግለጽ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ማስረዳት (በሌላ በኩል ፍቅራቸው በተግባር የሚፈተንበት ጊዜ መሆኑን እንዲረዱ ማሳሰብ)፤
 • መጠንቀቅ ማለት አለማመን እንዳልሆነ ለንስሐ ልጆቻችን በተደጋጋሚ ማስረዳት፤
 • ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ምእመናንን ሊቀስጡ ከሚችሉ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ሤራ ራሳቸውን እንዲጠብቁ በተለይም ሚድያዎችን ከመምረጥ ጋር በተያያዘ እንዲሁ ግንዛቤ ማስጨበጥ፤ ከግለሰቦች ሐሳብ ተጠብቀው የቤተ ክርስቲያንን ድምጽ ብቻ እንዲሰሙ፣ በየጊዜውም ከቅዱስ ሲኖዶስ በሚሰጡት መመሪያዎች እንዲመሩ ማሳሰብ፤ በዚህ ወቅት መደበኛውን የአኗኗር ስልት በመከተል መኖር የማይቻልባቸው ሁኔታዎችም ሊኖሩ እንደሚችሉ፤ ዕለታዊ ሕይወታቸው በተድላው ጊዜ በሚያደርጉት መልኩ መምራት ላይቻል እንደሚችል፡ አንዳንድ ሊተውአቸው ወይም ሊያጧቸው የሚችሉ ልምዶች እንዳሉ በማወቅ የሕሊና ዝግጅት እንዲያደርጉ ማስተማር፤

3.   ልጆችን በተመለከተ

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የልጆች ትምህርት ቤት በመዘጋቱ እና ልጆቻችን ቤት ውስጥ በመዋላቸው ለከፍተኛ የስነ ልቡና መቃወስ ሊዳረጉ ይችላሉ። ስለዚህ ልጆች ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ፈተናዎች እና እነዚህን ፈተናዎች ማራቅ እንዲችሉ ወላጆች ሊወስዷቸው የሚችሏቸውን መፍትሔዎች እንደሚከተለው እንጠቁማለን። ለልጆች ፈታኝ የሚሆኑ ጉዳዮች፦

 • ቤት ውስጥ በመዋላቸው ይልቁንም ወደ ውጪ እንደፈለጉ መውጣት እና ከጓደኞቻቸው ጋር በትምህርት ቤት፣ በቤተ ክርስቲያን እና በመጫወቻ ቦታዎች መገናኘት አለመቻላቸው ድብርት እና ሐዘን ሊፈጥርባቸው ይችላል፤
 • ከዜና ማሰራጫ እና ከወላጆቻቸው ስለበሽታው ተደጋጋሚ ከመስማታቸው የተነሳ ስለራሳቸውም ሆነ ስለ ቤተሰቦቻቸው ጤንነት ሊጨነቁ ይችላሉ፣ ቤተሰቡ በረሃብ እና በችግር ሊጠቃ እንደሚችል ከፍ ያለ ስጋት ሊያድርባቸው ይችላል፤
 • ብዙ ጊዜያቸውን ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ (ሞባይላቸው እና ቴሌቪዝን) ላይ ሲያውሉ ሊያድርባቸው የሚችለው ሱስ፣ ስንፍና እና መልካም ያልሆኑ ልማዶች ዘላቂ ጠባሳ ጥለው ሊሄዱ ይችላል፤
 • ከወንድም እና እኅቶቻቸው ጋር ብዙ ሰዓት በአንድ ቤት ውስጥ ከማሳለፋቸው የተነሳ መሰላቸት እና መጣላት እንዲሁም የፍቅር መቀዛቀዝ ሊፈጠር ይችላል። አዳጊዎች ነጻነታቸው የተነፈገ መስሎ ስለሚታያቸው በቤት ውስጥ ግጭት ሊፈጥሩ ይችላሉ፤
 • ወላጆች ሥራ ፈትተው ቤት ውስጥ በመዋላቸው እና/ወይም ሥራ በማጣታቸው ምክንያት በሚፈጠርባቸው ድብርት እንዲሁም በመካከላቸው የፍቅር መቀዝቀዝ እና ቅራኔ ቢፈጠሩ የልጆች ስነ ልቡና ክፉኛ ሊጎዳ ይችላል፤

እነዚህን ከላይ የተጠቀሱ የስነ ልቡና ችግሮች ለመፍታት እና አጋጣሚውን እንደ በጎ ዕድል ለመጠቀም ወላጆች ምን ማድረግ ይቻላሉ?

 • ከትምህርት ቤት ‘’በኦንላይን’’ /Online/ የሚሰጣቸውን ትምህርት እና የቤት ሥራ እንዲሠሩ መከታተል፣ አብሮ መሥራት፣ ተጨማሪ የሚያስፈልግ ከሆነ መጽሐፍትን ‘’በኦንላይን’’ መግዛት እና የሚሠሩትን ሁሉ መርሐ ግብር አውጥተው እንዲሠሩ ማድረግ፤
 • ‘’በኦንላይን’’ /Online/ የአብነት ትምህርትን (የቃል ትምህርቶችን) በቤተ ክርስቲያን አባቶች እና መምህራን እንዲማሩ ማድረግ፤
 • ከልጆቻችን ጋር አብሮ መጸለይ፤ መዝሙር ማስጠናት፣ መጫወት፤ ልጆችን የሚመጥኑ ፊልሞችን ማየት እና መጸሕፍትን ማንበብ፤
 • እንደ አመቺነቱ ግቢ ካለን በዚያ እንዲጫወቱ ማድረግ እና የጋራ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ከልጆች ጋር ማድርግ፤
 • የቤት ጽዳት እና ማስተካከል፣ አበባ እና የጓሮ አትክልትን መንከባከብ እና የመሳሰሉትን የቤት ውስጥ ሥራዎችን አብሮ መሥራት፤
 • የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በተመለከተ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እነርሱ በሚረዱት መጠን ማስረዳት፣ መወያየት እና ከመጸሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን በማንሳት መወያየት፤ ዓለም በሯሷ መቆም እንድማትችል ማስረዳት እና የእግዚአብሔርን መጋቢነት፣ ጠባቂነት እና አዳኝነት በዕድሜያቸው መጠን መግለጽ፤
 • ከስድስት ዓመት በላይ የሆኑ ልጆች በወላጆቻቸው በኩል ከተወሰኑ የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ጋር በስልክ እንዲያወሩ እና በቪድዮ እንዲተያዩ እና ምን እየሠሩ እንደሆነ እንዲጠያየቁ ማድረግ፤
 • እድሜቸው ከ7 ዓመት በላይ የሆኑ ልጆች ጠቃሚ የሆኑ ለምሳሌ የቋንቋ እና የኮምፒውተር ክሂሎቶችን እንዲያዳብሩ ማገዝ። ለምሳሌ ፕሮግራሚንግ እና ኮዲንግ እንዲማሩ የሚከተሉትን ምንጮች መጠቀም ይችላሉ፡- Scrach, w3schools, Tynker, codakids, codespark…
 • የአማርኛ ቋንቋን እንዲማሩ የተለያዩ መንገዶችን መጠቀም፣ ለዚህም ቤት ውስጥ ያሉ መጽሐፍትን እና የተለያዩ መተግበሪያዎችን፦ ለምሳሌ amharicteacher (website)፣ hahubet (youtube), amharicalphabet (app), amharicfidel (app)፣ መጠቀም ይቻላል፤
 • ከ10 ዓመት በላይ ያሉ ልጆች የስልካቸውን እና የኢንተርኔት አጠቃቀማቸውን መከታታል፤ የሚያዩትን እና የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ጋር የሚላላኩትን መረጃ ማየት፤ ለትምህርት መረጃ ለመለዋወጥ ካልሆነ በስተቀር ብዙም እንዳይጠቀሙ ማድረግ፤

4.  ወረርሽኙን ተከትለው የሚመጡ አካላዊና ስነ ልቡናዊ ጉዳቶች እና መፍትሔዎቻቸው፡

የሰው ልጅ በጠባዩ ከሌሎች ሰዎች ጋር አብሮነትን የሚወድ ሲሆን መስተጋብሩም የሕይወቱ ትልቅ አካል ነው፡፡ በወረርሽኙ ምክንያት (ታመውም ሆነ ለቅድመ ጥንቃቄ ተብሎ) ሰዎች ለብቻቸው በአንድ ቤት ተገድበው ለረጅም ጊዜ ሲቆዩ ከፍተኛ የሆነ ስነ ልቡናዊ እና አካላዊ ጉዳት ይደርስባቸዋል፡፡ አሁን ከተከሰተው ወረርሽኝ ጋር ተመሳሳይነት ያለው እና እ.ኤ.አ በ2003 ተከስቶ በነበረው “ሳርስ” ወረርሽኝ ምክንያት በቤታቸው እንዲውሉ ተገድደው በነበሩ ዜጎች ላይ የተደረጉ በርካታ ጥናቶች ሰዎቹ ላይ የአእምሮ ጤና መታወክ፣ የማገናዘብ አቅም መቀነስ እና ደባል ጠባያት ማዳበር እንደተፈጠረባቸው ያሳያሉ፡፡ የጉዳቶቹ መጠን ሰዎች ተለይተው በሚቆዩበት ቀን/ጊዜ/ ርዝመት የሚወሰን ሲሆን ለረጅም ጊዜ ተለይተው የሚቆዩት የበለጠ ሊጎዱ ይችላሉ፡፡ ምእመናን በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ቤት ውስጥ ለረጅም ጊዜ ሲቆዩ አካላዊ እና ስነ ልቡናዊ ጉዳት ሊያመጡ የሚችሉ አራት ዋና ዋና ምክንያቶችን እንጠቁማለን፦

ሀ) ከዐፀደ ቤተክርስቲያን እና ከምስጢራት መለየት፦ ምእመናን ከምስጢራተ ቤተክርስቲያን መለየታቸው እንዳይረጋጉ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ ምእመናን በቤተክርስቲያን ውስጥ አገልግሎቱን በመካፈል፣ ከአባቶች ቡራኬ እና ኑዛዜ በመቀበል፣ ከሚያገኟቸው ሰዎች ጋር በመወያየት ከኀዘናቸው ይጽናናሉ፣ ከጭንቀታቸው ይላቀቃሉ፡፡ ከመገናኛዋ ቤተ ክርስቲያን በሚርቁበት ወቅት የመጽናኛ ዓውደ ምሕረት ስለሚያጡ ለከፍተኛ ጭንቀት ሊጋለጡ ይችላል፡፡

ለ) ከሰዎች ተለይቶ መቀመጥ፦ ከሰዎች ጋር መዋል፣ በሥራ እና በአገልግሎት መገናኘት የሰዎች የደስታ እና የመረጋጋት ምንጭ ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊያን ምእመናን ካላቸው ጠንካራ ማኅበራዊ ሕይወት አንጻር በሚለዩበት ወቅት ለከፋ ለጭንቀት ሊዳረጉ ይችላሉ። ካልተጠነቀቁበት የእንቅልፍ ሥርዓታቸው ሊዛባና የጤና ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል። በሌላ በኩል በባለትዳሮችም ሆነ በወላጆች እና በልጆች መካከል አለመግባባት ሊፈጠር ይችላል፡፡

ሐ) በወረርሽኙ ስለመያዝ መጨነቅ እና የተዛባ የመረጃ ልቀት፦ በቤት ውስጥ ተለይተው ቢቀመጡም በሽታው በምን መልኩ ሊመጣባቸው እንደሚችል በመፍራት እና የተዛቡ መረጃዎችን አብዝቶ በመስማት የሚጨነቁ ይኖራሉ፡፡ በቂ እና የተሟላ መረጃ አለማግኘትም ሌላው የሰዎችን ጭንቀት የሚያባብስ ነገር ነው፡፡

መ) የአካል እንቅስቃሴ መገታት፦ ሰዎች በቀን ውስጥ ለበርካታ ሰዓታት ይንቀሳቀሳሉ፣ ብዙ አዳዲስ ነገሮችንም ያያሉ፡፡ ይህ ተፈጥሯዊ እንቅስቃሴ ሰውነታችን እና አእምሯችን በትክክል እንዲሠራ ያደርገዋል፡፡ በተቃራኒው ሰዎች በአንድ ቦታ/ቤት/ ብቻ ተወስነው በሚኖሩበት ጊዜ የሰውነት ክፍሎች ሕመም፣ የጡንቻ መዛል፣ የደም ዝውውር መቀነስ፣ የክብደት መጨመር፣ የአእምሮ መፍዘዝ ያስከትልባቸዋል፡፡

ለረጅም ጊዜ ከሌሎች ተለይቶ በቤት ውስጥ መኖር ካልተጠነቀቁበት ከፍተኛ የሆነ አካላዊና ስነ ልቡናዊ ጉዳቶችን ሊያስከትል ይባስ ብሎም ለድኅረ ውጥረት በሽታ (Post-traumatic stress disorder) ሊዳርግ ይችላል። ስለዚህም ሳይረፍድ መወሰድ ያለባቸውን መፍትሔዎችን እንደሚከተለው እንጠቁማለን።

4.1 መንፈሳዊ መፍትሔዎች

ይህንን ወቅት በጾም እና በጸሎት ማሳለፍ የሚጠበቅብን በመሆኑ ለብቻ መለየቱን እንደ መልካም አጋጣሚ ለሱባኤ መጠቀምም ይቻላል [መንፈሳዊ መፍትሔዎችን ክፍል አንድ ላይ ይመልከቱ]፡፡

 1. በጸሎት እና መጻሕፍትን በማንበብ አእምሮን ማሠራት፣
 2. ስግደት እና ምጽዋትን ማድረግ፣ የሚያጽናኑ መንፈሳዊ ትምህርቶችን እና መዝሙራትን ማዳመጥ፣

4.2 ሌሎች መፍትሔዎች

መንፈሳዊ ሥራዎችን ከመሥራት በተጨማሪ፣ ሌሎች የአካል እንቅስቃሴዎችንም እንደ ሁኔታው ማድረግ ይገባል፦

 1. የቤት ውስጥ አካል እንቅስቃሴ የሚጠይቁ ሥራዎችን (ለምሳሌ፦ ጽዳት እና ቤት ማዘጋጀት) ማብዛት፣ ቤታችንን እንድንወደው ማድረግ እና በስነልቡና መዘጋጀት፣
 2. የሚቻል ከሆነ የቢሮ ሥራዎችንም በቤት ውስጥ ማስቀጠል፣
 3. በቂ የሆኑ መረጃዎችን ከታማኝ ምንጮች ለተመጠነ ጊዜ እና ልክ መውሰድ፣
 4. ከሚቀርቧቸው ሰዎች ጋር በተመጠነ መልኩ መደዋወል (በተለይ ብቻቸውን ለሚኖሩ)፣
 5. ለሰውነት ጤና የሚጥቅሙ እና የተመጠኑ የሰውነት እንቅስቃሴዎችን/ስፖርት/ ማድረግ፣
 6. አመቺ በሆነ አገር/አካባቢ እያስፈቀዱ በከፍተኛ ጥንቃቄ ከቤት ወጥቶ አየር መቀበል/መራመድ። 

5.  የኮሮና ወረርሽኝ በአውሮፓ በሚገኙ አጥቢያዎች እና በምእመናን ላይ የደቀነው ኢኮኖሚያዊ ፈተና

5.1 በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ በአውሮፓ የሚገኙ አጥቢያዎች የሚገጥማቸው የገቢ ማሽቆልቆል

የተለያዩ ወጪዎች ማለትም የካህናት ደመወዝ፣ የሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ኪራይ እና ግዢ ብድር ክፍያ፣ እንዲሁም ሌሎች ወጪዎች እንዳሉ ሲቀጥሉ ምእመናን በአካል ወደ ቤተ ክርስቲያን ስለማይመጡ የአጥቢያው ገቢ ሊቀንስ ይችላል። ይህንን ችግር ለመፍታት አጥቢያዎች የሚከተሉትን ተግባራት  ቢያደርጉ ይመከራል፡-

 • በቀጥታ ስርጭት (“ላይቭ”) በሚሰጡ የትምህርት እና የቅዳሴ አገልግሎቶች መጨረሻ ላይ ምእመናን በቀጥታ በኢንተርኔት ክፍያ፣ በሞባይል ክፍያ) (ለምሳሌ ለኖርዌይ አገር በቪፕስ) ወይንም በሌላ በቀላል መንገድ ክፍያቸውን ወደ ቤተክርስቲያን ባንክ እንዲልኩ ማስታወቂያ መልቀቅ፣ ተከታታይ ቅስቀሳ መሥራት፤
 • ወረርሽኙን ተከትሎ የአገራት ምጣኔ ሀብት በመናጋቱ ሳብያ መንግሥታት የተለያየ ርምጃ ስለሚወስዱ ከመንግስታቱ የሚገኙ የድጋፍ መንገዶች ካሉ መረጃውን ማግኘት/ማጥናት/ እና መጠቀም፤
 • በሕንጻ ቤተክርስቲያን ግዢ ምክንያት ብድር ያለባቸው አጥቢያዎች የብድር መክፈያ እና የወለድ ሁኔታ እንዲታይ ለባንኮቻቸው ማመልከቻ ማቅረብ እና መከታተል፤

5.2 የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን የአጥቢያው ምእመናን ወቅታዊ ችግር በተመለከተ

የኮሮና ወረርሽኝ ተከትሎ በተለይ በአውሮፓ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ውስጥ የከፋ ችግር ላይ የሚወድቁት የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ወገኖቻችን ናቸው። ምክንያቱም የአገራቱ መንግሥታት የመኖሪያ ፈቃድ ለሌላቸውን ድጋፍ ስለማያደርጉላቸው እንዲሁም ሕጋዊ እንዳልሆኑ ስለሚቆጥሯቸው ነው። እነኝህ የነዋሪነት ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ብዙዎች ከመጠለያ ካምፖች ወጥተው የተለያዩ ሥራዎች እየሠሩ ራሳቸውን ያስተዳድሩ የነበሩ ሲሆን፣ በወረርሽኙ ሳቢያ ይሠሯቸው የነበሩ ሥራዎች በመቆማቸው ለከፋ ችግር ይዳረጋሉ። ይህንን ችግር በከፊልም ቢሆን ለመፍታት አጥቢያዎች የሚከተሉትን ሊያደርጉ ይችላሉ።

 • የድጋፍ ኮሚቴ መመሥረት (በስልክ ውይይት)፤
 • በአጥቢያው የሚታወቁ የመኖሪያ ፈቃድ ለሌላቸው ምእመናን፣ የእርዳታ ዓይነት እና በጠና የተቸገሩትን መለየት፤
 • የገንዘብ እና የዓይነት ድጋፍ ማሰባሰብና እነዚህ ወገኖቻችን ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ፤

5.3 የአብነት ትምህርት ቤቶችን እና ገዳማትን መከላከል ድጋፍ በተመለከተ

በአገር ቤት ወረርሽኝ ሲነሳ በቀዳሚነት ለጥቃት የሚጋለጡት ገዳማት እና የአብነት ትምህርት ቤቶች ናቸው። ለእዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ የመረጃ እጥረት፣ ከሕዝብ መኖሪያ ርቀው ስለሚገኙ በቶሎ ድጋፍ አለማግኘታቸው እና የገዳማቱ የጋራ አኗኗር ዘይቤ ተጠቃሽ ናቸው።

እነዚህ የቤተክርስቲያናችን ሕልውና የጀርባ አጥንት የሆኑት የዕውቀት ምንጮቻችንን የሚጠይቃቸው አካል አለመኖሩም ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ስለሆነም የአብነት ትምህርት ቤቶች ድጋፍ ለማድረግ በአውሮፓ የሚኖሩ ምእመናን በአንጻራነጽ በተሻለ የኢኮኖሚ ሁኔታ ስለሚገኙ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ለአብነት ትምህርት ቤቶች የሚደረገው ድጋፍ ማዕከላዊነቱን እንዲጠበቅ በቅዱስ ሲኖዶስ የተመሠረተውን ግብረ ኃይል ለማገዝ በአውሮፓ ያሉ አጥቢያዎችም ዝግጅት ማድረግ አለባቸው። ስለሆነም በአውሮፓ ያሉ ሀገረ ስብከቶች ግብረ ኃይሉን እና በማዕከላዊነት የሚወጡ መመሪያዎችን ማስተዋወቅ ቢችሉ መልካም ነው።ይህንንም ለመተግበር፡ –

 • በሀገረ ስብከት ደረጃ ውይይት እንዲደረግ እና ለአጥቢያዎች መመሪያ እንዲወርድ ማድረግ፤
 • የገዳማት እና የአብነት ትምህርት ቤቶች ጉዳይ አንገብጋቢ መሆኑን ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ መሥራት፤
 • በአውሮፓ የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ መመሥረት ወይንም ምእመናን በቀጥታ የሚረዱበትን መንገድ እንዲያውቁት ማድረግ፤
 • ወቅታዊ የድጋፍ ሂደቱን የተመለከተ መረጃ ለምእመናን እንዲደርስ ማድረግ የሚሉትን እንጠቁማለን።

6.  የቀጥታ ስርጭት እና ስብሰባዎችን ለማካሄድ የሚረዱ ቴክኖሎጂዎች ጥቆማ

በዚህ የሳንባ ቆልፍ (COVID19) በተስፋፋበትና ሰዎች ሁሉ በቤት ውስጥ ተሰባስበው ባሉበት ጊዜ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖችም ከሚወዷት ቤተ ክርስቲያናቸው ውስጥ የሚሠጠውን አገልግሎት ለማግኘትም አይችሉም። ይሁን እንጂ የዘመኑን ቴክኖሎጅ በመጠቀም ከቤተ ክርስቲያን የሚተላለፉ ትምህርቶችን እና ስብከቶችን መከታተል፣ የጋራ ጸሎት መሳተፍ እና ስብሰባዎችን ማካሄድ ይችላሉ። ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የቴክኖሎጅ ውጤቶች ለአገልግሎት መጠቀም ይቻላል።

6.1 በሁለት ወገን መነጋገር የሚያስችሉ

 

                 ስካይፕ (Skype.com)

 • በአንድ ስብሰባ ውስጥ እስከ 50 ተሳታፊዎች በነጻ መያዝ የሚችል ሲሆን የተሳታፊዎች ብዛት ከ50 በላይ ከሆነ ግን ክፍያ ይጠይቃል።
 • አጭር ማስፈንጠሪያ (short link) በማዘጋጀት በመላክ ተሳታፊዎች ማስፈንጠሪያው ተከትለው እና ስማቸውን አስገብተው] ወደ ስብሰባው ገብተው እንዲሳተፉ ማድረግ ይቻላል።
 • ከሞባይል ወይም ከኮምፒውተር ላይ በተጫነ ሶፍትዌር ወይም በኢንተርኔት ማሰሻ መጥቀም ይቻላል።
 • አጭር ማስፈንጠሪያውን (short link) ከከፈተው ሰው ውጭ ያሉት ተሳታፊዎች አካውንት መክፈት ግዴታቸው አይደለም።
  • ዙም (Zoom.us)
 • በነጻ ከ40 ደቂቃ ለማይረዝሙ ስብሰባዎች እስከ 100 ተሳታፊዎችን መያዝ ይችላል፤
 • ከ100 በላይ ተሳታፊዎችን እና ከ40 ደቂቃ የረዘሙ ስብሰባዎችን ለማድረግ ስብሰባውን የሚጀምረው ሰው በወር ከ20 EUR ያልበለጠ ክፍያ ይጠየቃል፤
 • አጭር ማስፈንጠሪያ (short link) በማዘጋጀት እና በመላክ ተሳታፊዎች፣ ማስፈንጠሪያው ተከትለው ወደ ስብሰባው እንዲገቡ ማድረግ ይቻላል፤
 • ከሞባይል ወይም ከኮምፒውተር ላይ በተጫነ ሶፍትዌር ወይም በኢንተርኔት ማሰሻ (browser) መጥቀም ይቻላል፤
 • ማስፈንጠሪያውን (short link) ከሚፈጥረው ሰው ውጭ ያሉት ተሳታፊዎች አካውንት መክፈት ግድ አይልም፤
 • ኢንተርኔት የሌላቸው ሰዎች በስብሰባው አዘጋጆች በሚሰጥ ስልክ ቁጥር ላይ በመደወል መሳተፍ ይቻላሉ።
  • ጎግል ሀንግአወት (hangouts.google.com)
 • በአንድ ስብሰባ ውስጥ እስከ 100 ተሳታፊዎች በነጻ መያዝ ይችላል፤
 • አጭር ማስፈንጠሪያ (short link) በማዘጋጀት እና በመላክ ተሳታፊዎች ማስፈንጠሪያው ተከትለው ወደ ስብሰባው እንዲገቡ ማድረግ ይቻላል፤
 • ከሞባይል ወይም ከኮምፒውተር ላይ በተጫነ ሶፍትዌር ወይም በኢንተርኔት ማሰሻ መጥቀም ይቻላል፤

6.2 ከአንድ ወገን ብቻ ለሚተላለፉ ቀጥታ ስርጭቶች

በርካታ ተከታታዮች ሲኖሩና የሚተላለፈው መልእክት (ለምሳሌ ትምህርት) ከአንድ ወገን ብቻ ሲሆን በሚከተሉት አማራጮች የቀጥታ ስርጭት ማድረግ የተሻለ ነው።

6.2.1 ዩቲዩብ (YouTube Live)

 • የዩቲዩብ አካውንት በጂሜል ከፍቶ ማስተላለፍ ይችላል፤
 • ተከታታዮች የዩቲዩብ አካውንት መኖር አይጠበቅባቸውም፤
 • አጭር ማስፈንጠሪያ (short link) በማዘጋጀት እና በመላክ ተሳታፊዎች፣ ማስፈንጠሪያው ተከትለው ወደ ስብሰባው እንዲገቡ ማድረግ ይቻላል፤
 • አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ስርጭቱን የተፈቀደላቸው ሰዎች (ለምሳሌ አጭር ማስፈንጠሪያውን ያገኙ ሰዎች) ብቻ እንዲመለከቱት መገደብ ይቻላል፤
 • የቀጥታ ስርጭቱ በዚያው ላይ በቪዲዮ መልክ የሚቀመጥ ስለሆነ ለሌላ ጊዜም ሊያገልግል ይችላል፤
 • አጭር ማስፈንጠሪያውን ያገኘ ሰው በሙሉ ከሞባይል ስልክ፣ ከኮምፕውተር እንዲሁን ከቴሌ ቪዢን ላይ በቀላሉ ማስፈንጠሪያውን በመጫን መርሐ ግብሩን መከታተል ይችላል።

6.2.2 ፌስቡክ (Facebook Live)

 • ስርጭቱን የሚያስተላልፈው የፌስቡክ አካውንት ሊኖረው ያስፈልጋል።
 • ተከታታዮችም የፌስቡክ አካውን ሊኖራቸው ያስፈልጋል። አለዚያ የሚፈልጉትን በጥራት ማየት አይችሉም።

ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ተሳታፊዎች መልእክቱን የሚያስተላልፉ ከሆነም ከላይ በተራ ቁጥር (ሀ) የዘረርናቸውን በመጠቀም ኮንፈረንስ ኮል ካደረጉ በኋላ መልእክቱን በዩቲዩብ እና/ወይም በፌስቡክ በቀጥታ ማስተላለፍ ይቻላል። የቀጥታ ስርጭቶችን ለማስተላለፍ ኦቢኤስ (https://obsproject.com/) የተባለ ሶፍትዌር በመጠቀም ነገሮችን ቀለል ማድረግ ይቻላል።

ማጠቃለያ ፦ በአጠቃላይ በወቅታዊው የኮርና ወረርሽኝ ሳቢያ የሚያጋጥሙ ዘርፈ ብዙ ወቅታዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የመረጃ ፍሰቱን ከማሳለጥ ጀምሮ በአውሮፓ ያሉ ምእመናን፣ ማኅበራት፣ አባቶች፣ እና አህጉረ ስብከቶች ያላቸውን ሚና በሚገባ ተረድተው ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። በተለይ ከችግሩ ድንገተኛነት አንፃር የረጅም ጊዜ አሠራር መንገዶችን የማይፈቅድ በመሆኑ ከጊዜ ጋር መሄድ ያስፈልጋል።