የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሁለት የወረዳ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤቶችን አዋቀረ።

በአውሮፓ ማእከል ኅ/ኤ/ሚ ክፍል

የካቲት 2 ቀን 2009 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት የወረዳ ቤተክህነት ጽሕፈት  ቤቶችን  አዋቀረ። ሀገረ ስብከቱ የመላው አውሮፓ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ሙሴ መቀመጫ በሆነችው በጀርመን ሀገረ በምትገኘው የሮሰልስሃይም ከተማ ጥር 19 እና  20 ቀን 2009 ዓ.ም ጉባኤውን  አካሂዷል። በጉባኤው ላይ የአህጉረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ በሸንገን ስቴት ውስጥ ባሉ የአውሮፓ ሀገራት ያሉ የሀገረ ስብከቱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች እና ተወካዮች የተገኙ ሲሆን በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችንም አሳልፏል።

ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልእክት  በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት እና የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለማጠናከር ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በጠበቀ መልኩ በዚህ ሀገረ ስብከት በሸንገን ስቴት ውስጥ ያሉ አጥቢያዎችን የሚያስተዳድሩ የወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶችን ማዋቀር አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል። በዚህም መሠረት ጉባኤው ተወያይቶ የእስካንድኒቪያን እና የቤሉክስ ወረዳ ቤተክህነት ጽ/ቤቶችን አቋቁሟል። የእስካንዲኒቪያን ወረዳ ቤተ ክህነት በሥሩ በዴንማርክ፣ በስዊድን፣ በፊንላንድ፣ በኖርዌይ እና በአይስላንድ ያሉ አብያተ ክርስቲያናትን የሚያስተዳድር ሲሆን የቤሉክስ ወረዳ ቤተ ክህነት ደግሞ በሥሩ በኔዘርላንድስ፣ በቤልጂየም፣ በሉግሰንበርግ እና በኦስትሪያ ያሉ አብያተ ክርስቲያናትን ይይዛል።

ለሁለቱም ወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች አራት አራት የሥራ አስፈጻሚ አባላት (ማለትም፡ የወረዳው ሊቀ ካህናት፣ ጸሐፊ፣ የስብከተ ወንጌል ክፍል ሓላፊ እና የሰንበት ት/ቤት ክፍል ሓላፊ) ተመርጦ ተሰይሟል። ለእስካንዲኒቪያን ወረዳ ቤተ ክህነት በዴንማርክ የኮፐንሀገን ደብረ ምሕረት አማኑኤል እና የአርሁስ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም አቢያተ ቤተክርስቲናት አስተዳዳሪ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ዘሚካኤል ደሬሳ በሊቀ ካህናትነት ተመርጠዋል። ለዚሁ ወረዳ ቤተ ክህነት መጋቤ ምሥጢር ቆሞስ አባ ቴዎድሮስ ጸሐፊ፣ መጋቤ ብሉይ ቀሲስ ለማ በሱፍቃድ የስብከተ ወንጌል ክፍል ሓላፊ እና ዲ/ን ሳምሶን መለሰ የሰንበት ት/ቤት ክፍል ሓላፊ ሆነው ተመርጠዋል። ለቤሉክስ ወረዳ ቤተ ክህነት ደግሞ በቤልጂየም የአንትወርፕ ደብረ ስብሐት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑት መልአከ ምሕረት ቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ ካሣ  ሊቀ ካህናት ሆነው የተመረጡ ሲሆን፤ አቶ አበበ ብዙዓየሁ የወረዳ ቤተ ክህነቱ ጸሐፊ፣ አባ ገብረ ሚካኤል የስብከተ ወንጌል ክፍል ሓላፊ እና ዲ/ን አእመረ አወቀ ደግሞ የሰንበት ት/ቤት ሓላፊ ሆነው ተመርጠዋል።

northwest_d_meeting

 

ጉባኤው ትኩረት ሰጥቶ ካያቸው የመወያያ ነጥቦች  ውስጥ  በሀገረ ስብከቱ ያለውን የአገልጋይ ካህናት እና መምህራንን እንቅስቃሴ በተመለከተ አንዱ ነው። በውይይቱ ላይም ሳይላኩ ተልከናል፣ ሳይማሩ ተምረናል በማለት የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና እና ሥርዓት የሚያፋልስ ትምህርት የሚያስትምሩ መምህራን ላይ ጥብቅ ክትትል በማድረግ ምእመናንን  ከነጣቂ ተኩላዎች፣ ቤተ ክርስቲያንን ከዘራፊዎች መጠበቅ የሁሉም አገልጋዮች እና ምእመናን ሓላፊነት መሆኑን የአህጉረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሙሴ አሳስበዋል። ብፁዕነታቸው አክለውም በተዋቀሩት ወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ውስጥ ምን ያክል አጥቢያ አቢያተ ክርስቲያናት እንዳሉ፣ በሥራቸውም የሚያገለግሉ ካህናት፣ ዲያቆናት  እና መምህራን በተመለከተ ሙሉ መረጃ አጣርቶ ለሀገረ ስብከቱ እንዲቀርብ መመሪያ አስተላልፈዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ ሀገረ ስብከቱን ማጠናከር የሁሉም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሓላፊነት እና መንፈሳዊ ግዴታ መሆኑን አስረድተው፤ ሁሉም እንደየአቅሙ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል።  በመጨረሻም ጉባኤው በየዓመቱ በመላው አውሮፓ ያሉ አገልጋይ ካህናት ተገናኝተው የሚመካከሩበት እንዲሁም ሁሉም ምእመናን በአንድ ላይ በመሆን ትምህርተ ወንጌልን የሚማሩበት ሰፊ ጉባኤ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ከስምምነት ላይ ደርሷል። ይህንን ታላቅ ጉባኤ እውን ለማድረግ በአህጉረ ስብከቱ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት አገልጋይ ካህናት በሙሉ ሀሳብ ሰጥተውበት ሥራው እንደሚጀመር ተገልጿል።

ጉባኤው በእነዚህ እና በሌሎች የተለያዩ የመወያያ ነጥቦች  ላይ መክሮ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ በብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ ቃለ ምዕዳን እና ቡራኬ ተጠናቋል። ይህንን ጉባኤ ለማዘጋጀት በሀገረ ስብከቱ ሥር ያሉ አገልግጋይ ካህናት የሊቀ ጳጳሱን መመሪያ ተቀብለው ሲሠሩ መቆየታቸውም ታውቋል። በማበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማዕከልም  የተቋቋሙትን የወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች  ለማጠናከር፣ እንደ ልጅ ለመታዘዝ እና ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑንን ከማዕከሉ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።