የዐቢይ ጾም ሳምንታት (ለሕፃናት) – ክፍል ሁለት
በልደት አስፋው
መጋቢት ፲፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ደኅና ናችሁ? እግዚአብሔር ይመስገን!፡፡ ልጆች! በልዩ ልዩ ምክንያት አልችል ብለን ዘግይተናል፡፡ በቅድሚያ በገባነው ቃል መሠረት ወቅቱን ጠብቀን ትምህርቱን ባለማቅረባችን እናንተን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡
ልጆች! የካቲት ፲፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ባቀረብንላችሁ ትምህርት ከሰባቱ አጽዋማት መካከል ዐቢይ ጾም አንዱ እንደኾነ፣ ዐቢይ ጾም ማለት ታላቅ ጾም ማለት እንደኾነ፣ ጾሙ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ጾም በመኾኑ ታላቅ እንደተባለ፣ ዕድሜአቸው ሰባት ዓመት ከኾናቸው ሕፃናት ጀምሮ ዅሉም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ዐቢይ ጾምን እና ሌሎችንም አጽዋማት መጾም እንደሚገባቸው፣ እንደዚሁም ስምንቱ የዐቢይ ጾም ሳምንታት (እሑዶች) ስማቸው ማን ማን እንደሚባል ነግረናችሁ ነበር፡፡
ልጆች! ሰባቱ አጽዋማት ማን ማን እንደሚባሉም ጠይቀናችሁ ነበር አይደል? መልሱንስ ጠይቃችሁ ተረዳችሁ? በጣም ጥሩ ልጆች! መልሱን እናስታውሳችሁ፤ ሰባቱ አጽዋማት የሚባሉት፡-
፩. ጾመ ነቢያት
፪. ጾመ ገሃድ (ጋድ)
፫. ጾመ ነነዌ
፬. ዐቢይ ጾም
፭. ጾመ ድኅነት (ረቡዕ እና ዓርብ)
፮. ጾመ ሐዋርያት
፯. ጾመ ፍልሰታ (የእመቤታችን ጾም) ናቸው፡፡
በአሁኑ ሰዓት ዐቢይ ጾምን እየጾምን ነው፡፡ የምንገኘውም ሦስተኛው ሳምንት ላይ ሲኾን ስሙም ‹‹ምኵራብ›› ይባላል፡፡ የሚቀጥለውና አራተኛው ሳምንት ደግሞ ‹‹መጻጕዕ›› ተብሎ ይጠራል፡፡
ልጆች! በዛሬው ዝግጅታችን ከመጀመሪያው እሑድ እስከ ሦስተኛው እሑድ (ከዘወረደ ጀምሮ እስከ ምኵራብ) ድረስ የሚገኙትን የዐቢይ ጾም ሳምንታት የሚመለከት ትምህርት ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ ትምህርቱን እንድከታተሉት በአክብሮት ጋብዘናችኋል!
፩. ዘወረደ
ልጆች! ከዐቢይ ጾም ሳምንታት መካከል የመጀመሪያው ሳምንት ‹‹ዘወረደ›› ይባላል፡፡ ዘወረደ ማለት ከላይ የመጣ፣ የወረደ ማለት ነው፡፡ ይህም አምላካችን ዓለምን ለማዳን ሲል ሥጋ መልበሱን (ሰው መኾኑን) ያመለክታል፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ ወርዶ፣ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቆ፣ ወንጌልን ለዓለም ካስተማረ በኋላ በፈቃዱ መከራ ተቀብሎ፣ በመስቀል ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ ከሙታን ተነሥቶ ዓለምን አድኗል፡፡ ልጆች! የመጀመሪያው ሳምንት የአምላካችን የማዳን ሥራ በስፋት የሚነገርበት ወቅት በመኾኑ ‹‹ዘወረደ›› ተብሎ ተሰይሟል፡፡
፪. ቅድስት
ሁለተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹‹ቅድስት›› ይባላል፡፡ ቅድስት ማለት የተለየች፣ የተመረጠች፣ የከበረች ማለት ነው፡፡ ልጆች! ለምን የተለየች፣ የተመረጠች፣ የከበረች እንደተባለች ታውቃላችሁ? ቅዱስ አምላካችን እግዚአብሔር ዓለምን (ሰውን) ለመቀደስ ሲል ወደ ምድር መምጣቱንና ዐቢይ ጾምን መጾሙን ለማስረዳት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሰንበትን ክብር ለማስገንዘብ ነው፡፡ ሰንበት ቅድስት፣ የተለየች፣ የተመረጠች፣ የከበረች ዕለት ናት፡፡ ስለዚህም ልጆች! ሁለተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹‹ቅድስት›› ተብሎ ይጠራል፡፡
፫. ምኵራብ
ልጆች! ሦስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ደግሞ ‹‹ምኵራብ›› ይባላል፡፡ ምኵራብ ማለት አዳራሽ ማለት ነው፡፡ ምኵራብ ድሮ የነበሩ የእግዚአብሔር ሰዎች መንፈሳዊ ትምህርት ይማሩበት የነበረ ሥፍራ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ይህንን የጸሎት ሥፍራ ሰዎች የንግድ ቦታ አደረጉት፡፡ ይህንን ዓለማዊ ተግባር ሲፈጽሙ የነበሩትን ዅሉ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል፡፡ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት›› ብሎ ከምኵራብ አስወጣቸው፡፡ ከዚያም ቃለ እግዚአብሔር አስተማራቸው፡፡ ልጆች! የእግዚአብሔር ቤት የጸሎት ቤት እንጂ የንግድ መነገጃ ሥፍራ አለመኾኑን ከዚህ ታሪክ እንማራለን፡፡
ለዛሬው በዚህ ይቆየን፡፡ ቀጣዩን ትምህርት ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በሚቀጥለው ዝግጅት ይዘንላችሁ እንቀርባለን፡፡ እስከዚያው ድረስ ሰላመ እግዚአብሔር ከዅላችን ጋር ይኹን!