በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ ዐውደ ርእይ ተካሄደ

“ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፤ ድርሻችንን እንወቅ!” በሚል መሪ ቃል በማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማዕከል የጀርመን ን/ማዕከል የተዘጋጀ ዐውደ ርእይ ከነሐሴ ፬ እስከ ፮  ቀን ፳፻፲ ዓ.ም. በጀርመን ሀገር በፍራንክፈርት ከተማ ተካሄደ።

ዐውደ ርእዩን በጸሎት የከፈቱት ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ የአውሮፓ አህጉረ ስብከት ጳጳስ ሲሆኑ  በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ እና በአካባቢ የሚገኙ የአብያተ ከርስቲያናት አስተዳዳሪዎች፣ ተጋባዥ መምህራን እና እንግዶች ተገኝተዋል። ብፁዕነታቸው ዐውደ ርእዩን ሲከፍቱ ባስተላለፉት መልእክት  ስለቤተ ክርስቲያናችን መሠረታዊ አስተምህሮ እና ወቅታዊ ችግሮች የሚያስገነዝቡ እንደዚህ ዓይነት መርሐግብራት ሊበረታቱ የሚገባቸው መሆኑን ገልፀዋል። አያይዘውም በቅርቡ የተፈጸመውን የቤተክርስቲያን  አስተዳደራዊ አንድነት ለማጽናት ካህናት እና ምእመናን በርትተው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው እና ይህንንም በፍቅር እና በመከባበር መንፈስ አብሮ በማገልገል መግለጽ ያስፈልጋል በማለት አባታዊ መመሪያ አስተላልፈዋል፡፡

ዐውደ ርእዩ “የቤተ ክርስትያን አስተምህሮ”፣  “የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት”፣ “የቤተ ክርስቲያን ተጋድሎ”፣ “ምን እናድርግ” እና “ማኅበረ ቅዱሳን ማነው” የሚሉ አምስት ዐበይት ከፍሎች የነበሩት ሲሆን በእያንዳንዱ ክፍል ከፖስተር ገለጻ በተጨማሪ በቪዲዮ የተደገፉ መረጃዎች እና ማብራሪያዎች ቀርበውበታል፡፡  

ከዐውደ ርዕይው በተጨማሪ ጎን ለጎን በመጋቤ ሐዲስ ምሥጢረ ሥላሴ ማናዬ ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል ።  እንዲሁም በትዕይንቱ ላይ ወይም በሌላ ርዕሰ ጉዳይ ጥያቄ ላላቸውም ማብራርያ ሰጥቷል። ለህጻናት እና ለአዳጊዎችም የሚሆን የትምህርት መርሐ ግብርም ተዘጋጅቶ ነበር።  በሦስቱ ቀናት ውስጥ በአጠቃለይ በግምት ወደ 200 አከባቢ የሚሆኑ ምእመናን በአማርኛ የተዘጋጀውን ትዕይንት እንዲሁም 17 ሰዎች ደግሞ የጀርመንኛው ትዕይንት ተመልክተውታል።

በመጨረሻም ዐውደ ርዕዩን የተመለከቱ ጎብኚዎች በሰጡት አስጠያየት በዐውደ ርዕይው ሰፊ ትምህርት እንዳገኙ፤ በሌሎች ከተሞችን እንዲካሄድ ያላቸውን ጉጉት እና ለወደፊቱ እነዚህ መሰለል መርሐ ግብሮች ለማገዝ ዝግጁ እንደሆኑ ገልጸዋል። ይህ ዐውደ ርእይ አውሮፓ ላይ ሲካሄድ የመጀመሪያው ሲሆን በቅርቡ በጀርመን ሀገር በርሊን እና ሙኒክ ከተሞችን ጨምሮ በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት እንደሚካሄድም ለማወቅ ተችሏል፡፡