ሠለስቱ ደቂቅ በትውልድ መካከል
በአባ ዘሚካኤል ደሬሳ
ታኅሣሥ 18 ቀን 2009 ዓ.ም
ትውልድ ያልፋል ትውልድ ይመጣል። ያልፈው ትውልድ እንደ እምነቱ እና እንደስሥራው ወይ ገነት ወይ ሲዖል ይኖራል። አዲሱ ትውልድ እንዲሁ የዚህን ዓለም ኑሮ ጊዜው ባመቻቸለት ሁኔታ ለሚቀጥለው ዘላለማዊ ሕይወት ወይ ለመንግስተ ሰማያት ወይ ለገኃነመ እሳት እራሱን ያዘጋጃል። ነገር ግን በትውልድ መካከል ሁልጊዜም እግዚአብሔር እንደትውልዱ የእምነት ፍላጎትና ጽናት መጠን ራሱን ይገልጻል። እንደሠለስቱ ደቂቅ ያለምንም አማራጭ በርሱ ሲተማመኑና እራሳችውን ከማንም በላይ ለርሱ አሳልፈው ሲሰጡ እግዚአብሔር አብሮአቸው መሆኑን ያረጋግጣል። እሱ ማንንም አሳፍሮ አያውቅም። ስለዚህም በነነቢዩ ዳንአልና ሠለስቱ ደቂቅ አናንያ፣ አዛርያና ሚሳአል ትውልድ ዘመን እግዚአብሐር በድንቅ ተአምራቱ በቅዱስ ገብርአል አሳይቶ ነበር።
በዚያ ዘመን ዓለማዊው የባቢሎን ንጉስ ናቡከደነጾር የኢየሩሳሌምን ከተማ በጦር ኃይል ማረካት፣ ህዝቡንም ለራሱ ጣዖት አምልኮ አዘጋጀ። እንደ ዛሬ ዘመን ማራኪ ሰዎች ወይም አድናቂ ፈላጊዎች ከእስራአል ልጆች መልከ መልካሞቹን፣ ጥበበኞቹን፣ ግርማ ሞገስ ያላችውን፣ ሰግደው ለጣዖት በማሰገድ በንጉሱ ፊት መቆም የሚችሉትን እንዲመርጡ አዘዘ። የከለዳውያንን ትምህርትና ቋንቋ እንዲያስተምሩ፣ የጣዖት አምልኮም ስልጠና እንዲሰጧቸው አስጠንቀቃቸው። ዛሬም ዓለማዊነት እንደ ናቡከደነጾር በኃይል ሳይሆን ባሰለጠናቸው ምድራውያን ሰውን ልቦና በሰለጠነ/በሰየጠነ መንገድ ወርሮ በግልጽ ላልቆመ ጣዖት በየአንዳንዱ ልቦና ሲሆን በተደናቂነት ባይሆን በአድናቂነት ስሜት መስጦ እያሰገደ ወጥመዱን ዘርግቷል።
በዚያ ዘመን ከነበሩት ሕዝብ መካከል ከይሁዳ የመጡ እግዚአብሔርን በእውነት የሚያምኑ እስራኤላውያን ነቢዩ ዳንአልና ሠለስቱ ደቂቅ አናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤል ነበሩ። እነሱ ባይቀበሉትም እንኳን ያለ ፈቃዳቸው የናቡከደነጾር ባሪያ እንደርሱ ያለ የግብር ስም አወጣላችው፣ ዳንኤልን ብልጣሶር፣ አናንያን ሲድራቅ፣ ሚሳአልን ሚሳቅ፣ አዛርያን አብድናጎ ብሎ ሰየማቸው። በአንጻሩ ደግሞ ዛሬ በዚህ ትውልድ የምናየው የባርነት ይሁን የነጻነት ያላስተዋልነው ስመ ግብርናት በፈቃዳችን ለነጻነት በመልካም ልጅነት ጊዜ የተነቀሱትን መስቀል በኋላ አድገው አፍረውበት ፍቀው የሚያጠፉትን እነሆ እናያለን። ሌሎች ደግሞ ሰለጠንን ብለው የአጋንንትንና ልዩ ልዩ የአውሬው ምሳሌ የሆኑትን አራዊት ሲነቀሱና በመፈንሱ ምልክት ሲታተሙበት ተመልክተናል። አረ ስንቱ እግዚአብሔርና እራስንም ጨምሮ ማንነትን የመካድ ምሳሌ ነግሶ፣ ገዝፎ ተንሰራፍቷል። ይህ ሁሉ ለሥጋ ድሎት ሲባል ይሆን?
አልወደዱትም እንጂ ለሥጋ ድሎትማ ከእስራአል ልጆች የተመረጡት ሠለስቱ ደቂቅ የተለየ አመጋገብ፣ ልዩ ጥንቃቄና ስልጠና እንዲደረግላቸው በናቡከደነጾር ተወስኖላችው ነበር። በአንጻሩም ፍቅረ እግዚአብሔርን የተመሉ ዳንኤልና ሠለስቱ ደቂቅ በከለዳውያን ትምህርትና ቋንቋ የጣዖት አምልኮም ስልጠና እንዲሁም በጣዖት አምልኮ የረከሰ መብልና ጠጅ እንዳይረክሱ ልዩ ጥንቃቄ አድርገው ነበር። እንዲያውም እግዚአብሔር እንዳይለያቸው ከማንኛውም የርኩሰት ንክኪ ራሳችውን ጠበቁ። እርም የሆነውን ሁሉ እንዳይመገቡም የጃንደረቦቹን አለቃ ለመኑት። “የጃንደረቦቹም አለቃ ዳንኤልን መብሉንና መጠጡን ያዘዘላችሁን ጌታዬን ንጉሡን እፈራለሁ፤ በዕድሜ እንደ እናንተ ካሉ ብላቴኖች ይልቅ ፊታችሁ ከስቶ ያየ እንደ ሆነ፥ ከንጉሡ ዘንድ በራሴ ታስፈርዱብኛላችሁ አለው። ዳንኤልም እኛን ባሪያዎችህን አሥር ቀን ያህል ትፈትነን ዘንድ እለምንሃለሁ፤ የምንበላውንም ጥራጥሬ የምንጠጣውንም ውኃ ይስጡን፤ ከዚያም በኋላ የእኛን ፊትና ከንጉሡ መብል የሚበሉትን የብላቴኖችን ፊት ተመልከት አለው። ይህንም ነገራቸውን ሰምቶ አሥር ቀን ፈተናቸው። ከአሥር ቀንም በኋላ ከንጉሡ መብል ከበሉ ብላቴኖች ሁሉ ይልቅ ፊታቸው አምሮ ሥጋቸውም ወፍሮ ታየ። ሜልዳርም መብላቸውንና የሚጠጡትን ጠጅ አስቀርቶ ጥራጥሬውን ሰጣቸው። “ (ት.ዳን 1)። የዚህን ትውልድ ህይወት ስንመለከት እንደ ሠለስቱ ደቂቅ ያሉ በዓለማዊ ትምህርት ተውጠው እግዚአብሔርን ያልካዱ፣ ለዚህ ዓለም ምግብ ጎምዥተው ጾም ያልተዉ፣ እርም የሆነውን ያልነኩ እንዳሉ ሁሉ፣ በተቃራኒው እንኳን ሊጾሙ እምነታቸውን የተዉና ማንናታችውን የዘነጉ፣ በአውሬው መንፈስ የተዋጡ እንዳሉ መዘንጋት የለብንም። እኛ ራሳችን ምን ያህል ማንነታችንን እርም ጠብቀን ይሆን?
ከላይ እንዳየነው ለእግዚአብሔር ክብር ብለው እንዳይረክሱ ራሳቸውን ከጣዖት ቅሬታ የጠበቁትን፣ ማንነታችውን ያልካዱትን፣ በአምላካችው የታመኑትን እንዴት እግዚአብሔር በዓለማዊው ንጉስ ፊት እንዳከብራቸው ተመልከቱ። እሱ አምላክ እውቀት፣ ጥበብ፣ ማስተዋል እንደመላቸው ቃሉ ያስረዳናል። “አራቱ ብላቴኖች እግዚአብሔር በትምህርትና በጥበብ ሁሉ እውቀትንና ማስተዋልን ሰጣቸው፤ ዳንኤልም በራእይና በሕልም ሁሉ አስተዋይ ነበረ። ንጉሡም በተነጋገራቸው ጊዜ ከብላቴኖቹ ሁሉ እንደ ዳንኤልና እንደ አናንያ እንደ ሚሳኤልና እንደ አዛርያ ያለ አልተገኘም። ንጉሡም በጠየቃቸው በጥበብና በማስተዋል ነገር ሁሉ በግዛቱ ሁሉ ከሚኖሩ የሕልም ተርጓሚዎችና አስማተኞች ሁሉ እነርሱ አሥር እጅ የበለጡ ሆነው አገኘባቸው። “(ት፣ዳን 1)። ትውልዱ ይህን በአምላክ ታምኖ መክበርን አስተውሎ ይሆን? አንዳንዶች ያልፍልኛል በሚል ሰበብ እምነታችውን፣ ማንነታችውን፣ ስማችውን ወዘተ ክደው ያሰቡት ሳይሳላካ ትርፉ ጭንቀት ብቻ የሆነባቸው ሞልተዋል። በሀገራችው አዛዥ የነበሩ፣ በእውቀት ብዙ የደከሙ፣ በልምድ የዳበረ ማንነት የነበራችው፣ ማንነታችው ጋሽቦ፣ ለመታዘዝ እንኳን በአግባቡ ክብር ያላገኙ በየመጠለያው እድሜያቸውን የፈጁ እንዳሉ ለብዙዎች ግልጽ ነው።
በነሠለስቱ ደቂቅ ዘመን እግዚአብሔር ልጆቹን የሚፈልግበት የቁርጥ ቀን መጣ። ፈተናው በሰው ፊት እጅግ ከባድ ነበር። በመልካም ጊዜ ሁሉም አለሁ ሊል ይችላል፣ ጉዱ ግን የቁርጥ ቀን የደረሰ ጊዜ ነው። ከጥቂቱ ሰው በቀር ሁሉ በአንድ ላይ እግዚአብሔርን ትቶ ለጣዖት የሚሰግድበት ቀን ሲደርስ እንዲህ ነው። ንጉሡ ናቡከደነፆር ቁመቱ ስድሳ ክንድ ወርዱም ስድስት ክንድ የሆነውን የወርቁን ምስል አሠርቶ በባቢሎንም አውራጃ በዱራ ሜዳ አቆመው። ንጉሱም ባለስልጣናቱን መኳንንትንና ሹማምቶችን፥ አዛዦችንና አዛውንቶችን፥ ሕዝቡንም ሁሉ ላቆመው ምስል ምረቃ ይመጡ ዘንድ ላከ። እንደታአዘዘው የተጠሩ ሁሉ ናቡከደነፆርም ባቆመው ምስል ፊት ቆሙ። የፈተናው ሰዓት በግልጽ ደርሶ፣ አዋጅ ነጋሪውም እየጮኸ እንዲህ አለ። “ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የምትናገሩ ሆይ፥ የመለከትንና የእንቢልታን፥ የመሰንቆንና የክራርን፥ የበገናንና የዋሽንትን፥ የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ፥ ተደፍታችሁ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቁ ምስል እንድትሰግዱ ታዝዛችኋል። ተደፍቶም የማይሰግድ በዚያን ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣላል” (ት.ዳን . 3)። በዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሕዛብ እና እንዲሁም ንጉሱን የፈሩ ሁሉ የመለከቱንና የእንቢልታውን፥ የመሰንቆውንና የክራሩን፥ የበገናውንና የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ በሰሙ ጊዜ ተደፉ፥ ንጉሡም ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቅ ምስል ሰገዱ። ጽኑዓን ሠለስቱ ደቂቅ እራሳችውን ከርኩሰት የጠብቁ፣ እየጠብቁ ያሉቱ ግን ራሳቸውን ለጣዖት ዝቅ አላደረጉም፣ በአምላካቸው እግዚአብሔር ታምነዋልና።
ነገር ግን ከሳሾች መጥተው እንዲህ የሚል ክስ አቀረቡ “በባቢሎን አውራጃ ሥራ ላይ የሾምሃቸው ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም የሚባሉ አይሁድ አሉ፤ ንጉሥ ሆይ፥ እነዚህ ሰዎች ትእዛዝህን እንቢ ብለዋል፤ አማልክትህን አያመልኩም፥ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል አይሰግዱም።”(ት. ዳን. 3)። ንጉሱም ተቆጥቶ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎንም ያመጡ ዘንድ አዘዘ፤ እንዲህም ሲል ጠየቃቸው “ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም ሆይ፥ አምላኬን አለማምለካችሁ፥ ላቆምሁትም ለወርቁ ምስል አለመስገዳችሁ እውነት ነውን? አሁንም የመለከቱንና የእንቢልታውን የመሰንቆውንና የክራሩን የበገናውንና የዋሽንቱን የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ተደፍታችሁ ላሠራሁት ምስል ብትሰግዱ መልካም ነው፤ ባትሰግዱ ግን በዚያ ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ትጣላላችሁ፤ ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው?” (ት.ዳን. 3) ብሎ በቁጣና በኃይል ተናገራቸው። የእግዚአብሔር መንፈስ ያደረባቸው ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም ግን በትህትና እንዲህ ሲሉ መለሱ፣ “ናቡከደነፆር ሆይ፥ በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም። የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፥ ነገር ግን፥ ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ባያድነን፥ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ አሉት።”(ት. ዳን. 3)።
ትውልዱ ይህንን የጽናት ቃል፣ የሞትና የሽረት ቃል፣ እራስን አሳልፎ ለአምላክ የመስጠት ቃል፣ የመጨረሻ ቃል ኪዳን ሊያስተውለው ግድ ይለናል። ቅዱሳኑ በድፍረት ”ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ባያድነን፥ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ።” ነበር ያሉት። ይህ ትውልድ በአብዛኛው እንዲህ ያለ የጽናት ቃል አለው ይሆን? ከእምነት አንጻር ስናየው ዓለማዊነት ውጦት፣ ነገርን ሁሉ በአፍላ ይጀምራል በወረት ይተዋል። ምኞቱ ልክ የለውም፣ አምሮቱ ብዙ ነው። ያማረውን ሲያገኝ ገና ሳያጣጥመው ፈጥኖ ይሰለቸዋል። ያወቀውን ይረሳል ላላወቀው ይጓጓል። የያዘውን ማንነት ይረግማል፣ ያናንቃል፣ ይክዳል፣ ይረግጣል፣ የሚጨብጠው ሲያጣ የረገጠውን መልሶ ያነሳል። የተከለከለውን፣ ተው የተባለውን ይሽራል። እርም ይነካል። የታፈረውን ይደፍራል። የተከበረውን ያዋርዳል። የተፈቀደለትን አይጠቀምበት፣ በክብር አይዝም፣ በቸልታ ይመለከታል። ሁሉን ሊያውቅ ይሻል፣ አንዱን አያስተውል። ሁሉ እያለው፣ ምንም የለው። እንደሠለስቱ ደቂቅ መቼ ይሆን? ባለው ማንነቱና እምነቱ እርግጥ ጭብጥ ያለ እርጋታን የሚያገኘው። (እመጓ 162)
ሠለስቱ ደቂቅ ግን ከላይ እንደተገለጽው እራሳችውን እርም ከሆነ ንክኪ የጠበቁ የእግዚአብሔር ባርያዎች በመሆናችው አፍላነት ያልበገራችው፣ ምኞት ያላማለላቸው፣ ማንነትን የወደዱ፣ አምላካችውን ያከብሩ፣ ፍጻሜውን የተረዱ፣ ለመጨረሻው ቃል ኪዳን የታመኑ፣ የታደሉ በመሆናቸው “አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ“ ባሉት ጊዜ ናቡከደነፆር በሲድራቅና በሚሳቅ በአብደናጎም ላይ ተቆጣ እንዲህም አለ፥ “የእቶንም እሳት ይነድድ ከነበረው ይልቅ ሰባት እጥፍ አድርገው እንዲያነድዱት አዘዘ። ሲድራቅንና ሚሳቅንም አብደናጎንም ያስሩ ዘንድ፥ ወደሚነድድም ወደ እቶን እሳት ይጥሏቸው ዘንድ በሠራዊቱ ውስጥ ከነበሩት ኃያላን አዘዘ።“ እንዳዘዘም ወደ እሳቱ ተጣሉ። የንጉሡም ትእዛዝ አስቸኳይ ስለሆነ የእቶኑም እሳት እጅግ ስለሚነድድ፥ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎንንም ወደ እሳት የጣሏቸውን ኃያላን ሰዎች የእሳቱ ወላፈን ገደላቸው።
ይገርማል! እሳቱ እንኳን አውቆ ለራሱ የተዘጋጁትን ትቶ የጣዖት አደግዳጊዎች ሰዎችን በላ፣ ቃሉ “ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎንም የጣሉአቸውን ኃያላን ሰዎች የእሳቱ ወላፈን ገደላቸው “ ይለናል። የዘመኑ ዓለማዊነት አደግዳጊዎችም እንዲሁ ናቸው። የእውነት አምላክን ትተው ለሥጋ ያጎበጉባሉ፣ ያራግባሉ፣ ያናፍሳሉ ወዘተ፣ ግን የእሳቱ ሰለባዎቹ እነሱ ናችው። የዝሙት ሰለባዎች፣ የጭፈራ ቤት ሰለባዎች፣ የአሺሽ ሰላባዎች፣ የቁማር ሰለባዎች፣ የአመጽ ሰለባዎች፣ የመለያየት ሰለባዎች፣ ራስ ወዳዶች፣ ውሸታሞች፣ አድር ባዮች፣ ሸፍጥኞች፣ ተኮለኞች፣ ወዘተ በመሆናቸው የቆሰቆሱት የእሳት ወላፈን መዘዝ ጠንቁና የጨበጡት የግፍ ደም ቆይቶም ቢሆን እራሳችውን ሳይበላ አይቀርም። ወደእሳቱ የተጣሉት ግፉዓን ግን አልተቃጠሉም፣ ከእሳቱ አቅም በላይ ሆኑ፣ ለምን ወጣቶቹ የታመኑለት አምላክ ከእሳት አቅም በላይ ነው። ከነገሮች ሁሉ አቅም በለይ ነው። ስለዚህ እሱ ስለተዋሃዳችው ሊያቃጥላቸው አልቻለም። በአስደናቂ ሁኔታ መልአኩን ቅዱስ ገብርአልን ልኮ አዳናቸው::
ቅዱስ እግዚአብሔር በሠለስቱ ደቂቅ ጽናት ውስጥ ሆኖ ናቡከደነጾርን አፉን ከፍቶ ፊቱን ጸፍቶ አናገረው። በተአምራቱ አስደነቀው። በችሎታው ማረከው። እርሱ በፊቱ ታማኝ ምስክሮቹን ሠለስቱ ደቂቅን አግኝቱዋልና፣ ስለነሱ ይህንን ድንቅ ሥራ ሊያከናውን ፈቃዱ ሆኑዋልና። ንጉሡ ናቡከደነፆር ተደነቀ ፈጥኖም ተነሣ፤ አማካሪዎቹንም። “ሦስት ሰዎች አስረን በእሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን?“ ብሎ ተናገራቸው። እነርሱም አዎን እውነት ነው ብለው ለንጉሡ መለሱለት። እርሱም “እነሆ፥ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ ምንም አላቈሰላቸውም፤ የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል” ብሎ መለሰ። የዚያን ጊዜም ናቡከደነፆር ወደሚነድደው ወደ እሳቱ እቶን በር ቀርቦ “እናንተ የልዑል አምላክ ባሪያዎች፥ ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም፥ ኑ ውጡ” ብሎ ተናገራቸው። ሲድራቅና ሚሳቅም አብደናጎም ከእሳቱ መካከል ወጡ። መሳፍንቱና ሹማምቶቹም አዛዦቹና የንጉሡ አማካሪዎች ተሰብስበው እሳቱ በእነዚያ ሰዎች አካል ላይ ኃይል እንዳልነበረው፥ የራሳቸውም ጠጕር እንዳልተቃጠለች፥ ሰናፊላቸውም እንዳልተለወጠ፥ የእሳቱም ሽታ እንዳልደረሰባቸው አዩ። ናቡከደነፆርም መልሶ “መልአኩን የላከ፥ ከአምላካቸውም በቀር ማንም አምላክ እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ።” (ት. ዳን. 3) ብሎ ተናገረ።
ድንቅ የእግዚአብሔርን ሥራ ያየ ንጉስ ናቡከደነጾር እንኳን በራሱ የተናቀ ጣዖት አምልኮ አፍሮ፣ የናቀውን የሠለስቱን ደቂቅ አምላክ እግዚአብሔርን አክብሮ “እናንተ የልዑል አምላክ ባርያዎች” አለ፣ ሠለስቱ ደቂቅ የተናቀባቸውን አምላክ ለማክበር ስለሱ የእሳት መስዋእት በመሆን ከሀዲው ናቡከደነጾር “ልዑል አምላክ” እስኪል ድረስ ለእግዚአብሔር ታምነዋል። እነሱንም “እናንተ የልዑል አምላክ ባሪያዎች፥ ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም፥ ኑ ውጡ” እንዲላችው እግዚአብሔር ግርማ ሞገስን ሰጥቷቸዋልና። እሱ ቅዱስ እግዚአብሔር ሁል ጊዜም ታማኝ ነው። ታማኝ ልጆቹን እንዲህ በምክንያት ሲያገኝ፣ በተአምራቱ ልጆቹን ደስ ሊያሰኝ ከሀድያንን ሊያሳፍር በልጆቹ እና በቅዱሳን መላእክቱ ይገለጻል።
እንግዲህ እግዚአብሔር ለሚታመኑት ቅርብ፣ ለካዱት ሩቅ መሆኑን እሳት ውስጥ ተጥለው እሳቱ ባልነካቸው ሠለስቱ ደቂቅና የእሳቱ ወላፈን በገደላቸው የጣዖት አደግዳጊዎች ግልጽ ሆኖልናል። ዓለም ሁልጊዜም ቅርጽዋን እየለዋወጠች የምትማርካችው አደግዳጊዎቹዋን አታጣም። በነሠለስቱ ደቂቅ ዘመን ጣዖት አቁማ ኑ ስገዱ እያለች፣ ዛሬ ደግሞ በቀረጸቻቸው አድር ባዮች መሪነት ወይ በመናፍቅነት፣ ወይ በዓለማዊነት በፈቃዳችን ልታስተን ወጥመዱዋን እንደዘረጋች ከቶም ለአፍታ መዘንጋት የለብንም።
ባጠቃላይም ሕይወት የአንድ ጊዜ ሙከራ ናትና ድጋሚ የላትም። ይችን እድል ሠለስቱ ደቂቅ በተገቢው ተጠቅመውባታል። መጽሐፍ “ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፣ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል።” ማቴ. 16፥25 እንዲል። እኛም እውነት ነው የተጠራነው በረከትን በእምነት እንድንቀበል ነው። በዚያውም ሥጋዊ ክብር፣ ንዋይና ወረት የሚንጠውን ትውልድ ሕመም የተረዳን የአንድ ጊዜ እድሉን እንዳያጣ ተስፋውን ማመላከት ግድ ይለናል። ግን ትውልዱ አይጨበጤ ነው፣ አያናግርህ፣ ጆሮ አይሰጥህ። ገና ልትነግረው ሀ ን ስትጀምርለት ከየመንደሩ በቃረመው ብልጠት ሆ ብሎ ይቀድምሀል። ችግሩን ነግረሀው ማርከሻውን ሳትሰጠው ሞጭልፎህ ይሄዳል። አንዳንዱ የህይወቱ ታሪኩ ከጽንስ ጀምሮ ወጥነት የጎደለው ከዚህም ከዚያም ውጥንቅጥ የተማሪ ኮፌዳ ውስጥ እህልን ይመስላል። (እመጓ 162) ከመደበኛው የመዳን እውን እውቀት ይልቅ ለሳቅ የሚመቸውን ይመርጣል። ቤተክርስቲያን ለዘመናት እራሱዋንም ሆነ ሀገርና ህዝብ ጠብቃ ካቆየችበት በዐይን የሚታይ፣ በእጅ የሚዳሰስ እውቀት ይልቅ ፈርሶ በስብሶ በወደመ በመናፍቅ ጥቅስ ይኩራራል። ሌላው የግሎባላዜሽን (ዓለማዊነት) ፈረስ ሆኖ፣ ዓይነ ልቦናው ታውሮ፣ በራሱ አፍሮ ስሙን፣ ትውልዱን፣ ዘሩን፣ ሀገሩን፣ ማንነቱን፣ እምነቱን ይረግማል። ታዲያ በዚህ ሁሉ ለተጎዳ ወገን ከእርም ይወጣ ዘንድ እንዲያመላክተው የሠለስቱ ደቂቅ ህይወት ምሳሌ አይሆነው ይሆን?
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር