ሆሣዕና

በዲ/ን ብሩክ አሸናፊ

መጋቢት 23 ቀን 2010 ዓ.ም.

ሆሣዕና ማለት መድኃኒት ማለት ነው። ሆሣዕና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ እና በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ከሕዝቡም ብዙዎች ልብሳቸውንና የዘንባባ ዝንጣፊ በመንገድ እያነጠፉለት የሚቀድሙትም የሚከተሉትም ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ሥም የሚመጣ ቡሩክ ነው ሆሣዕና በአርያም እያሉ እያመሰገኑት ወደ ኢየሩሳሌም የገባበትና የለዋጮችን ገበታዎችና የርግብ ሻጮችን ወንበሮች ገልብጦ ቤተ መቅደሱን ያነጻበት እና ለአምልኮ ብቻ የቀደሰበት በዓል ነው።

ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ሊገባ በቀረበ ጊዜ በደብረ ዘይት አጠገብ ከምትገኝ ቤተ ፋጌ ሲደርስ ሰው ሁሉ ከማዕሠረ ኃጢአት የሚፈታበት ጊዜ እንደደረሰ ለማጠየቅ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ በዚያም አህያ ከውርንጫዋ ጋር ታስራ ታገኛላችሁ ፤ ፈታችሁ አምጡልኝ ፤ ማንም አንዳች ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ ሲል ላካቸው። መንደር የሲዖል ፣ አህያይቱና ውርንጫይቱ የአዳምና የልጆቹ ፣ በመንደር መታሰራቸው አዳምና ልጆቹ በመርገመ ሥጋ በመርገመ ነፍስ ተይዘው በሲዖል በባርነት መኖራቸውንና ጌታችንም የሲዖል ባርነት አስወግዶ ነጻነትን የሚያድልበት ጊዜ እንደቀረበ ያጠይቃል። ዛሬም እኛ ልጆቹ በማዕሰረ ኃጢአት ተይዘን ከእርሱ ስንርቅ ከማዕሰረ ኃጢአት ፈትተው ወደርሱ የሚያቀርቡንን ካህናትን ሰጥቶናል።

ደቀ መዛሙርቱም ሄደው አህያይቱንና ውርንጫይቱን አመጡለት ፤ ልብስ የአካልን ነውር እንደሚሰውር አንተም ከባቴ አበሳ ነህ ሲሉ ልብሳቸውን እንደኮርቻ ጎዘጎዙለት። አምላካችንም በሁለቱም ላይ በጥበብ ተቀመጠባቸው። በአህያ መቀመጡ ስለ ምን ነው? ቢሉ ፡

  1. ትንቢቱንና ምሳሌውን ለመፈጸም።

ትንቢት “የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በይ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ትሑትም ሆኖ በአህያም በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣልዘካ 9:9 ተብሎ በዘካርያስ የተተነበየው።

ምሳሌ ቀድሞ አባቶች ነቢያት ዘመነ ጸብዕ እንደሆነ በፈረስ ተቀምጠው ዘገር ነጥቀው ይታያሉ ፤ ዘመነ ሰላም የሆነ እንደሆነ በአህያ ተቀምጠው መነሳንስ ይዘው ይታያሉና ዘመነ ሰላም ደረሰ ሲል።

  1. በአህያ የተቀመጠ ሸሽቶ አያመልጥም አሳዶም አይዝም ፤ እርሱም ካልሹኝ አልገኝም ከሹኝም አልታጣም ሲል።

  2. በትሑታን አድሬባቸው እኖራለው ሲል።

  3. አህያ ቀንበር መሸከም የለመደች እንደሆነች እስራኤልም ሕግ መጠበቅ ለምደዋልና ውርንጫይቱ ቀንበር መሸከም ያልመደች እንደሆነች አህዛብም ሕግ መጠበቅ ያለመዱ ናቸውና።

  4. አህያ የኦሪት ምሳሌ ኦሪት የተለመደች ሕግ ናትና ፤ ውርንጫይቱ የወንጌል ምሳሌ ወንጌል ያልተለመደች ሕግ ናትና።

ከሕዝቡም ብዙዎች እንኳን ለአንተ የተቀመጥክበትም መሬት መንካት አይገባውም ሲሉ ልብሳቸውን በጎዳና አነጠፉለት። አንድም በአዩ ልማድ ኤልሳዕ አዩን ቅብዐ መንግሥት በቀባው ጊዜ ከጓደኞቹ እኩሌቶቹ አነጽፈዋል እኩሌቶቹም ጋርደዋል። አብርሐም ይስሐቅን ፣ ይስሕቅ ያዕቆብን በወለዱ ጊዜ ፣ እስራኤላውያን ከግብጽ በወጡ ጊዜ ሰሌን ይዘው አመስግነዋልና በአበው ልማድ ሌሎቹም ከዛፍ (ዘንባባ ፣ ቴምርና ወይራ) ጫፍ ጫፉን እየቆረጡ ከመንገድ ያነጥፉ ነበር። ዘንባባ እሾህማ ነው ትምህርተ መዊዕ አለህ ሲሉ ፣ ለብልቦ ይተወዋል እንጂ እሳት አይበላውም ባህርይህ አይመረመርም ሲሉ። ቴምር ልዑል ነው ልዑለ ባህርይ ነህ ሲሉ ፤ ፍሬው አንድ ነው ዋህደ ባህርይ ነህ ሲሉ ፤ ፍሬው በእሾህ የተከበበ ነው ባህርይህ አይመረመርም ሲሉ፤ ዘይት ጽኑዕ ነው ጽኑዐ ባህርይ ነህ ሲሉ ፤ መስዋዕት ነው መስዋዕት ትሆናለህ ሲሉ።

ህዝቡም ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ሥም የሚመጣ ቡሩክ ነው ሆሣዕና በአርያም እያሉ እያመሰገኑት። ከዳዊት ዘር ከተወለደች ከቅድስተ ቅዱሳን ከድንግል ማርያም በመወለዱ የዳዊት አምላክ የዳዊት ልጅ ተባለ። የዳዊት ልጅ መድኃኒት መባል ይገባዋል አሉ። በእግዚአብሔር ሥም የሚመጣ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ የሚመጣ ፤ እግዚአብሔር መስክሮለት የሚመጣ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለበት በረከተ ሥጋን በረከተ ነፍስን የሚያድል ሆሣዕና በአርያም በሰማይ ያለ መድኃኒት ነው እያሉ አመሰገኑት። ከዚህ የምሥጋና ድምጽ የተነሳም ይህ ማን ነው? እንዲህ ያለ የምሥጋና ጎርፍ የሚጎርፍለት ማን ነው? ብላ ከተማይቱ ተናወጠች። እናንት መኳንንቶች በሮችን ክፈቱ የዘላለም ደጆች ይከፈቱ የክብር ንጉሥ ይግባ። ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው? እግዚአብሔር ነው ብርቱና ኃያል እግዚአብሔር ነው በሰልፍ ኃያል። እናንት መኳንንቶች በሮችን ክፈቱ የዘላለም ደጆች ይከፈቱ የክብር ንጉሥ ይግባ። ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው? የጭፍሮች አምላክ እግዚአብሔር እርሱ የክብር ንጉሥ ነው።መዝ 23:7-10

ጌታችንም ወደ መቅደስ ገባና በመቅደስ የሚሸጡትንም የሚገዙትንም ሁሉ አወጣ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠና ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፏል እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋቹኋት ብሎ ቤተ መቅደሱን አነጻ ለአምልኮ ብቻም ለየ።

በመቅደስም ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ ቀረቡና ፈወሳቸው። ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ድንቃድንቅ በመቅደስም ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮሁትን ልጆች ባዩ ጊዜ ተቆጥተው ዝም እንዲያሰኝላቸው የሚሉትን አትሰማምን? አሉት። አምላካችንም እሰማለሁ ከሕጻናትና ከሚጠቡ አፍ ምሥጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁትምን? አላቸውና ትቷቸው ከከተማ ወደ ቢታንያ ወጣ።ማቴ 21:1-17

ቅዱስ ጳውሎስ ዝሙትና አምልኮ ጣዖት ነግሶባት በነበረችው በቆሮንቶስ ከተማ ለሚኖሩ ሰዎች በላከው መልዕክቱ ላይ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁ የእግዚአብሔር መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን?” 1ቆሮ 3:16 ብሎ ህንጻ ሰውነታቸውን የኃጢአት መሸጫና መለወጫ እንዳያደርጉትና ለእግዚአብሔር እንዲለዩት አሳስቧቸዋል።  በልባችን ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ምዋርት፣ ጥል፣ ክርክር፣ ቅንዓት፣ ቁጣ፣ አድመኝነት፣ መለያየት፣ መናፍቅነት፣ ምቀኝነት፣ መግደል፣ ስካር፣ ዘፋኝነት እና ይህንን የመሳሰሉት ከነገሡ ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ እያሳዘንን ነውና ወደ መምህረ ንስሐዎቻችን ቀርበን ከማእሰረ ኃጢአት ተፈተን ልባችንን ልናነጻ ይገባናል። ከክፉ መሸሽ መልካምን ማድረግ ይገባልና በምትኩ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት እና ራስን መግዛትን ገንዘብ አድርገን መቅደስ የሆነ ሰውነታችንን ለእግዚአብሔር ልንለይ ያስፈልጋል። ገላ 5:19-23 ከማእሰረ ኃጢአታችን በንስሐ ተፈተን፣ መልካም ሥራን ሰርተን፣ ቅዱስ ሥጋውን ስንበላ፣ ክቡር ደሙን ስንጠጣ የእግዚአብሔር ማደሪያዎች እንሆናለን የእግዚአብሔርም ሥራ በቅዱሳኑ እንደተገለጠ በእኛም ይገለጣል። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል ፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁዮሐ 6:56። ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከመላእክቱ፣ ከቅዱሳኑ፣ ከሕጻናቱ ጋር ሆነን ንጉሡን ኢየሱስ ክርስቶስን የምሥጋና ጎርፍ በሚፈልቅባት፣ ምስጋናው በማይቋረጥባት በኢየሩሳሌም ሰማያዊት በመንግሥተ ሰማይ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያልን እንድናመሰግነው አምላከ ድንግል ማርያም ይርዳን።

ይቆየን

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!