የስዊዘርላንድ ግንኙነት ጣቢያ አዉደ ርዕይ አካሄደ።

 በስዊዘርላንድ ግንኙነት ጣቢያ

መስከረም 1 ቀን 2010 ዓ.ም.

ነሐሴ ፳ እና ፳፩ ፳፻፱ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤ/ማ/ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን አዉሮፓ ማእከል የስዊዘርላንድ ግንኙነት ጣቢያ ከስዊዘርላንድ የሎዛን ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ጋር በመተባበር በስዊዘርላንድ ሀገር ለሁለተኛ ጊዜ ልዩ የአብነት እና የገዳማት ቀን በሎዛን ከተማ አካሂዷል። የዕለቱ መሪ ቃል ”ኑ አብረን እንስራ፤ ለውጥም እናመጣለን” የሚል ነበር። መርሐ ግብሩን በስዊዘርላንድ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑት መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ኃይለ ጊዮርጊስ መሪነት በጸሎተ ተጀምሯል።  ከጸሎቱ መርሐ ግብር በኃላ መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ኃይለ ጊዮርጊስ የእንኳን አደረሳችሁ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም ከኢትዮጵያ የመጡትን ልዑካን አመስግነው ቤተክርስቲያናችን ዛሬ ያለንበት ድረስ ለመድረስ ገዳማት እና የአብነት ትምህርት ቤቶች ያደረጉትን አስተዋፅኦ ገልፀው አውደ ርዕዩን በይፋ ከፍተዋል።
DSC02341 DSC02412

አውደ ርዕዩ በሦስት ትይንቶች ተከፍሎ የቀረበ ሲሆን በመጀመሪያው ትዕይንት ፍኖተ ቤተ ክርስቲያን በሚል የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ ክርስቲያን ታሪክ ከህገ ልቡና ጀምሮ አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ ምን ይመስል እንደነበር፤ የቤተክርስቲያን አገልግሎት በአውሮፓ እንዴት እንደተመሰረተ እና አሁን ያለበት ደረጃንም ለመዳሰስ ተሞክሯል።  የዐውደ ርእዩ ቀጣይ ክፍል ስለ ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ዝርዝር ገለፃና ያጋጠሟቸዉን ተግዳራቶች እንዲሁም ማህበረ ቅዱሳን እንዴት የልማት ፕሮጀክቶትን ቀርፆ ለዉጦችን እያመጣ መሆኑን ገልጿል።  የመጨረሻው ትዕይንት የነበረው ስለ ማህበረ ቅዱሳን አመሰራረት፣ ራእይ እና የአገልግሎት አቅጣጫ እንዲሁም በአውሮፓ ማእከል  እና በስዊዘርላንድ ግንኙነት ጣቢያ ስላለው እንቅስቃሴ ሰፊ ማብራርያ ተደርጓል። ከትይንቶቹ ቦኋላም ስብከተ ወንጌል በዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ ተሰጥቷል።

DSC02379_2 DSC02375_2

እሁድ ከሰዓት ቦኋላ በነበረው መርሐ ግብርም በቪዲዮ የታገዘ ስለ ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ጠቅለል ያለ ገለፃ ተሰጥቷል። በዕለቱም በርከት ያሉ ምእመናን አና አገልጋይ ዲያቆናት ወንድሞች ከሎዛን እና ከተለያዩ የስዊዘርላንድ ከተሞች የተገኙ ሲሆን ምእመናንም ይህን መርሐ ግብር ያዘጋጀውን ማኅበረ ቅዱሳንን አመስግነው ሁልጊዜ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አንደዚህ አይነት አውደ ርዕዮች እና ገለፃዎች ቢደረጉ እና በተለያዩ ከተሞችም እንዲቀጥል ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

image-0-02-05-2a9c119feb869f4c92a60b21e5147d2182f56bffb3a7cf5f16c77e4487cab67e-V image-0-02-05-9348c3fa4c4113720b3a8a8a152361ae21a323acf69e160d089ed5bface2c42e-V (1)

በመጨረሻም መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ኃይለ ጊዮርጊስ ይህ መርሐ ግብር እንዲሳካ ድጋፍ ያደረጉትን ሁሉ አመስግነው ምዕመናን ገዳማትን ለመርዳት የሚያደርጉትን ጥረት እንዲቀጥሉ አሳስበው መርሐ ግብሩ በጸሎት ተዘግቷል።

የስዊዘርላንድ ግንኙነት ጣቢያም ለዝግጅቱ መሳካት ከጅማሬ እስከ ፍፃሜ ከፍተኛ ትብብር ያደረጉትን የደብሩን አስተዳዳሪ፣ ዐውደ ርእዩ እንዲካሄድ በተለያየ መልኩ እገዛ ያደረጉትን የሎዛን ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የሰበካ ጉባዔ አባላትን እና ምእመናን እንዲሁም አውደ ርእዩን በመጎብኘት እና በገንዘባቸው ድጋፍ በማድረግ የተባበሩትን ምእመናን በሙሉ አመስግኖ ይህ ቀና ትብብር ለወደፊትም እንደማይለያቸው ግንኙነት ጣቢያው ያለውን ጽኑ እምነት ገልጿል።