በጀርመን ካስል ደብረ ቀራንዮ መድኃኔ ዓለም ቤተክርስትያን ዐውደ ርዕይ ተካሄደ

በጀርመን ንዑስ ማእከል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በአውሮፓ ማእከል የጀርመን ንዑስ ማእከል አዘጋጅነት “ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፤ ድርሻችንን እንወቅ” በሚል መሪ ቃል የካቲት 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በካስል ደብረ ቀራንዮ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ዐውደ ርዕይ ተካሄደ።

ዐውደ ርዕዩን የካስል ደብረ ቀራንዮ መድኃኔ ዓለም እና የሐምቡርግ ደብረ መድኃኒት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስትያን አስተዳዳሪ መጋቤ ምሥጢር ኅሩይ ኤርምያስ (ዶ/ር) በጸሎት የከፈቱት ሲሆን፤ ከ50 በላይ ምዕመናን ተመልክተውታል። ዐውደ ርእዩ በዋናነትም በአራት ክፍሎች የተደራጀ ሲሆን ስለ ቤተክርስቲያናችን መሠረተ እምነት፣ ስለ ሐዋርያዊ አገልግሎት ምንነትና እና የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የሐዋርያዊ አገልግሎት ጉዞ፣ በዓለምና በኢትዮጵያ በተለያዩ ክፍላተ ዘመን ስለነበረው የቤተ ክርስቲያን ተጋድሎ፣ እና ወቅታዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተጋድሎ (በተለይም ከአክራሪ እስልምና ች እና ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ጋር ያለው ተጋድሎ) በድምጽ ወምስል የታገዘ ገለጻ በዝርዝር ቀርቧል፡፡ 

የጀርመን ንዑስ ማዕከልም ለዝግጅቱ መሳካት ከጅማሬ እስከ ፍጻሜ ከፍተኛ ትብብር ያደረጉትን የደብሩን አስተዳዳሪ እና ሰበካ ጉባኤ፣ በዐውደ ርእዩ ላይ በገላጭነት የተሳተፉትን የደብሩን ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት፣ ለዝግጅቱ መሳካት በተለያየ መልኩ እገዛ ያደረጉትን ምዕመናን በሙሉ አመስግኖ ይህ ቀና ትብብር ለወደፊትም እንደማይለየው ያለውን ጽኑ እምነት ገልጿል። 

በመጨረሻም መጋቤ ምሥጢር ዶ/ር ኅሩይ ኤርምያስ ከምንጊዜውም በላይ ለቤተክርስቲያን ህልውና በጋራ የምንቆምበት ጊዜ በመሆኑ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለመደገፍ ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽዖ ልናደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል። በተጨማሪም ደብሩ በአሁኑ ወቅት ያለበትን የሕንጻ ቤተክርስትያን ግዢ ዕዳ እንዳጠናቀቀ ማኅበረ ቅዱሳን በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚያደርገውን የገዳማት እና የአብነት ት/ቤቶችን ልማት እንቅስቃሴ በተለያዩ መንገዶች እንደሚደግፍ ቃል በመግባት መርሐ ግብሩን በጸሎት ዘግተዋል፡፡