ብሥራታዊዉ መልአክ

ክፍል ሁለት

ከማርታ ታከለ

የካቲት ፫ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

        እንደምን አላችሁ ልጆች? ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችሁም ጋር ይሁን!

 

ዛሬ በክፍል አንድ መጨረሻ ላይ ያነሳናቸውን ጥያቄዎች በመመለስ እንጀምራለን።

 

ቅዱስ ገብርኤልና ሌሎችም ቅዱሳን መላእክት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ለቁጣም ሆነ ለምህረት ወደሚልካቸው ቦታ እየተላላኩ መኖር ጀመሩ።ለቁጣም ሆነ ለምህረት የሚልካቸው በምድር ወደሚኖሩ ሰዎች ዘንድ ነበር።እነዚህ በምድር የሚኖሩ ሰዎች ማን ፈጠራቸው? ከየት መጡ?ለምንስ በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ይኖሩ ነበር አልን?

 

እግዚአብሔር አምላክ  ከዕለተ እሁድ አንስቶ እስከ ዕለተ አርብ ድረስ ሰማይንና ምድርን የሚታየውንና የማይታየውን ሁሉ ፈጠረ። በስድስተኛው ቀን ሁሉን ፈጥሮ ካዘጋጀ በኋላ ‘ ሰውን እንደመልካችን እንደምሳሌያችን እንፍጠር’ ብሎ ከሌሎቹ ፍጥረታት በተለየ መልኩ አዳምንና ሔዋንን ፈጥሮ የብርሃን ልብስ አልብሶ በገነት አስቀመጣቸው። ሌሎች ፍጥረታት ሁሉ እንዲገዙላቸው አደረገ። ልምላሜዋ ካማረ እና ብዙ ፍሬዎች ካሉባት ገነት ሲያስቀምጣቸው ግን አንድ ትዕዛዝ አዘዛቸው።በገነት ካሉት እጽዋት ሁሉ እንዲበሉ ነገር ግን በገነት መኻከል ካለችው ከዕፀ በለስ ፍሬ እንዳይበሉ አዘዛቸው። እነርሱም ትዕዛዙን አክብረው በደስታና በሐሴት በገነት መኖር ጀመሩ።

 

በዚህ ጊዜ በክፍል አንድ ታሪኩን ያየነው ሀሰተኛው መልአክ ሳጥናኤል በአዳም ላይ ቂም ያዘበት። እግዚአብሔር በእርሱ ምትክ እንደፈጠረውና ብዙ ክብር እንደሰጠው በማየቱ አዳምንና ሔዋንን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያጣላበትን ጊዜ ሲጠብቅ ኖረ።ከዕለታት በአንዱ ቀንም እባብ ሌሎች እንስሳት እንደሚያደርጉት አዳምንና ሔዋንን እጅ ለመንሳት ወይም ስም ሳይወጣለት ቆይቶ ኖሮ አዳም ለሌሎቹ እንስሳት ሁሉ ስም እንዳወጣላቸው ስም እንዲያወጣለት ወደ ገነት ሲሄድ ሳጥናኤል ያገኘዋል።ወዴት እንደሚሄድ ይጠይቀውና እሱም ወደዛው ስለሚሄድ አብረው ጉዟቸውን ይቀጥላሉ። ትንሽ እንደተጓዙ ‘ይህች ወደገነት የምታደርስ መንገድ አድካሚ ናት በየተራ እየተዛዘልን እንሂድ’ብሎ ሳጥናኤል እባብን ይጠይቀዋል በነገሩ ስለተስማማ ቀድሞ እሱ ይሸከመዋል። ትንሽ ከሄዱ በኋላ ያወርደውና በተራው እባብ ላይ ወጥቶ ይታዘልበታል። በዛውም ተፈጥሮው ረቂቅ መንፈስ ስለሆን በሰውነቱ ይገባል።

 

እባብም በገነት ፈሳሾችና አትክልቶች መኻከል ተቀምጣ ወደነበረችው ወደ ሔዋን መጣ። ‘ንግስተ ሰማይ ወምድር  ሆይ ሰላም ላንቺ ይሁን’ ብሎ ሰላምታ አቀረበላት። ሔዋንም ንግስተ ምድር እንጂ ንግስተ ሰማይ አይደለሁም ብላ በማስተካከል ፈንታ እባብ ባቀረበላት በዚህ አዲስ ሰላምታ ደስ ተሰኘች።እባብም  በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? አላት። ሔዋንም ለእባቡ ‘በገነት ካለው ከዛፍ ፍሬ እንበላለን፤ ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ፥ እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም’ ብሎ እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው ነገረችው።  እባብም ‘ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ’ አላት ።

 

በዚህ ጌዜ ሔዋን ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ አየች ከፍሬውም ወሰደችና በላች። ለአዳምም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ።

 

በዚህ ጊዜ የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ። ዕራቁታቸውን እንደ ሆኑ አወቁ። የበለስንም ቅጠሎች ሰፍተው ለራሳቸው ግልድም አደረጉ።ቀኑ በመሸ ጊዜ የእግዚአብሔርን ድምፅ ከገነት ውስጥ ሲመላለስ ሰሙ። አዳምና ሚስቱም ከእግዚአብሔር ፊት በገነት ዛፎች መካከል ተሸሸጉ። እግዚአብሔር አምላክም አዳምን ጠርቶ ‘ወዴት ነህ?’ አለው። እርሱም ‘በገነት ድምፅህን ሰማሁ፤ ዕራቁቴንም ስለ ሆንሁ ፈራሁ፥ ተሸሸግሁም።’ ብሎ መለሰ እግዚአብሔርም ‘ዕራቁትህን እንደ ሆንህ ማን ነገረህ? ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍ በውኑ በላህን?’ ብሎ ጠየቀው አዳምም አለ ‘ከእኔ ጋር እንድትሆን የሰጠኸኝ ሴት እርስዋ ከዛፉ ሰጠችኝና በላሁ።’ አለ። እግዚአብሔር አምላክም ሴቲቱን ‘ይህ ያደረግሽው ምንድር ነው?’ አላት። ሴቲቱም ‘እባብ አሳተኝና በላሁ።’ አለች።

 

እግዚአብሔር አምላክም እባቡን ‘ይህን ስላደረግህ ከእንስሳት ከምድር አራዊትም ሁሉ ተለይተህ አንተ የተረገምህ ትሆናለህ፤ በሆድህም ትሄዳለህ፥ አፈርንም በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ትበላለህ። በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ’ አለው።ለሴቲቱም ‘በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ፤ ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፥ እርሱም ገዥሽ ይሆናል’ አላት።አዳምንም ‘የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ።እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ። ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ፤ አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም ትመለሳለህ’ አለው። እግዚአብሔርም አዳምንና ሔዋንን ትዕዛዙን አላከበሩምና ከገነት አስወጣቸው፥ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በዔድን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ።

 

ከዚህ በኋላ አዳምና ሔዋን በተድላና ደስታ ይኖሩባት ከነበረችው ከገነት ተባረው ከገነት ፍጹም ከተለየችው ምድር ላይ ራሳቸውን አገኙ። በዚያም በጣም በሀዘንና በለቅሶ መኖር ጀመሩ። አዳምም ራሱን እስኪስትና በድን እስኪሆን ጊዜ ድረስ ደረቱን እየመታና እያለቀሰ ከእግዚአብሔር ይቅርታን ይለምን ነበር። ሔዋንም በእኔ ምክንያት ይህ ሁሉ ቅጣት መጣብን እግዚአብሔርን አሳዘንን።እግዚአብሔርን ያህል ጌታ ገነትን ያህል ቦታ አጣን እያሉ። ብዙ ሱባኤና ጸሎት ያዙ። እግዚአብሔርም አጥብቀው ይቅርታውን ስለፈለጉ፥ ‘ከ5500 ዘመን በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ’ በማለት ቃል ኪዳን ገባላቸው። እነርሱም ልጆች ወልደውና ብዙ ሆነው የማዳኑን ቀን ሲጠባበቁ ኖሩ።

 

ስለዚህ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም በጨለማና በሞት ጥላ ሲኖሩ ለቆዩት የአዳም ልጆች ቅዱስ ገብርኤል የምስራች ዜና ይዞ እንዲወርድ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ።

 

ልጆች ቅዱስ ገብርኤል የምስራቹን ሊናገር የመጣው ወይም የተላከው ወደማን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ይህንን በቀጣይ ክፍል እንመለከተዋለን።

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክብር!